“ዝምተኛዉ ገዳይ”

0
169

በአሜሪካ ማዕከላዊ እና ምሥራቃዊ ግዛቶች በሚገኙ ከተሞች  በአስር ዓመታት ውስጥ ያልተከሰተ ከፍተኛ የሙቀት መጠን መመዝገቡን እና ሁነቱ ተባብሶ ሞትን ወደ ማስከተል ሊሸጋገር እንደሚችል ባለሙያዎች ማስጠንቀቃቸውን ኤን ዲቲቪ ድረ ገጽ   አስነብቧል፡፡

የሀገሪቱ ብሔራዊ የአየር ትንበያ አገልግሎት እንዳስታወቀው የከፋው የአየር ሁኔታ በእጅጉ ወበቅ በማስከተል በተለያዩ ከተሞች 80 ሚሊዬን በሚሆኑ ኗሪዎች ላይ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ኗሪዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፤ ባለሙያዎች፡፡  ኗሪዎች  በቂ  ፈሳሽ መጠጣት እና ቀዝቀዝ የሚያደርጉ አማራጮችን ማመቻቸት እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል፤  ባለሙያዎች፡፡

የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዋ ክሪስቲ ኢቢ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የአየር ሁኔታን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት ላይ ሙቀቱ እየጨመረ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው አፅንኦት ሰጥተው የገለጹት፡፡

በአሜሪካ በርካታ ከተሞች የከፋ የሙቀት መጠን እየገጠማቸው መሆኑን ያአብራሩት ባለሙያዎቹ ሙቀቱን “ዝምተኛው ገዳይ” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

የከፋው ሙቀት በአሜሪካ ከኦሃዮ እስከ ሜይን ያሉትን ቦስተን፣ ክሊቭላንድ፣ ቡፋሎ እና የካሪቡ አካባቢዎችን እየጐዳ ነው፡፡ የተራዘመው ሙቀት በቀጣዮቹ ጥቂት ሣምንታትም በመካከለኛው ምዕራብ፣ ሰሜን ምሥራቅ እና በመካከለኛ የአትላንቲክ ክልሎች እንደሚቀጥል ነው ባለሙያዎቹ የጠቆሙት፡፡

የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ትንበያ አገልግሎት ባወጣው ማሳሰቢያ የኦሃዮ ሸለቆ እና ሰሜን ምሥራቅ ባለፈው ሳምንት በሙቀት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም የአካል እብጠት እና  ሞት  መድረሱን  ባለሙያዎች አረጋግጠዋል፡፡

ሰኔ 17/2024 እ.አ.አ ቺካጐ 36 ሴንቲ ግሬድ የተለካ ከፍተኛ መጠን ተመዝግቦበታል፡፡

ከቺካጐ በተጨማሪ ኒውዮርክ፣ ፊላደልፊያ እና ዋሽንግተን ከፍተኛ ሙቀት ያጋጠማቸው መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

በ2023 እ.አ.አ 2 ሺህ 300 ሰዎች በእጅጉ በጨመረው የአየር ሙቀት ህይወታቸው ማለፉን እና በያዝነው በ2024 ከዚህ የበለጠ የሟቾች ቁጥር ሊመዘገብ እንደሚችል ባለሙያዎች ጠቁመዋል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here