ዛሬም ጠንቀቅ!

0
28

ኤች አይ ቪ  ከተገኘበት እ.አ.አ 1981   ጀምሮ እስከ 2024 መጨረሻ ወር ድረስ በተደረገ ጥናት 44 ነጥብ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎችን ሕይወት ማሳጣቱን  የዓለም ጤና ድርጅት  መረጃ አመላክቷል:: ከእነዚህም ውስጥ 65 በመቶው  አፍሪካውያን ናቸው:: መረጃው አክሎ እንደጠቆመው እ.አ.አ በ2024 ብቻ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች   ኤች አይ ቪ በደማቸው እንደሚኖር በጥናቱ ተገምቷል፤  ከእነዚህ ውስጥም   630 ሺህ ሰዎች ሕይዎታቸውን አጥተዋል::

ቫይረሱ ከተከሰተበት እ.አ.አ 1981 ጀምሮ  በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም ሀገራት ስርጭቱ እንደቀጠለ መሆኑን ነው መረጃው ያመላከተው። ይህም በሽታው ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና ጉዳይ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል::

ኤች.አይ.ቪ (Human Immuno deficiency Virus) ነጭ የደም ሴሎችን  በማጥቃት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም /ሲዲፎር/ የሚያዳክም ቫይረስ ነው::  ኤድስ  ኤች.አይ.ቪ የሚያደርሰው የመጨረሻ ደረጃ ወይም የበሽታው ስም ነው። ኤች አይ ቪ በደሙ ውስጥ ያለበት ሰው ኤድስ በሽታ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ዓመታት ይወስድበታል:: ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ እስከ አስር ዓመት   ምንም አይነት የሕመም ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ እንደሚችልም መረጃው ይጠቁማል:: ቫይረሱ  ቀስ በቀስም አቅምን በማዳከም ለሌሎች በሽታዎች አጋልጦ ይሰጣል::

የኤች አይ ቪ ምልክቶቹ

የኤች አይ ቪ ምልክቶች በሽታው እንዳለበት ደረጃ ይለያያል::  አንድ ሰው በቫይረሱ ከተያዘ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በሰውነቱ በቀላሉ ይሰራጫል:: ነገር ግን አንዳንዶቹ እስከ መጨረሻው ደረጃ ድረስ ሁኔታቸውን ላያውቁ ይችላሉ::

አንዳንዶች ደግሞ የኢንፍሉዌንዛ  ሕመም ምልክት ማለትም ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ሽፍታ እና  የጉሮሮ መቁሰል ምልክቶች ይታዩባቸዋል::  ቀስ በቀስ በሽታ የመከላከል ሥርዓትን እያዳከመ ሲሄድ የንፍፊት እብጠት፣ ክብደት መቀነስ፣ትኩሳት ፣ ተቅማጥ እና ሳል ይከሰታል::

ኤች አይ ቪ እንዴት ይተላለፋል?

ኤች አይ ቪ በደማቸው ውስጥ በተገኘባቸው ሰዎች ሰውነት ውስጥ በሚኖር ፈሳሽ ይገኛል። ማለትም በደም፣ ከወንድ የዘር ፈሳሽ ፣ ከሴት ብልት በሚወጣ ፈሳሽ እና በጡት ወተት ውስጥ ይገኛል:: ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችለው ደግሞ ልቅ  የግብረ ሥጋ ግንኙነት በማድረግ፣ ስለታማ ነገሮችን በጋራ በመጠቀም (መርፌ፣ ምላጭ፣ ስሪንጅ) እንዲሁም  የጥርስ ቡርሽን በጋራ በመጠቀም ነው::  ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ያለባት እናት በእርግዝናዋ ወራት፣ በምጥ ጊዜ  እንዲሁም ጡት በምታጠባበት ወቅት  ወደ  ልጅ ልታስተላልፍ ትችላለች:: ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ያረጋገጡ  እናቶች በሕክምና በመታገዝ መድኃኒትን በሚገባ በመውሰዳቸው ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ  ጤናማ ልጆችን መውለድ እንደሚችሉ መረጃው አመላክቷል::

የማይተላለፍባቸው መንገዶች

በሳል፣ በጋራ በመመገብ፣ በመሳሳም፣ በመጨባበጥ፣ በመተቃቀፍ፣ በማስነጠስ፣ የመመገቢያ እና የመጠጫ ቁሳቁሶችን በጋራ በመጠቀም፣ አልባሳትን አብሮ በመጋራት(አንሶላ እና ብርድልብስ)፣መጸዳጃ  እና  መታጠቢያ ክፍሎችን በጋራ መጠቀም እና ከሰው ጋር በመቀራረብ ቫይረሱ  አይተላለፍም።

ኤች አይቪ በደም ውስጥ እንዳለ የሚታወቀው በጤና ተቋማት በሚደረግ የደም ምርመራ ብቻ ነው:: በመሆኑም አንድ ሰው ለቫይረሱ እንደተጋለጠ ስጋት ካደረበት ከሦስት ወራት በኋላ የደም ናሙና በማድረግ ማረጋጋጥ ይችላል:: አንዳንዴ ግን ከሦስት ወራት በኋላ እንደገና ምርመራ እንዲያደርግ ሊጠየቁ ይችላል::

የኤች አይ ቪ መከላከያ መንገዶች

ኤች አይ ቪ እንዳይተላለፍ መከላከል የሚቻለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ጥንቃቄ የተሞላበት ሲሆን ነው። ኮንዶምን በተገቢው መንገድ መጠቀምም ከቫይረሱ  ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአባላዘር በሽታዎች ይታደጋል:: እንዲሁም አንድ ለአንድ መወሰን እና መታቀብም በቫይረሱ እንዳይያዙ ያደርጋል::

 

ሕክምና

ለኤች አይ ቪ እስካሁን  መድኃኒት እንዳልተገኘለት የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አሳውቋል:: ይሁንና ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ እንዳይባዛ በሚያደርጉ ፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒቶች ይታከማል። መድኃኒቱ በሽታ የመከላከል ሥርዓት እንዲጠናከርም ያስችላል::  ይህም ሌሎች በሽታዎችን ለመቋቋም ይረዳል:: ውጤታማ የፀረ ኤች አይቪ ሕክምና (ART) አሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ዕድሜያቸው እንዲረዝም ያደርጋል፤ ቫይረሱ ከአንዱ ወደ አንዱ የመተላለፍ መጠኑንም እንዲቀንስ ያደርጋል።

በአማራ ክልል ያለውን የኤች አይ ቪ ሁኔታን በተመለከተም  በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ የማሕበረሰብ ንቅናቄ ቡድን አስተባባሪ አቶ በቃሉ ዳኜ እንደገለጹት በክልሉ ያለው የቫይረሱ ስርጭት ከቦታ ቦታ ጉራማይሌ ነው:: በተለያዩ አካባቢዎች  ከአንድ  ነጥብ አንድ በመቶ እስከ 32 በመቶ ስርጭት እንዳለው ነው የገለጹት::  አሁን ባለው ሁኔታ በክልሉ በተደረገ ጥናት ከአንድ ሺህ ሰው አስር አንዱ ኤች አይ ቪ በደሙ ይኖርበታል ተብሎ ይታሰባል:: በዚህ መሠረት በክልሉ  173 ሺህ ሰዎች ቫይረሱ  በደማቸው አለባቸው ተብሎ እንደ ሚገመት የጠቆሙት አስተባባሪው 162ሺህ 159 ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው መገኘቱ በሕክምና ተረጋግጦ የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት እንደጀመሩ ተናግረዋል::

በአሁን ወቅት የኤች አይቪ ስርጭት ጨምሯል ወይስ አልጨመረም የሚለው በጥናት መረጋገጥ  እንዳለበት አቶ በቃሉ አስገንዝበዋል::

እ.አ.አ በ2030 ከኤች አይቪ ነጻ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር በማሰብ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው አቶ በቃሉ ያስረዱት:: በፊት ሁሉንም ማሕበረሰብ ለመድረስ ጥረት ይደረግ እንደ ነበር ያወሱት ኃላፊው፤ አሁን ግን ለበሽታው ተጋላጭ የተባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተለይተው በትኩረት የግንዛቤ እና የክህሎት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ነው የተናገሩት::

በክልሉ ለቫይረሱ ተጋላጭ የተባሉ 12 የማሕብረሰብ ክፍሎች ተለይተዋል:: እነሱም ሴተኛ አዳሪዎች፣ ታራሚዎች፣ አደንዛዥ ዕጽ በጋራ  ተጠቃሚዎች ፣ አፍላ ወጣቶች፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚሠሩ የቀን ሠራተኞች ፣የትዳር አጋሮቻቸውን በሞት ያጡ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፀጥታ ዘርፍ ላይ ያሉ፣ አካል ጉዳተኞች እና ጎዳና ተዳዳሪዎች ናቸው:: አሁን ባለው መረጃ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ላይ ስርጭቱ ከፍ ብሎ እንደሚገኝም ነው የገለጹት::

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በክልሉ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጨባቸው 84 ወረዳዎች ተለይተዋል:: በተለይም በስምንቱ የከተማ አስተዳደሮች ማለትም  በጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሐን፣ ደብረታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ እና ኮምቦልቻ ላይ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ በመረጋገጡ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ  ነው::  በእነዚህ አካባቢዎች የግንዛቤ የመፍጠር እና ማስረጽ እና በኤች አይቪ ዙሪያ ዕውቀት እና ክሎታቸውን እንዲያሳድጉ ተደርጓል::  ራሳቸውን እንዲያውቁ የደም ምርመራ እንዲያደርጉ እና ቫይረሱ በደማቸው  መኖሩ ከተረጋገጠ  ደግሞ የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት እንዲወስዱ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ::

ሕብረተሰቡ ስለበሽታው ባለው የክህሎት ክፍተት ፣ ኮንዶምን በአግባቡ ባለመጠቀም  እና ከእድሜ ቀድሞ ወሲብ መጀመር በሽታው በነዚህ ቦታዎች ሊስፋፋ ማስቻሉን የቡድን አስተባባሪው ጠቁመዋል::

የኮንዶም እጥረት መኖሩን የጠቆሙት አቶ በቃሉ እጥረቱ የተከሰተው ከፍላጎት አንጻር እና ከአቅርቦት ችግር መሆኑንም ጠቁመዋል::

የዘንድሮው የዓለም የኤድስ ቀንም “ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስን ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል:: በዚህ መሪ ቃል ሊከበር የተወሰነው አብዛኛውን ጊዜ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል የሚውለው ገንዘብ የሚገኘው ከለጋሽ ድርጅቶች ነበር:: ሆኖም አሁን ላይ  ለጋሽ ድርጅቶች ሥራቸውን በማቆማቸው በሽታውን ለመከላከል በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ተግዳሮቶች ተፈጥረዋል:: በመሆኑም  እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ በሽታውን መከላከል እንደሚገባ አጽንኦት ለመስጠት በማለም ነው:: በአሁኑ ጊዜ የመከላከል ሥራው በመንግሥት በጀት እና ከማሕበረሰቡ በሚሰበሰብ (AIDS FUND) እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል::

በክልሉ በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ እንዳለ የጠቆሙት አስተባባሪው እያንዳንዱ ግለሰብ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር ራሱን ከኤች አይቪ  እንዲጠብቅ ምክር ለግሰዋል:: የዓለም የኤች አይቪ ኤድስ ቀን በዓለም ለ38ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ37ኛ ጊዜ ሕዳር 22/2018 ዓ.ም እተከበረ ነው::

ጤና አዳም

ኤች አይ ቪ በደማቸው መኖሩ በጤና ተቋማት በምርመራ ያረጋገጡ ነፍሰ ጡሮች በተቻለ ፍጥነት የፀረ ኤች አይ ቨ (ART) መድኃኒት መውሰድ አለባቸው። ይህም የእናትን ጤና ይጠብቃል:: እንዲሁም ልጅ ከመወለዱ በፊት ኤች አይ ቪ ወደ ፅንሱ እንዳይተላለፍ  ይረዳል::

ኤ አር ቲ (ART) በየቀኑ መወሰድ አለበት:: ምክንያቱም ኤ አር ቲ (ART) በሰው አካል ውስጥ ያለውን  የቫይረስ  መጠን ይቀንሳል:: ይህም ሰዎች ሙሉ እና ጤናማ ሕይወት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል::

ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here