ዘንገና

0
50

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ክረምቱስ እንዴት ነው? ጊዜያችሁን ከጨዋታ ባሻገር በክረምት ትምህርት፣ ስፖርት ስልጠናዎች፣ በንባብ እና በሌሎች ጠቃሚ ነገሮች እያሳለፋችሁ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ልጆች የዘንገና ሐይቅን ታውቁታላችሁ? ስለሐይቁ የተወሰነ መረጃ እናጋረችሁ፡፡

ልጆች፣ የዘንገና ሐይቅ መገኛ በባንጃ ወረዳ በከሳ ቸውሳ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ ከእንጅባራ ከተማ በስድስት ኪሎ ሜትር ርቅት በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ በ430 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር ደግሞ በ127 ኪሎ ሜትር ይርቃል፡፡ የዘንገና ሐይቅ የእንቁላል ቅርጽ አለው፡፡ አጠቃላይ ሥፋቱ 55 ሄክታር ነው፤ ከባሕር ጠለል በላይ ሁለት ሺህ 515 ሜትር ከፍታም አለው።

 

ወደ ሐይቁ በእግር መሔድ የሚፈልጉ ጎብኚዎች በጫካው መሀል እየተዝናኑ እና ንጹህ አየር እየተነፈሱ መጓዝ ይችላሉ። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ጥናት መሠረት ሐይቁ 150 ሜትር ጥልቀት አለው፡፡ ርዝመቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ አንድ ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡ የእንቁላል ቅርጽ ያለው የዘንገና ሐይቅ በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መፈጠሩን ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡

የሐይቁ ውኃ ያረፈው ሰው በራሱ እጅ እንደሠራው ገበቴ ተፈጥሮ ባዘጋጀው ስፍራ ነው፡፡ ውኃውን ከምድር ሆነው ሲያዩት እንደ መስታወት ያንጸባርቃል፡፡ ፀጥ ረጭ ያለ ነው፡፡ አየር ላይ ሆነው ሲመለከቱት አረንጓዴ፣ መሬት ላይ ሲያዩት ደግሞ ሰማያዊ ቀለም አለው፡፡

 

የሐይቁ ቀለም አረንጓዴ እና ሰማያዊ የሆነው በዙሪያው ባሉት እፅዋት ነጸብራቅ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተለያዩ እጽዋት የተከበበ ነው፡፡ ከ75 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች፣ የዱር እንስሳት እና አእዋፍም በዙሪያ ገባው እንደሚገኙም ከባንጃ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ለምሳሌ ጦጣዎች፣ የዱር ቀበሮዎች፣ ጅቦች፣ አሳማዎች፣ አጋዘኖች፣ ቀበሮዎች ወዘተ በሐይቁ ዙሪያ በሚገኙ እፅዋት ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡ ዳክዬ፣ ቁራ፣ ጭልፊት፣ ርግብ፣ ጉጉት እና ሌሎች የአእዋፍ ዝርያዎችም ዘንገና ሐይቅ መኖሪያቸው ነው።

ዘንገና ባለብዙ ጸጋ ነው። እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ፣ አስተማማኝ ሰላም፣ ተስማሚ የአየር ጸባይ እና መሰል ምቹ ሁኔታዎችን የታደለ ነው፡፡ ሐይቁ እምብዛም ያልተጎበኘ እና ያልተጠቀምንበት ግን ማራኪ ሃብታችን ነው፡፡ በሐይቁ ውስጥ ቦርፊሽ ፣ ቲላፒያ እና ባርቤል የተባሉ የዓሣ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡

 

ተረት

እዚሁ ተወኝ

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት መነኩሲት ጎህ ሲቀድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሄዱ ይነሳሉ፡፡ አንድ ዛፍ አጠገብ ሲደርሱ ተንበረከኩና ሁለት እጃቸውን በልመና መልክ ዘርግተው፤ ጸለዩ፡፡

“አምላኬ ሆይ! ድንገት ከወትሮው ፀሎቴ አሳንሼብህ ይሆናል፡፡ ሁሉን የምትሰጥ፤ የነገሩህን የማትረሳ፣ የለመኑህን የማትነሳ፣ ሰማይን ያለ ካስማ ያቆምክ፣ የማያርሱ የማይዘሩ ወፎችን የእለት ጉሮሮ የምትዘጋ፣ ምንም የማይሳንህ አምላክ ሆይ! ካንተ ልግስና አንፃር እጅግ ትንሽ ነገር ነው የምለምንህ፡፡ እባክህ ዕድሜዬን ጨምርልኝ?”

ለካ ይህን ፀሎታቸውን ሲያደርሱ፣ ሁሌ ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቆ የሚያዳምጣቸው አንድ ተንኮለኛ ሰው ኖሯል፡፡

በሚቀጥለው ማለዳ ጎህ በቀደደ ሰዓት ያ ተንኮለኛ ሰው፣ ቀደም ብሎ ዛፍ ላይ ወጥቶ ይጠብቃቸዋል፡፡ እሳቸው እንደልማዳቸው መጥተው ፀሎትና ልመናቸውን አሰሙ፡፡ በመጨረሻም፤ “ዕድሜዬን ጨምርልኝ፣ አደራ!” አሉ፡፡

ይሄኔ፤ ያ የቆሎ ተማሪ፤

“አንቺ መነኩሲት! ምን ያህል ዕድሜ ልጨምርልሽ?” አለ ድምፁን ጎላ አድርጎ፡፡ መነኩሲቷ ደነገጡ፡፡ ፀሎታቸው ተሰማ! ሲያስቡት ሃያም ትንሽ ነው፡፡ አርባም ትንሽ ነው፡፡ መቶም ትንሽ ዕድሜ ነው፡፡ በመጨረሻ እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “አምላኬ ሆይ! አንድ ድሃን ከነጭራሹስ እዚሁ ብትተወኝ (ባልሞት)፣ ምን እጎዳሃለሁ!” አሉ ይባላል፡፡ ምኞታችን እና ፍላጎታችን ሁሌም በልክ እና በቅጥ መሆን እንዳለበት ከተረቱ እንማራለን፡፡

 

ይሞክሩ

  1. ነጭ ተሳፋሪዎች አረንጓዴ አውቶብስ ውስጥ?
  2. የሲሸልስ ዋና ከተማ ማን ትባላለች?
  3. ከውኃ ተፈጥሮ በውኃ የሚጠፋ?

 

 

መልስ

  1. ቃሪያ

2 ቪክቶሪያ

3 ጨው

 

ስም ከመቃብር በላይ ይቆማል፡ መልካም ሥራ መሥራት ሁሌም ስምን ያስጠራል፡፡

ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው፡ አንድ ሥራ ክብደቱ ሚታወቀው ሲይዙት ነው፡፡

ውኃ እድፍን ያጠራል፤ ትምህርት ልብን ያበራል፡ ትምህርት አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here