ዓለምነሽ ፈንታሁን በ2017 የትምህርት ዘመን የሰባተኛ ክፍል ትምህርቷን 94 በመቶ አማካይ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ስምንተኛ ክፍል ተዘዋውራለች:: በ2018 የትምህርት ዘመን ደግሞ የስምንተኛ ክፍል ውጤቷ ከሰባተኛ ክፍል የበለጠ ለማስመዝገብ አቅዳለች:: ይህንንም ዕውን ለማድረግ የክረምቱን የእረፍት ጊዜያት በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲ ተመላሽ ወጣቶች በባሕር ዳር ከተማ በአጼ ሰርጸ ድንግል አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየሰጡት ያለውን የማጠናከሪያ ትምህርት እየተከታተለች ትገኛለች::
የማጠናከሪያ ትምህርት ለመከታተል የወሰነችው የትምህርት ሥርዓቱ መቀየሩን ተከትሎ የትምህርት ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት ይዘቶችን ቀድሞ ለመቃኘት እንደሆነ ተናግራለች:: በተጨማሪም በ2018 የትምህርት ዘመን የስምንተኛ ክፍል ክልል ዓቀፍ ፈተና ተፈታኝ በመሆኗ ቀድሞ በመዘጋጀት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ነው::
ዓለምነሽ የስድስተኛ ክፍል ፈተናን በወሰደችበት ዓመት ቀድማ በበጎ ፈቃድ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት መከታተሏ ለተሻለ ውጤት እንዳበቃት ታስታውሳለች:: ውጤቱ በዚህ ዓመትም የክረምት ወቅት የእረፍት ጊዜዋን ትምህርት ላይ እንድታሳልፍ እንዳነሳሳት ገልጻለች::
በጎ ፈቃደኛ የዩኒቨርሲቲ ተመላሽ ወጣቶች በተማሪዎች ዘንድ ከባድ ናቸው ተብለው የሚፈረጁ የትምህርት አይነቶችን ለይተው እየሰጡ መሆናቸው በሁሉም የትምህርት አይነቶች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያግዝ ዓለምነሽ ተናግራለች:: እሷም ከሌሎች የትምህርት አይነቶች በተለየ ደክም የምትልባቸው (ጀኔራል ሳይንስ፣ ማትስ እና እንግሊዝኛ) የትምህርት አይነቶችን እየተከታተለች ትገኛለች:: አሁንም የተማሪዎችን ፍላጎት መሠረት አድርገው ሌሎች የትምህርት አይነቶችን ለመጀመር እንደነገሯቸው ገልጻልናለች::
”ትምህርቱ በነጻነት እየተሰጠ መሆኑም የእረፍት ጊዜያችንን ይበልጥ እንድንወደው አድርጎናል:: ትምህርቱን የሚሰጡን በዕድሜ ከተማሪዎች ብዙም የማይራራቁ መሆናቸው ደግሞ ሁሉም ያልገባውን በነጻነት ሳይሸማቀቅ እየጠየቀ የንግግር ክህሎቱንም እያሳደገ ነው” በማለት የመማር ማስተማሩ ሂደት ውጤታማ እንደሆነ ታምናለች::
‘‘ጊዜው የውድድር ነው” የምትለው ዓለምነሽ፣ እያንዳንዱን ትርፍ ጊዜ ራስን በሚያበቁ ሥራዎች ማሳለፍ እንደሚገባ አሳስባለች:: ታዳጊዎች የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች መሆናቸውን ከወዲሁ በመረዳት ራሳቸውን በዕውቀት እንዲያበቁ ጠቁማለች:: ወላጆችም የልጆቻቸውን ውሎ በአንክሮ መከታተል እንደሚኖርባቸው አሳስባለች:: ሁሉም ተማሪዎች ቀሪ ጊዜያትን ይዘቶችን ቀድሞ ለመቃኘት እንዲያውሉ፣ በአዲሱ የትምህርት ዘመንም ማሳካት የሚፈልጉትን ውጤት እንዲያቅዱ መክራለች::
ሚኪያስ ታዘባቸው ሌላው በአጼ ሰርጸ ድንግል አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተሰጠ ያለውን የማጠናከሪያ ትምህርት እየተከታተለ ያገኘነው ታዳጊ ነው:: ባለፈው የትምህርት ዘመን የክረምት ወቅት የማጠናከሪያ ትምህርት እንዳልተከታተለ የሚናገረው ታዳጊው፣ ይህም በሰባተኛ ክፍል የሚጠብቀውን ውጤት እንዳያሳካ እንዳደረገው በልበ ሙሉነት ገልቷል::
ታዳጊው በአዲሱ የትምህርት ዓመት የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን ይወስዳል:: ከ90 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገብንም ግቡ አድርጓል:: ለዚህም በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እየተሰጠ ያለውን የማጠናከሪያ ትምህርት በንቃት ከመከታተል ጀምሮ ከትምህርት ውጪ የሚሆንባቸውን ሰዓታት አጋዠ መጻሕፍትን በማንበብ እና የፈጠራ ክህሎቱን በሚያዳብሩ ሥራዎች እንደሚያሳልፍ ተናግሯል::
ሚኪያስ የማጠናከሪያ ትምህርቱን ፋይዳ የሚያስረዳው “የአዲሱ ዓመት ትምህርት እንግዳ እንዳይሆንብን ቀድመን እንድንረዳው የሚያደርግ ነው” በማለት ነው:: በተጨማሪም በጀኔራል ሳይንስ የትምህርት አይነት ዝቅተኛ ውጤት እንደነበረው የሚናገረው ሚኪያስ፣ በበጎ ፈቃደኞች እየተሰጠ ባለው ትምህርት ይዘቱን እንደወደደው አረጋግጧል::
በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችም የእረፍት ጊዜያቸውን ባልባሌ ነገር ታጥረው ከማሳለፍ ወጥተው ለቀጣይ የትምህርት ዘመን ውጤታቸውን በሚያሻሽሉ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ራሱን በተሞክሮነት በመጥቀስ አሳስቧል::
ተማሪዎች በየዓመቱ የሚሰጠውን ትምህርት በወርሀ ሰኔ ካጠናቀቁ በኋላ ከትምህርት ውጪ የሚሆኑባቸውን ከሁለት ወራት ያላነሱ ጊዜያትን በተለያዩ የሥራ እና የመዝናኛ ሥራዎች እንዲያሳልፉ ይጠበቃል:: ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመለሱ ተማሪዎች ደግሞ ለታዲጊዎች የሚበጀውን መንገድ የማሳየት ኃላፊነት አለባቸው:: ይህም በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል::
ግሩም ሙሉቀን በእረፍት ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ ተሠማርቷል:: የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪግ ተማሪው ግሩም፣ ከሌሎች በጎ ፈቃደኞች ጋር ሆኖ መማር ማስተማር እያከናወነ የሚገኘው በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው አጼ ሰርጸ ድንግል ትምህርት ቤት ነው::
ግሩም በበጎ ፈቃድ ተግባር ለምን እንደተሠማራ ሲናገር፤ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በቡድን የማጥናት ልምድ ነበረው። ይህም ልምዱ የተሻለ የትምህርት እንቅስቃሴን እንዲያሳልፍ ረድቶታል:: ለራሱ የጠቀመውን ይህን ተሞክሮ ለሌሎች ተማሪዎች ለማጋራት፣ ከትምህርት ውጪ የሆኑ ልጆች ትርፍ ጊዜያቸውን ለማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያውሉ ለማንቃት፣ በቀጣይ የትምህርት ዘመንም የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከወዲሁ አቅደው እንዲነሱ ለማድረግ ነው::
የሂሳብ እና ፊዚክስ የትምህርት አይነቶችን በበጎ ፈቃድ የሚያስተምረው ግሩም የነገዋ ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸውን ሳይንቲስቶች፣ መሀንዲሶች፣ የሕክምና ዶክተሮች፣ መምህራንን… ለማፍራት ዛሬ ላይ መሠረትን መጣል ይገባል ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል:: ለዚህም ተማሪዎችን ትምህርትን እንዲወዱ ማድረግ፣ በማጠናከሪያ ትምህርት ማገዝ እና ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ ማድረግ ይገባል ብሎ ያምናል:: እሱም የዚህ አካል በመሆኑ ደስተኛ እንደሆነ ተናግሯል:: ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ በሚሆኑባቸው ወቅቶች በጓደኞቻቸው ተጽእኖም ይሁን በሌላ ምክንያት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመሩ መከታተል እንደሚገባም ግሩም ለወላጆች አስገንዝቧል::
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ክቤ የኋላ የቋንቋ ትምህርት የምትሰጥ በጎ ፈቃደኛ ናት:: የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ከማድረግም በላይ ለህሊና እርካታ ልዩ ትርጉም ይሰጣል::ሕጻናት ላይ መሥራት ደግሞ ነገን መሥራት በመሆኑ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው ትላለች::
”ሕጻናት የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢ በመሆናቸው ከወዲሁ ንቁ እና ብቁ እንዲሆኑ ማገዝ ይገባል። ሕጻናትን ማጎልበት እና የዛሬ ሐሳባቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ መርዳት ነገን የተሻለ ለማድረግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። የእኛም ዋነኛ ዓላማ ተማሪዎች የቀጣዩን የትምህርት ይዘት ቀድሞ በማስተማወቅ የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዲኖራቸው ማገዝ ነው። በተጨማሪም የአሁኑ ትውልድ ለትምህርት ያለው አተያይ እጅግ የወረደ ነው። ራስን በትምህርት ያላበቃ ትውልድ የትም እንደማይደርስ ሁሉም ማወቅ ይኖርበታል! ይህንን የልተገባ አካሄድ ማረም የሚቻለው ደግሞ ወጣቱ ተባብሮ በጋራ መሥራት ሲችል ነው” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
ወጣቱ ትውልድ ሕጻናትን ያነሳል፤ አረጋውያንን ይደግፋል። ታዳጊዎች ላይ መሥራት የነገን መንገድ መጥረግ ነው። ስለዚህ ሕጻናት ነገን አሻግረው እንዲመለከቱ በማድረግ የተሻለ ነገን ለመፍጠር የዛሬው የወጣቱ የበጎ ፈቃድ ሥራ የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ከቤ ጠቁማለች።
ወጣቷ እንደምትለው የትምህርት ሥርዓቱ ከተቀየረ ገና ከሁለት ዓመት ያልተሻገረ በመሆኑ ተማሪዎች ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል ሲሸጋገሩ የትምህርቱ ይዘት ምን አይነት ይሆን ብለው እንዳይጨነቁ ቀድሞ ማሳወቅ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩት ዜጎች ሌላኛው ዓላማቸው ነው። የተማሪዎች ፍላጎትም ከፍተኛ ሆኖ እንዳገኙት ተናግራለች። በአሁኑ ወቅት የትምህርት ዓመቱን ይዘት ቀድመው በመረዳታቸው ዋናው የትምህርት ሥራ የሚከፈትበትን ወቅት ጓጉተው እንዲጠብቁ እንደሚያደርጋቸው ታምናለች። በተጨማሪም ነገ ላይ በትምህርት አጀማመራቸው እና አቀባበላቸው ላይ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን መደናገር እና የትምህርት አቀባበል ተጽእኖ በእጅጉ እንደሚቀንስ ይታመናል።
”የማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎች ነገ ላይ መሠረት እንዲጥሉ የሚያደርግ መግቢያ ነው” የምትለው ክቤ፤ በዚህ እሳቤ ሁሉም ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መውሰድ እንደሚገባቸው አስገንዝባለች። ለዚህ ደግሞ ወላጆች ትልቁን ኃላፊነት መወጣት እንደሚኖርባቸው ታምናለች። ልጆች በአዲሱ የትምህርት ዓመት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከተፈለገ አሁንም ቀሪ ጊዜያትን ትምህርታቸውን በሚያግዙ ሥራዎች ላይ እንዲያሳልፉ መቀስቀስ እንደሚገባ ጠቁማለች። በትምህርት ዓለም ውስጥ ሁለት ሰዓት ልዩ ትርጉም ስላለው አሁንም ቀሪዎቹን ጊዜያት ከአልባሌ ቦታዎች ርቆ ትምህርት ቤት ማሳለፍ ለቀጣይ የትምህርት መነቃቃት እንደሚያግዝም ከቤ አስገንዝባለች።
ግዕዝ በአማርኛ
- ውእቱ – እርሱ
- ይኢቲ – እርሷ
- ውእቶሙ – እነርሱ(ለወንዶች)
- ውእቶን – እነርሱ(ለሴቶች)
- አንተ- አንተ
- አንቲ – አንቺ
- አንትሙ – እናንተ(ለወንዶች)
- አንትን – እናንተ(ለሴቶች)
- አነ – እኔ
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም