አውስትራሊያ የተወለዱት ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን እና ኒውዚላንድ የተወለዱት ባለቤታቸው ዶ/ር ሬግናልድ ሃምሊን በ1950 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት አዋላጅ ሀኪሞችን በአዲስ አበባ ልዕልተ ፀሐይ ሆስፒታል ለመቅጠር ያወጣውን ማስታወቂያ ሰምተው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ወሰኑ። በ1959 ዓ.ም ሃኪሞቹ ባልና ሚስቶች ውቅያኖስ አቋርጠው አዲስ አበባ ገቡ።
ካትሪን ሃምሊን እና ባለቤታቸው ሬግናልድ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እቅዳቸው ለሦስት ሳምንታት ብቻ ቆይተው ወደሀገራቸው በመመለስ የቀድሞ ሥራቸውን ማሳለጥ ነበር። ገና የኢትዮጵያን መሬት በረገጡባት ምሽት ግን አንድ የማሕጸን ሃኪም “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፊስቱላ ሁኔታ ልባችሁን ይሰብረዋል” ሲል ነገራቸው።
በዚያን ወቅት ታዲያ ጥንዶቹ የፊስቱላን በሽታ አይተው አያውቁም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የማሕጸን ፊስቱላ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ጠፍቶ ለዚሁ ተግባር ተብለው የተሠሩ ሆስፒታሎችም ተዘግተው ነበርና ነው። ኒውዮርክን የመሳሰሉት ትልልቅ ከተሞችም በሽታውን አጥፍተው ገና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ነበር የፊስቱላ ሆስፒታሎቻቸውን የዘጉት።
በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የኖሩት እነካትሪን ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ በሽታ ምንም አይነት ህክምና እንደሌለውና በርካቶችን እያሰቃየ እንደሆነ እውቀቱ አልነበራቸውም። ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነባራዊ ሁኔታውን ማየት ሲችሉ ግን ተገረሙ።
በእርግጥም ያ የማሕጸን ሃኪም እንደነገራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያጋጥመው ፈውስ አልባ የሴቶች የፊስቱላ በሽታ የነካትሪን ልብ ተሰበረ።
ጥንዶቹ የቀዶ ሕክምና ሙያተኞች ታዲያ ለሦስት ሳምንታት የመጡበትን የኢትዮጵያ ቆይታ በማራዘም በፊስቱላ ምክንያት የሚገለሉትን ኢትዮጵያዊያን ለሦስት ዓመታት ለማከም ወስነው ወደ ሥራ ገቡ። ሥራቸውም ፈጣን ለውጥ አስመዘገበ።
ሦስት ዓመት ሲሞላቸው ግን አዳዲስ የበሽታው ተጠቂዎች በመገኘታቸው ወደ አውስትራሊያ ከመመለስ ይልቅ በዚሁ ሥራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መቀጠል እንዳለባቸው ባልና ሚስቱ ወሰኑ። ለሥራቸው እንዲያግዛቸው አንድ የሕክምና ተቋም ማቋቋም ደግሞ ተከታዩ እቅዳቸው ነበር። እናም ወደ ኢትዮጵያ በመጡ በአስራ አምስተኛ ዓመታቸው አዲስ አበባ ውስጥ በ1964 ዓ.ምየፊስቱላ ማዕከል ሆስፒታል አሰገንብተውሥራ ጀመሩ።
ዛሬ የኢትዮጵያ ሃምሊን ፊስቱላ ማዕከል የማሕጸን ፊስቱላን ለማጥፋት በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርአያነት የሚታይ ተቋም ነው። በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ ሙከራዎችን አድርጎ ሴቶችን ከሕመማቸው ፈውሶ ወደ ትክክለኛ የሕይወት መስመራቸው የሚያስገባና በቤተሰባቸው እና በማሕበረሰባቸው ያላቸውን ሚና እንዲያስቀጥሉ የሚያስችል ተቋም ሆኗል።
ለሦስት ሳምንታት ሥራ ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን ኢትዮጵያን ሀገራቸው አድርገው ላለፉት 61 ዓመታት ከሞት ጋር የሚታገሉ የፊስቱላ ታካሚዎችን ወደ ሕይዎት እየመለሱ የሙያ እና የሞራል ግዴታቸውን ማድረግ ከሚችሉት በላይ ሲከፍሉ ከቆዩ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ባስገነቡት የፊስቱላ የሕክምና ማዕከል ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው ቤታቸው በ96 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል።
ካትሪን ሃምሊን እና ባለቤታቸው ሬግ ከ15 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለዚሁ ተግባር ብቻ ሆስፒታል ገንብተው የጀመሩት ተግባር ዛሬ ቀጥሏል:: ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ትኩረት እንዲያገኝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ እንዲሁም በሀገራችን ለዘጠነኛ ጊዜ በየዓመቱ ግንቦት 15/ሜይ23/ ዕለቱ ታስቦ ይውላል::
”ዑደትን በመስበር ፊስቱላን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንከላከል” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ታስቦ ውሏል:: ዕለቱ በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ተቋማት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተው ውይይት አድርገዋል::
ለመሆኑ በወሊድ ወቅት ፊስቱላ እንዴት ይከሰታል? ለሚለው እናቶች ለፊስቱላ የሚዳረጉት በወሊድ ወቅት የምጥ ሂደት ሲራዘም በሚፈጥር ውስጣዊ ጉዳት በጽንሱ መተላለፊያ /ቡርዝ ካናል/ እና በፊንጢጣ መካከል ሽንቁር ይፈጠራል:: በዚህ ወቅት ሽንት ወይንም ዐይነ ምድር ወይንም ሁለቱን ለመቆጣጠር ችግር ሲፈጠር መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች በዕለቱ አብራርተዋል::
ለዚህ ችግር የሚጋለጡትም ቅድመ ወሊድ ክትትል ለማድረግ የጤና ተቋማት በየአቅራቢያው አለመኖር፣ ማህበራዊ ተጽእኖዎች /በቤቷ ብትወልድ ይሻላል/ የሚል አስተሳሰብ፣ በጤና ተቋም ምርመራ እና ክትትል አለማድረግ፤ ብታደርግም ተገቢውን የህክምና መፍትሄ ማመላከት የሚያስችል ክህሎት ያላቸው ባለሞያዎች እጥረት… ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ የጤና ባለያዎች አረጋግጠዋል::
በዓለም አቀፍ ደረጃ እናቶችን ለከፋ አደጋ የሚዳርጋቸውን ፊስቱላ አሜሪካ ከ1935 እስከ 1950 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ትኩረት አድርጋ በመሥራቷ መቆጣጠር መቻሏም ተጠቁሟል::
በዕለቱ በጤና ቢሮ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት እና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ ልየው እንደገለፁት በክልሉ የፊስቱላ ተጠቂዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ነው:: በሽታው በአብዛኛው በተራዘመ ምጥ፣ በልጅነት በሚፈፀም ጋብቻ እና በሌሎች ተዛማጅ ችግሮች እንደሚከሰትም አንስተዋል::
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ እናቶችን በወሊድ ጊዜ ከሚገጥማቸው ፊስቱላ ለመታደግ ከጐንደር ዩኒቨርሲቲ እና ከባሕር ዳሩ ሐምሊን የፊስቱላ ማዕከል ጋር በመተባበር ተጠቂዎች የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀጠም የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው:: ይሁንና አሁን ላይ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መናጋት ”ከድጡ ወደ ማጡ” እንደሚባለው ነፍሰጡሮች በሰለጠነ የጤና ባለሙያ እንዳይገላገሉ አድርጓቸዋል:: ከዚህ ባለፈ ችግሩ የተከሰተባቸው እናቶች ፈጥነው ወደ ማዕከላት ለመድረስ የመጓጓዣ እጥረት ገጥሟቸዋል:: ተባባሪ አካላትም ተጠቂዎችን እንደበፊቱ አፈላልጐ ለማግኘት የሰላሙ እጦት ሌላ ጫና መፍጠሩ በዕለቱ ተጠቁሟል::
በክልሉ ባለፈው ዓመት ብቻ በተደረገ ልየታ 475 እናቶች የፊስቱላ ተጠቂ መሆናቸው መረጋገጡን በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶች ጤና አስተባባሪ ዶ/ር ኤርሚያስ አዱኛ ተናግረዋል:: ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 321ዱ በባሕር ዳር ሐምሊን የፊስቱላ ሕክምና ማዕከል እና በጐንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ህክምና ተደርጐላቸው ፈውስ አግኝተዋል::
ይሁንና የፊስቱላ ተጠቂ እናቶች መዳን የሚችለውን ጉዳት ”የፈጣሪ ቁጣ ነው!” በሚል እምነት ትዳራቸውን እንደሚፈቱ፣ ቤተሰቦቻቸው በሚፈጠረው ፈሳሽ ሽታ ከቤት አውጥተው ብቻቸውን እንዲኖሩ እንደሚያደርጓቸው፣ ከማህበራዊ ሕይወታቸው እንደሚገለሉም የጤና ባለሙያዎች በሚያደርጉት ክትትል ማረጋገጣቸውን መስክረዋል:: አሁን ላይ ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉንም ባለሙያዎች አንስተዋል::
በተራዘመ/በተስተጓጎለ/ ምጥ የሚገላገሉ እናቶች ከእምስት በመቶ በላይ በሕይወት ያለ ልጅ የመውለድ እድል እንደ ሌላቸውም ባለሙያዎች ተናግረዋል:: በአጠቃላይ በዓለም ላይ በዓመት ከ37 ሺህ እስከ 39 ሺህ እናቶች በፊስቱላ ይጠቃሉ:: ከእነዚህ ውስጥ በየዓመቱ 350 እናቶች በኢትዮጵያ የችግሩ ሰላባ ይሆናሉ::
የፊስቱላ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ወ/ሮ መልኬ መኮንን አንዷ ናቸው:: በምዕራብ ጐጃም ዞን የሰከላ ወረዳ ነዋሪዋ ወ/ሮ መልኬ ሰባት ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ከሁለት እስከ ሦስት ቀን በተራዘመ ምጥ ያለጤና ባለሙያ እገዛ ተገለሰግለዋል:: ስምንተኛ ልጃቸውን ግን ምጣቸው ከበፊቱም በመዘግየቱ ለፊስቱላ ተጋልጠዋል::
እርሳቸው እንደሚሉት ጽንሱ በተራዘመው ምጥ ሆዳቸው ውስጥ እንዳለ ጠፍቷል:: ያንን ጊዜ ሲያስታውሱትም ”በአምስተኛ ቀኔ ፈሳሽ ተከሰተ:: በሰባተኛ ቀኔ ባሕር ዳር ሐምሊን ሆስፒታል ደረስሁ፤ አንድ ወር በነፃ ታክሜ አሁን መዳን ችያለሁ” በማለት ችግሩንና መፍትሄውን ነገሩን::
የ35 ዓመቷ ወ/ሮ ለዚህ ችግር የተጋለጡት ጤና ጣቢያው ከሚኖሩበት ቀዬ መራቁ እና መንገዱ ወጣ ገባ በመሆኑ የእርገዝና ክትትልም ሆነ በሰለጠነ ባለሙያ ታግዘው መገላገል አልቻሉም:: በዚህም ምክንያት አራት ልጆቻቸውን በሞት አጥተዋል:: ”በጤና ጣቢያ መውለድ ጥሩ መሆኑን አሁን ተገንዝቤያለሁ:: ዘንድሮ እንኳን ልጇ እኔም ጠፍቼ ነበር” ሲሉ ነው የተራዘመ ምጥ እናቶችን ለፊስቱላ ከማጋለጥ በዘለለ ጽንሱ እንደሚጠፋ የገለፁት::
ሌላዋ የ35 ዓመቷ የፊስቱላ ተጠቂ ወ/ሮ አበጠር ወንድይፍራው ናቸው:: የደራ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ አበጠር አራት ልጆችን በቤት ውስጥ ተገላግለዋል:: አምስተኛ ልጃቸውን እንደቀደሙ በቤት ሊገላገሉ ቢያሰቡም አልተሳካም:: በተራዘመ ምጥ ልጃቸውን አጥተዋል፤ እርሳቸውም ለፊስቱላ ተጋልጠዋል:: በዚህ ሁኔታ ለስድስት ዓመታት በስቃይ ቆይተዋል:: ችግሩ ሲብስባቸው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ተቋም ቢያመሩም ችግሩ ከተቋሙ በላይ በመሆኑ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ሐምሊን ሆስፒታል ተልከው መዳናቸውን በዕለቱ ተገኝተው አስረድተዋል::
ወ/ሮ አበጠር እርሳቸው ብቻ ድነው አልቀሩም፤ በችግሩ ውስጥ የነበረች እህታቸው እና ጐረቤታቸውን ልከው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል:: እርሳቸው አሁን ሙሉ በሙሉ ጤናቸው መመለሱን በውይይቱ ለተገኘው ተሳታፊ መስከረዋል::
ታዲያ አሁን ላይ በክልሉ የፊስቱላ ተጠቂዎች ወደ ህክምና ማዕከል ለማድረስ ወረዳዎች እና ዞኖች የሰላሙ እጦት ችግር እንደፈጠርባቸው አንስተዋል:: በተለይም አምቡላንስ እና ሌሎች የመጓጓዣ መኪኖች አለመኖር የፊስቱላ ተጠቂዎች ልየታ ቢደረግም ወደማዕከላት ማምጣት አለመቻሉን ከየአካባቢው የመጡ የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል::
ማዕከሉ ዘንድሮ ከ100 ለሚበልጡ የፊስቱላ ተጠቂዎች ህክምና መስጠቱን የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ሐምሊን ፊስቱላ ማዕከል የፊስቱላ መከላከል ባለሙያ አቶ ወርቁ ኪሮስ ናቸው። ባለሙያው እንደሚሉት በየአካባቢው ተደብቀው የሚገኙ የፊስቱላ ተጠቂዎች ወደ ማዕከሉ መጥተው ታክመው እንዲድኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል:: የመጓጓዣ ችግርን በተመለከተም ማዕከላት የፊስቱላ ጠጠቂዎች ቁጥር በዛ ካለ በየአካባቢው ያሉ ባለሙያዎች ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር ወደባሕር ዳር ካመጧቸው ወጫቸው እንደሚሸፈን ተናግረዋል:: ይህ ካልተቻለ ቁጥራቸው በርከት ያለ ከሆነ ካሳወቋቸው እነሱም ሂደው ማምጣት እንደሚችሉ አቶ ወርቁ ተናግረዋል::
በአማራ ክልል ከባሕር ዳር እና ከጎንደር ኒቨርሲቲ ፊስቱላ ማዕከል በተጨማሪ እንጅባራ፣ ደሴ፣ ማርቆስ እና ወረታ የፊስቱላ ተጠቂዎች ማቆያ መኖሩን አቶ ወርቁ ጠቁመዋል:: የማህፀን መውጣትን ጨምሮ ህክምናው በነጻ እንደሚሰጥም አቶ ወርቁ አስገንዝበዋል::
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም