ዘመንን በሰላም አሻጋሪዉ ድልድይ

0
137

ጆን ኤፍ ኬኔዲ ሁሉም ለእውነተኛ ሰላም ጥረት ሊያደርግ እንደሚገባ ሲናገሩ ሰላም በምድር ላይ ያለው ሕይወት ዋጋ ያለው እንዲሆን ስለሚያደርግ፣ ሰዎች እና ሀገራት እንዲያድጉ፣ ተስፋ እንዲያደርጉ እና ለልጆቻቸው የተሻለ ሕይወት እንዲገነቡ እንደሚያስችል እምነትን አሳድረው ነው::

ሰላም እንዴት እና መቼ ይገነባል? ለሚለውም ጆንኦፍ ኬኔዲ ምላሽ የሰጡበት ንግግራቸው በተለይ ለዛሬዋ ዓለም ትልቅ ትርጉም ያለው ይመስላል:: “ሰላም በየዕለቱ፣ በየሳምንቱ፣ በየወሩ፣ በየዓመቱ እየተገነባ የሚሄድ፤ በሂደትም የሰዎችን መጥፎ አመለካከት እየቀየረ አዲስ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው”የሚል ነው::

የሀገር ዳር ድንበርን ለማስጠበቅ ከሚደረጉ ጦርነቶች በተጨማሪ ውስጣዊ ልዩነቶች በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት ፍላጎትን በኀይል ለማሳካት ጥረት ማድረግን ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በእርስ በርስ የግጭት አዙሪት ውስጥ እየተመላለሱ ይገኛሉ:: የቴክኖሎጂ ዕድገትን ተከትሎ ሀገራት ወደ ጦር መሣሪያ ማምረት ሽቅድድም ውስጥ መግባታቸው፣ የሳይበር ጥቃቶች መጨመር፣ የታጣቂ ኅይሎች እና የሽብር ቡድኖች በቁጥርም ሆነ በአቅም እየተደራጁ መምጣታቸው ዓለም ከግጭት አዙሪት እንዳትወጣ ማድረጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል:: የዓለም አቀፍ ትብብር ውጥረት ውስጥ መግባቱ በሁሉም መልኩ ግጭት እና ሁከትን የመከላከል እና የመፍታት አቅም እየቀነሰ መምጣት የዛሬዋ ዓለም ፈተናዎች ሆነው ዘልቀዋል::

የበርካታ የዓለም ሀገራት ችግሮች በሐሳብ የበላይነት መፍትሔ እንዲያገኙ በወሬ እየወተወቱ ቢሆንም እውነታው የኀይል የበላይነት ሚዛን የሚደፋ መስሏቸው የገቡበት ጦርነት ንጹሀን ዜጎችን ለከፋ ስቃይ እና መከራ ዳርጓቸዋል:: ሩስያ ከዩክሬን እንዲሁም እስራኤል ከጋዛ የገቡበት ጦርነት ዓለም ወደ ከፋ መጠፋፋት እንድትገባ እየገፋፋት እስኪመስል እየተስተዋለ ነው:: ሶሪያ እና ዩጎዝላቪያ በእርስ በርስ ጦርነት ሕዝባቸው ለመከራ መዳረጉ ይታወሳል:: የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነትም ሕዝቡን ዛሬም በስቃይ ውስጥ እንዲያልፍ አድርጎታል::

ኢትዮጵያም በተለይ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ሳትፈልግ የገባችበት የሰሜኑ ጦርነት ዳፋ ዛሬም ቀጥሎ በተለያዩ አካባቢዎች መፍትሔ ርቋቸው የቀጠሉ ግጭቶች ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉት ነው:: የሰሜኑ ጦርነት የአማራ ክልልን ጨምሮ ኢትዮጵያን ለሁሉ አቀፍ ኪሳራ ዳርጓት መቋጫው ሰላማዊ ስምምነት ቢሆንም ጦርነቱ ግን መልኩን ቀይሮ አሁንም ድረስ ቀጥሏል:: በተለይ ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው የሰላም እጦት የአማራ ክልል የትውልድ ክፍተት እንዲያጋጥመው፣ በምጣኔ ሐብት ወደ ኋላ እንዲመለስ፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩ እንዲላላ እና እርስ በራሱ በመጥፎ እንዲተያይ ለሚያደርጉ ቁርሾዎች እየዳረገው ይገኛል::

የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ በመንግሥት በኩል እየተገለጸ ይገኛል:: ችግሩ አሁንም ሥር ነቀል መፍትሔ ባለማግኘቱ  የሚፈጠሩ ቀውሶች ግን እንደቀጠሉ ናቸው:: ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ከሰላም እና ደኅንነት ስጋት ነጻ አለመሆናቸው፣  የክልሉ የትምህርት እንቅስቃሴ አሁንም ድረስ ወደተሟላ ደረጃ አለመመለሱ፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች ከስጋት ነጻ ሆነው በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ባለመግባታቸው የክልሉ ገቢ ወደ ሚፈለገው ደረጃ አለመሸጋገሩ… አሁንም ለሰላም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ የማንቂያ ደወል ነው::

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ለክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፣ አሁንም እያደረሰ ይገኛል:: በዓመቱ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም:: በዚህም አገላለጽ መሠረት 2 ሚሊዮን 543 ሺህ 128 ተማሪዎች ብቻ የተማሪ ምዝገባ አከናውነው በመማር ላይ ይገኛሉ:: በክልሉ 40 በመቶ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዳልጀመሩ የገለጹት ኃላፊዋ፣ ማሳያ አድርገው ያነሱት አሁንም ድረስ በ17 ወረዳዎች ትምህርት ቤቶች አለመከፈታቸውን  ነው::

መማር ማስተማሩን ውጤታማ ለማድረግ ከሚያስችሉ ሁነቶች መካከል አንዱ  የተማሪ መጻሕፍት ለዝርፊያ እና ውድመት መጋለጣቸውን፣ ትምህርት ቤቶችም በታጠቁ ኀይሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና የመምህራን ግድያ መፈጸሙንም ኃላፊዋ ጠቁመዋል:: እነዚህ ሁሉ በትምህርት ዘርፉ ላይ የተፈጸሙ ችግሮች የትምህርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባና በክልሉ የትውልድ ክፍተት እንዲፈጠር የማድረግ ዕድሉ ከፍተኛ ስለሚሆን ችግሮች በውይይት ሊፈቱ ይገባል የሚሉት በርካቶች ናቸው::

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ በቀጣይ ሕዝቡን እና መንግሥታዊ መዋቅሩን በማወያየት ትምህርትን አጀንዳ ማድረግ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በመጠገን ወደ ሥራ ማስገባት፣ የተዘጉ ትምህርት ቤቶችን ማስከፈት፣ ተማሪ ማስመዝገብ እና መማር ማስተማሩን ማስቀጠል ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው::

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በክልሉ ገቢ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩም ተመላክቷል:: የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ለአሚኮ እንዳስታወቀው የጸጥታ ችግሩ ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ በክልሉ የገቢ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል:: ለአብነት በ2015 በጀት ዓመት  119 ሺህ 605 ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ አልከፈሉም። ይሁን እንጅ በተያዘው በጀት ዓመት በየደረጃው ያሉ የገቢ ተቋማት የተለያዩ አማራጮችን በማስቀመጥ የሚጠበቀውን ግብር እያስከፈሉ እንደሚገኙ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰን እና አሠባሠብ ክትትል ዋና የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አትንኩት በላይ አስታውቀዋል::

አሁንም 80 በመቶ የሚሆኑት ግብር ከፋዮች የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እንደሚገኙ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል:: በክልሉ ውስጥ 501 ሺህ 184 ግብር ከፋዮች ቢኖሩም 200 ሺህ 461 ግብር ከፋዮች በወቅታዊ ችግር ምክንያት የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈል እንዳልቻሉ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል:: በመሆኑም ግብራቸውን በወቅቱ መክፈል ላልቻሉ ግብር ከፋዮች ተጨማሪ የክፍያ ጊዜ መሰጠቱን ቢሮው አስታውቋል::

ታዲያ በተደጋጋሚ በጦርነት አዙሪት እየደረሰ ካለው መጠነ ሰፊ ጉዳት ለመውጣት ቀዳሚው መፍትሔ ምንድን ነው? ለሚለው መንገዱን ማመላከት ይገባል:: ችግሮችን መተማመን ላይ በተመሠረተ ውይይት መፍታትን ማስቀደም ዋናው የሰላም ምሰሶ መሆኑን ያስታወቁት የታሪክ እና የባሕል ምሁሩ ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው:: የሥልጣን ጥማት መተማመን እና ሰላምን ያጠፋል በማለት ነዉ  ምሁሩ የገለጹት::

“መጋደል የሚጠቅመን ቢሆን ኖሮ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ ትጠቀም ነበር፤ ሰላም የሚያመጣም ቢሆን ኢትዮጵያ እስካሁን ሰላም ይመጣላት ነበር። ነገር ግን ይሄ አልሆነም፤ በአንደኛው ጦርነት የሞቱትን ሰዎች ሳንቀብር፣ ለወገኖቻቸው ሳናረዳ ወደ ሌላ ጦርነት መግባት የተገባ አይደለም” ብለዋል::

በተከታታይ እየተደረጉ ያሉ ጦርነቶች በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሱት ያለውን ጉዳት በመረዳት ጥይት እየገዙ ከመገዳደል ይልቅ እየተወያዩ ማልማትን ማስቀደም እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ አስገንዝበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here