“ዕድሜ ይስጥልኝ!”

0
156

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፅንሰ ሀሳብ እንደየ ኅብረተሰቡ የዕድገት ደረጃ እና አካባቢያዊ ሁኔታ በመለያየቱ አንድ ወጥ ትርጉም የለውም::  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ”የሁሉም የማኅበረሰብ አካል የሥልጣኔ  ውጤት ነው” ይለዋል::

ፅንሰ ሀሳቡ ሲተነተን የበጎ ፈቃድ  አገልግሎት በተለያዩ መስኮች እያንዳንዱ ሰው ያለ ትርፍ ፍለጋ እና ያለ ክፍያ ሙያዊ አጽንዖት ባልተጫነው ሁኔታ ለማያውቋቸው ግለሰቦች እና ለማያውቋቸው ጎረቤቶቹ፣ ለማኅበረሰቡ እና በጠቅላላው ለሕዝብ የሚያበረክተው  አስተዋጽዖ መሆኑን ያመላክታል::

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕድሜ እና ፆታ፣ ማኅበራዊ ደረጃ፣ መልከዐ ምድራዊ አቀማመጥ  ሳይገድበው የሰብዓዊነት መርህን ብቻ መሠረት በማድረግ የሚሰጥ ወይም የሚከናወን ተግባር ነው:: በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማለት ተሳታፊዎች በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ በማድረግ ውስጣቸው ከሚሰማቸው ሰብአዊ አመለካከት ተነስተው ለማኅበረሰቡ ሰፊ የልማት አውታሮችን በመዘርጋት የዜግነት ኃላፊነትን የሚገነዘቡ ሀገራዊ እና ብሔራዊ ግዴታዎችን የሚያውቁበት፣ በማኅበራዊ ሚናዎች ስር ግንባር ቀደም የሚሆኑ፣ የሀገር እና የወገን ፍቅርን የሚያዳብሩበት ትልቅ ሚና ያለው ተግባር ነው::

በጎ ፍቃድ የሚሠሩ ወጣቶችም  የእረፍት ጊዜያቸውን ተጠቅመው  ልማትን ለማምጣት ለአካባቢ ደሕንነት በነጻ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን ፣ ጉልበታቸውን እና ዕውቀታቸውን ከማዋል በተጨማሪ በጎ አመለካከትን የሚያሰርጹበት ተግባር  እንደሆነ መረጃው አመላክቷል:: በጎ ፈቃድ የተቸገሩትን  ከመርዳት ባለፈ  በጎ ምኞትን ተላብሰው ከማኅበረሰባቸው ጎን ሆነው የሚያውቁትን የሚያስተምሩበት እና ከሌሎች አካላትም የሕይወት ክህሎት የሚቀስሙበት ዋነኛ መንገድ መሆኑን መረጃው አመላክቷል:: በመሆኑም በጎ ፍቃደኝነት ዕድሜ፣ ጾታ፣ መልከዐ ምድራዊ ወሰን ሳይገድበው በሰብአዊነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚሰጥ አገልግሎት ነው::

የወጣቱን ማኅበራዊ ተሳትፎ ለማበረታታት፣ ለማሳደግ እና  ዕምቅ አቅሙን ለመጠቀም፣ ለሕፃናት እና ለታዳጊ ወጣቶች አርዓያ (ሞዴል) የሚሆን  ትውልድ ለማፍራት፣ በመንግሥት እና በኅብረተሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት፣ ለኅብረተሰቡ ተቆርቋሪ እና የኃላፊነት ስሜት የሚሰማው ዜጋ በማፍራት ከአልባሌ ቦታዎች ርቀው ኅብረተሰቡን ሊጠቅሙ በሚችሉ የሥራ መስኮች የሚሰማሩበትን ዕድል ይፈጥራል – በጎ ፈቃድ አገልግሎት::

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት  የዜግነት ኃላፊነትን እንዲገነዘቡ፣ ሀገራዊና ብሔራዊ ግዴታቸውን እንዲያውቁና በማህበራዊ ሚናዎቻቸው ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሀገርንና የወገንን ፍቅር የሚያዳብሩበት ሁኔታ ለመፍጠር ብሎም ዓለማዊ ተግዳሮቶችን ተቋቁመውና ጠንካራ የሥራ ፍላጎት አዳብረው ራዕያቸውን ማሳካት የሚችሉ ወጣቶችን ለማፍራት የሚረዳ ተግባር ነው::

ለሀገር፣ ለወገን ፣ ለራስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው የበጎ ፈቃድ እንዴት? እና መቼ ተጀመረ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም:: በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በጎ ፈቃድ መቼ እንደተጀመረ የሚያመላክት መረጃ ባይኖርም የረጅም ጊዜ ታሪክ እንዳለው አመላካች ተግባራት አሉ:: ለምሳሌ ፍሎረንስ ናይታግኒ የተባለች እንግሊዛዊት እ.አ.አ ከ1810 እስከ 1930 በክሪሚያ ጦርነት ወቅት የጦር ጉዳተኞችን በመንከባከብ እና ሆስፒታሎችን በማጽዳት የብዙዎችን ሕይወት ማትረፏን /tour-florence.info/ መረጃ ይጠቁማል::

በኢትዮጵያም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መቼ እና በማን እንደተጀመረ የተጠናከረ መረጃ ባይኖርም የረጅም ጊዜ የአገልግሎት ታሪክ እንዳለው ይታመናል:: ለዚህም ኢትዮጵያዊያን በጦርነት እና በችግር ጊዜ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ልምዳቸው ከፍተኛ ነው:: በተለይ በ1962 ዓ.ም ከውጭ የመጡ 279 አሜሪካዊያን በጎ ፈቃደኛ መምህራን ጽንሰ ሀሳቡ የበለጠ እንዲሰርጽ አድርገዋል::

በተደራጀ መንገድም ባይሆን በሀገራችን ሲፈፀም የቆየው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የክረምት እና የበጋ በሚል መርሐግብር ተጀምሮ ዛሬ ድረስ ዘልቋል::

ዘንድሮም “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው  የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ:: ወጣቶቹ  በቀይ መስቀል አገልግሎቶች (ደም ልገሳ)፣ በትምህርት አገልግሎት መሠረተ ትምህርትን በማስፋፋትና ለመደበኛ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ በጤና  ( በሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት፣ በተላላፊ በሽታዎች መከላከል)፣ በማኅበራዊ ደህንነትና በማህበረሰብ ልማት አገልግሎት (ወላጆቻቸውን እና ደጋፊዎቻቸውን በተለያዩ ምክንያት ያጡ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን በመርዳት)… ይሳተፋሉ ::

እኛም በባሕር ዳር ከተማ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዴት እየተከናወነ ነው? በማለት  ከተሳታፊ ወጣቶች ጋር ቆይታ አድርገናል:: በከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች  ይሳተፋሉ:: ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ዓብይ ጋሻው አንዱ ነው:: ወጣቱ በበጋ በበጎ ፋቃድ አገልግሎት የማስተማር ሥራ ያከናውናል:: በክረምቱ ወቅት ደግሞ ከሀምሌ አጋማሽ ጀምሮ በፋሲሎ ክፍለ ከተማ በአጼ ሰርፀ ድንግል አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ከአምስተኛ  ክፍል ጀምሮ ላሉ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣል::

ዓብይ እንደሚለው ተማሪዎች የክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን ማጠናከሪያ ትምህርት በመውሰድ ማሳለፋቸው  አልባሌ ቦታ እንዳያሳልፉ፣ እና ለቀጣዩ የትምህርት ጊዜ ግንዛቤያቸው እንዲሠፋ ያስችላቸዋል:: ለእሱ እና ለሌሎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተሳተፉ ወጣቶች ጊዜያቸውን ከማኅበራዊ ሕይወት ከሚያሳልፉት ጊዜ በመቀነስ ሌሎችን መደገፍ መንፈሳዊ እርካታ የሚያገኙበት ሂደት እንደሆነ ነው የሚገልፀው::

በበጎ ፍቃድ የተሰማራ ወጣት ምስጋና ጠብቆ ሳይሆን ካለው ጊዜ ቀንሶ ሌሎችን በተለያየ ዘርፍ ማገልገል ዓላማ ያለው ተግባር  እንደሆነ ያነሳው ዓብይ፤ በቤት ጥገና፣ የወባ መራቢያ  ማፋሰሻ ቦይን በማጽዳት፣ ችግኝ በመትከል እና አረጋዊያንን በመንከባከብ  ከሌሎች ወጣቶች እና ወጣት ማህበራት ጋር ያገለግላል:: በክረምት ወቅት ደግሞ ከሃምሌ 15 እስከ ነሀሴ 25 የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ያሳልፋል::

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል በባሕር ዳር ፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ እማሆይ ያልጋ ወርቁ አንዷ ናቸው::  እማሆይ  ያልጋ ወርቁ በበጎ ፈቃደኞች ቤታቸው በመጠገኑ በክረምት የነበረውን ስቃይ ሲያስታውሱ፤  “የረባ ያልጋ ልብስ እንኳን በሌለው ባዶ ጎጆ የክረምቱ ዝናብ በቤቴ ዙሪያውን እየፈሰሰ ሲያስቸግር መተኛት ቀርቶ መቀመጡ ለኔ አይነት እርጅና ለተጫነው ሰው አይታሰብም ነበር! ክረምት ሲመጣ አጥንትን ሰርስሮ የሚገባው ብርድ ከእርጅና በተጨማሪ ለበሽታ ይዳርገኝ  ነበር”በማለት ነው::

በዘንድሮው ክረምት በወጣቶች በጎ ፍቃድ የቤታቸው ጣሪያ ሙሉው ፈርሶ እንደገና በመታደሱ ካለፉት የክረምት ወቅቶች የተለየ ጊዜን እያሳለፉ ነው፤ ዘንድሮ ቤታቸው አያፈስም:: በቤት ውስጥ ይገባ ከነበረ ዝናብ እና ጎርፍ የታደጓቸውን በጎ ፈቃደኛ ሰዎች  ሁሉ “እድሜ ይስጥልኝ!” በማለት አመስግነዋል::

በወጣትነት የእድሜ ክልል ተሯሩጠው ይሠሩ እንደነበር ያስታወሱት የ78 ዓመቷ እማሆይ ያልጋ፤ እድሜያቸው  ሲጨምር ግን ጧሪ እና ደጋፊ በማጣታቸው እጃቸውን ለእርዳታ ለመዘርጋት  መገደዳቸው እንዳሳዘናቸው  ነው የተናገሩት:: ”የወጣቶች የዛሬ በጎ ተግባር ከቀጠለ ነገም ከነገ ወዲያም የወደቀን የሚያነሳ፣ ለወደቀው የሚደርስ፣ አይዞህ! ባይ በጎ ትውልድ ይመጣል እና በጎ ተግባሩ  ወደ ፊትም ይቀጥል” የሚል ጽኑ ምኞታቸውን አሳውቀዋል::

የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ማኀበራዊ ልማት ዘርፍ ጽ/ቤት መረጃ መሰረት በክፍለ ከተማው የክረምት የዜጎች በጎ ፍቃድ አገልግሎት 17 ሺህ 509 ወጣቶች ፣ 11 ሺህ 670 ሌሎች የማኀበረሰብ ክፍሎች በጥቅሉ ከ29 ሺህ በላይ ዜጎች በ4 ቱ ቀበሌ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝ ነው::

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here