ዘግናኙ የየካቲት ክስተት

0
185

በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ሀገራቸውን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ወረራ የፈፀመውን የፋሽስት ጣሊያንን ሀይል በሚገባ አንበርክከው ታሪክ የሰሩበት የጥቁር ሕዘብ ድል ነው። ኢትዮጵያ ለጥቁር አፍሪካውያን የነፃነት፣ የአልበገሬነት እና የአሸናፊነት ምልክት፣ ለአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃያላን አስደንጋጭ መልዕክት ያስተላለፈ ደማቅ ታሪክ ነው።
አድዋ በውድ መስዋዕትነት ያስከበረችው ነፃነት በአለም ካርታ ውስጥ ያስገባት፣ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ነፃ ሉአላዊት ሀገር፣ ያውም የሊግ ፍኦ ኔሽንስ አባል ሀገር የሆነችበትን ክብር አጎናፅፏታል። ይሁን እንጂ የፋሽስት ጣሊያንን መንግሥት የምስራቅ አፍሪካ ግዛቱን የማስፋፋት እቅዱን ለማሳካት ኢትዮጵያን ዳግም በመውረር የግዛቱ አካል ለማድረግ ጦርነት ከፍቷል።
ለአርባ አመታት ያህል የአድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል ራሱን ሲያዘጋጅ የቆየው የዱቼ ሙሶሎኒ ፋሽስታዊ አገዛዝ ኢትዮጵያን ዳግም ለመውረር የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራውን ማንኛውንም የጦር መሳሪያ ሁሉ እና በአለማቀፍ የጦር ሕግ የተከለከለን የመርዝ ጋዝ ጭምር ታጥቆ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈተ። ይህ ሉአላዊ በሆነች እና በሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል ሀገር ላይ የተቃጣ ትክክል ያልሆነ የቅኝ ግዛት ፍላጎት ትንኮሳ ነበር።
ኢትዮጵያን በሰሜን ከኤርትራ እና በደቡብ ከጣሊያን ከሱማሌላንድ በመነሳት ከሁለት አቅጣጫ ወረረች። ኢትዮጵያውያን ጦርነቱን ከአድዋው በማይተናነስ ውጊያ ቢዋጉም አድዋን መድገም የማያስችል ሁኔታ ተደቀነበት፣ በጦር ሜዳ ፍልሚያ አልበገር ያሉት ጀግኖች ዳግም ሽንፈት ሊያከናንቡት መሆኑን ሲረዳው ጨካኙ የፋሽስት አገዛዝ የመጨረሻ ያለውን ካርድ መዘዘው። በአለማቀፍ የጦር ሕግ የተከለከለ የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ኢትዮጵያን የግድ እንዲቆጣጠር ከሙሶሊኒ የወጣው ቀጭን ትእዛዝ በጭካኔ ተፈፀመ፣ የመርዝ ጋዙ የኢትዮጵያን ሰራዊት ፈታው። ኢትዮጵያ በጣሊያን ቁጥጥር ስር ገባች፤ እናም የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ አንድ አካል ሆና ተጠቃለለች።
የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ጠቅላይ ግዛት አዲስ አበባ ሆነች። ዋና እንደራሴው ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ በአዲስ አበባ ሆኖ ማስተዳደር ጀመረ። ማርሻሉ በኢትዮጵያ ላይ ከባድ ጥላቻ እና የበቀል ስሜት የተሞላ ስለነበር ፍፁም ጨቋኝ አገዛዝን በመዘርጋት በርካታ ኢሰብአዊ የጦር ወንጀሎችን በንፁሃን ላይ ፈፀመ። በጦርነቱ ወቅት አንድ የቀይ መስቀል ሆስፒታልን በቦምብ ደብድቧል፣ ቁስለኞችን ከሆስፒታል አስወጥቶ ገድሏል፣ በአዲሰ አበባ እና በደብረ ሊባኖስም ንፁሃንን ጨፍጭፏል።
ከሁሉ የሚልቀው ግን ከየካቲት 12 እስከ 15/ 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና አካባቢው በሶስት ቀናት ውስጥ ከ30ሺ በላይ የሚሆን ሕዝብ በግፍ ያለቀበት ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሁሌም ሲታወስ ይኖራል። የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ተብሎ በታሪክ ይዘከራል። መላው ዓለም የፋሽስትን የጭካኔ እና የኢሰብአዊነት ጥግ አይቶበታል። የኢትዮጵያውያን መቼም ለነፃነት አልበገሬነታቸውን ያስመሰከሩበት፣ ጣሊያን “አሳፋሪ” የተባለችበት ይህ ጉልህ የታሪካችን ክፍል የዚህ ሳምንት የታሪክ አምዳችን አብይ ርእሰ ጉዳይ ሆኗል።
ፋሽስት ጣሊያን ያለ የሌለ አቅሙን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ በጨካኝ አምባገነናዊ እንዲሁም ዘረኛ አስተዳደር ሕዝቡን ለከፋ መከራ ዳረገው። በኢትዮጵያውያን ላይ የበቀል ስራውን ጀመረ፤ በየጊዜው በሚፈፅመው ኢሰብአዊ አያያዝ ሕዘቡን በምሬት ለትግል እያነሳሳ መጣ።
በከተሞች ብቻ የተወሰነው የፋሽስቱ አስተዳደር ሕዝቡን ከማስመረሩ የተነሳ ጀግኖቻችን እየጠበቁ ጥቃት ይፈፀሙ ጀመር። ከእነዚህ መካከል ሁለት ቆራጥ ወጣቶች በጨካኙ እንደራሴ ማርሻል ግራዚያኒ ላይ ግድያ ለመፈፀም እንዲያሴሩ ግድ አላቸው። በመሆኑም ማርሻል ግራዚያኒ የጣሊያኑ ንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ሕፃን መወለዱን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ለመደገስ መዘጋጀቱን አስታክከው አላማቸውን ለማሳካት አብርሀም ደቦጭ እና ሞገስ አስግዶም የተባሉ የኤርትራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን በሚስጢር ያዘጋጁትን የእጅ ቦምቦች ይዘው ግራዚያኒ ንግግር እያደረገ ወደ ነበረበት የቤተመንግስቱ አካባቢ በድፍረት በመግባት ግራዚያኒ ላይ ቦምቦቹን በቅርብ ርቀት ሆነው ደጋግመው ወረወሩ። ያልተጠበቀው ፍንዳታ ስነ ስርአቱን ሲያናውጠው ግራዚያኒ ተመትቶ ወደቀ፣ መረጃዎች እንደጠቆሙት ግራዚያኒ ከሁለት መቶ በላይ ቦታዎች ቆስሎ ለጥቂት ከሞት አመለጠ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም። ወጣቶቹ አላማቸውን ፈፅመው በፍጥነት ከግቢው ወጥተው ተሰወሩ። ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳምም ሄደው ተደበቁ።
ለነፍሳቸው የቆረጡት እነዚህ ጀግና ሁለት ወጣቶች ግራዚያኒን ለመግደል ድንገት የፈፀሙት ጥቃት ያስደነገጠው የፋሽስት ሀይል የፈሪ በትሩን በንፁሃን ላይ በበቀል ስሜት አሳረፈ። ወታደሮቹም በስነ ስርአቱ ለመታደም በቤተመንግስቱ ቅጥርም ግቢ በተሰበሰቡት አቅመ ደካማ ንፁሃን ላይ መትረየሶቻቸውን አርከፈከፉ። ወዲያውኑ የንፁሃን አስከሬን ተከመረ። በዚህ ያልረካው ፋሽስት ሌላ ጥፋት አዘዘ። በዚያው እለት አዲስ አበባ ዘግናኝ እልቂት ተጠነሰሰላት።
በወቅቱ የተከሰተውን የግፍ ጥግ ከመሰከሩ በርካታ የአይን እማኞች ምስክርነት ከሰጡ የውጭ ሀገር እና የአገሬው ሰዎች አንዱ ዶ/ር ሌዲስላቭ ሳቫ ወይም ሻስካ የሚባል ሀንጋሪያዊ ይጠቀሳል። ሻስካ እንደሚያስታውሰው ከግድያ ሙከራው በኋላ ወዲያዉኑ የፋሽስት ፓርቲ መሪው ጉይዶ ኮርቴሴ “ጥቁር ለባሽ ኮማንዶውን ወደ ፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት ጠርቶ ተልእኮ ሰጠ፣ ሹማምንቱን ሰብስቦ መከረ፣ እንዲሁም የሰራዊቱ አካላት ትእዛዝ እስኪወርድላቸው ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ አዘዘ። ወዲያውም ወታደሮቹ እስከ አፍንጫ ታጥቀው በሁሉም አቅጣጫ በፍጥነት ተሰማሩ። በከተማው ያለ እያንዳንዱ ሰው ታዳኝ ነበር፣ ነገር ግን የተከሰተው ነገር የከፋ ነበር። እውነታውን እንዳለ ለማስቀመጥ ግድ እንደሚለኝ በየመንገዱ ደም እንደ ጎርፍ ይፈስ ነበር። የአሞራ መንጋ የሚያንዣብብበት፣ የወንዶች፣ የሴቶች እና የሕፃናት አስከሬኖች በየቦታው ወዳድቋል።
“ትልቁ ጭፍጨፋ የጀመረው ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ነበር። በዚያ አሰቃቂ ምሽት ወቅት ኢትዮጵያውያን በታጠቁ ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ኮማንዶዎች በጥብቅ ጥበቃ መኪኖቹ ላይ ይታጎራሉ። ፆታ እና እድሜ ሳይለዩ ፍፁም ያልታጠቁ ጥቁር ህዝቦችን ለመግደል ሽጉጦች፣ የፖሊስ ቆመጦች፣ ጠብመንጃዎች እና ጩቤዎች ጥቅም ላይ ዋሉ። አራጆቹ ያዩትን ማንኛውም ጥቁር ህዝብ ሁሉ በቁጥጥር ስር እየዋለ እና በመኪና ላይ እየተወሰደ ይገደል ጀመር። መኪናው ላይ እንዳለ ወይም በትንሹ ግቢ አቅራቢያ (የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህንፃ ውስጥ) ይገደላሉ፣ አንዳንዴም ጥቁር ለባሾቹ ባገኙት ሁሉ ይገደላል። የኢትዮጵያውያን ቤቶች እየተፈለጉ ሰዎቹን ከውስጥ እንዳሉ ይቃጥላሉ። ቃጠሎውን ለማፋጠን ቤንዚን እና ነዳጅ በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ ውሏል። ሕዝቡን የመረሸኑ ተግባር ሌሊቱን ሙሉ ያለማቋረጥ ተፈፀመ። ነገር ግን ግድያው በጩቤ፣በሳንጃ እና ተጠቂውን አናቱን በቆመጥ በመቀጥቀጥ ተፈፅሟል። መንገዱ በሙሉ በእሳት ተያይዟል። ከቃጠሎው ለማምለጥ ከሞከሩ በመትረየሶች ወይም በሣንጃ እየተወጉ ይገደላሉ። የሚረሸኑ እስረኞችን ይዘው ወደ ትንሹ ግቢ ከመጡት መኪኖች የሚፈሰው ደም በጎዳናዎቹ ላይ ይጎርፋል።
በፍፁም የማልረሳው ሲል ሳቫ ሲያጠቃልል፣ “በዚያው ምሽት የጣሊያን መኮንኖች፣ ሴቶች ብዬ ለመጥራት በሚከብዱኝ፣ ሚስቶቻቸው ታጅበው፣ በቅንጡ መኪኖቻቸው በደም በጨቀየው መንገድ ላይ ሲያልፉ እና ግድያውን እና ቃጠሎውን በደንብ ከሚያሳይ ቦታ ላይ ቆመውን ሲመለከቱ ያየሁትን በፍፁም አልረሳውም።”
በሌላም በኩል በሮበርትኸርበርት እና ዳላስ ሀንሰን የተባሉ አሜሪካዊያን ሚሺነሪዎች ሪፖርት እንዳደረጉት ጅምላ ጭፍጨፋው ከተካሄደ ጥቂት ቆይተው ከተማዋን ሲጎበኙ፣ “ከዚህ በፊት ሰዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች የነበሩበት እጅግ በጣም ሰፊ የሆኑ አካባቢዎች ተቃጥለው ባዶ ሆኖ አገኘን። ከሆስፒታሉ ግድግዳዎች ዙሪያ እንኳ ብዙ ጎጆ ቤቶች የነበሩ ቢሆንም አመዳቸው ቀርቶ አገኘነው። በውድመቱ በጣም ልባችን ተነክቷል፣ በተለይ ቤቶቹ የተቃጠሉት ባለቤቶቻቸው ከውስጥ እያሉ መሆኑን ስንረዳ ሀዘናችን ከበደ” ብለው ነበር።
በዚህ ጊዜ በየጎዳናዎቹ የሚታይ አንድም ኢትዮጵያዊ አልነበረም፣ ነገር ግን በርካታ ጣሊያናውያን ይዘዋወሩ ነበር። አብዛኞቹ ይህን እና ያንን ቦታ አቃጠልኩ ሲሉ እና ብዙ ኢትዮጵያዊያንን መግደላቸውን ይናገሩ ነበር።
ግራዚያኒን የመግደል ሙከራው ጠንሳሽ ይሆናሉ በሚል ንጉሰ ነገስት ሀይለ ስላሴ ውጭ ሀገራት ልከው ያስተማሯቸው ከ120 የሚበልጡ ምሁራንም እየተፈለጉ ተገደሉ። ከእነዚህ መካከል በለንደን እና ፈረንሳይ ሀገራት የተማሩ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። ከአዲስ አበባው ዘግናኝ ጅምላ ጭፍጨፋ በኋላ የግድያ ሙከራውን የፈፀሙት ሁለቱ ወጣቶች ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም አምልጠው ተደብቀው እንደሚገኙ መረጃ በመገኘቱ የፋሽስቱ ነፍሰበላ ቡድን ወደ ደብረ ሊባኖስ ዘመተ። በዚያም አብርሀም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም መረጃው አስቀድሞ ደርሷቸው ስለነበር ከአካባቢው ሸሽተው በገጠር ከሚገኙ አርበኞች ጋር መቀላቀል እንደቻሉ ይነገራል። ይሁን እንጂ የፋሽስቱ ቡድን የገዳሙ መነኮሳት ወጣቶቹን ደብቃችኋል በሚል በአሰቃቂ ሁኔታ በመቶዎቹ ጨፈጨፈ። ሌላ ወንጀል።ሌላ ጥፋት።
ምንም እንኳ የፋሽስት ጣሊያንን ወራሪ ቡድን ሕዝቡን በዚህ መልኩ በማሸበር ፀጥ አድርጌ እገዛዋለሁ በሚል እሳቤ የፈፀመው ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ጭካኔያዊ ድርጊት ውጤቱ የተገላቢጦሽ ነበር። አሰቃቂው ጭፍጨፋ በኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ላይ ጥልቅ የሆነ ተፅእኖ ያደረገ እና የነፃነት ትግሉን በአዲስ ጉልበት አጠናክሮታል። አንድ “ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያ ኒውስ” የተሰኘ ሚዲያ የጅቡቲ ወኪል ከጭፍጨፋው አጭር ጊዜ በኋላ ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያውያን ከአዲስ አበባ አጠቃላይ በሚባል ሁኔታ ለቀው ወጥተው እንደነበር እና በክስተቱ የተነሳ አቢሲኒያውያኑ ከመዋጋት ሌላ ምንም የቀራቸው ነገር እንደሌለው ተገንዝበው ነበር። በመሆኑም በየአካባቢው ካሉ አርበኞች ጋር የሚቀላቀሉ ከጭፍጨፋው ያመለጡ ወጣቶች ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምር ሆኗል። የፋሽስቱ እንዲህ ያለው ግፍ ያንገበገበው ኢትዮጵያዊ ቤት ንብረቱን እየተወ ወደ ጫካው ተመመ።
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here