ከዝቅተኛ ንግድ ጀምረው በሪል ስቴት ዘርፍ ላይ የተሠማሩትን የአቶ በሱፍቃድ ተስፋዬ የህይዎት ጉዞ እና የንግድ አጀማመር እንዲሁም በሪል ስቴት ዘርፉ የገጠማቸውን ፈተና በክፍል አንድ አስቃኝተናችኋል:: በዚህ የመጨረሻው ክፍል የውጪ ሀገር ተሞክሯቸውን፣ የወደፊት እቅዳቻን እና ሌሎች ጠቃሚ ሀሳቦችን አካተናል:: መልካም ንባብ::
የሀገራችንን የሪል ስቴት ዘርፍ እንዴት ያዩታል?
አሁን ያለው የእኛ ሀገር የሪል ስቴት አሠራር ከሌሎች ይለያል:: ለረጅም ጊዜ ስንጠይቅ የነበረው የሪል ስቴት አዋጁ በቅርብ ጊዜ ይጸድቃል ብለን እንጠብቃለን:: መመሪያውን አይተነዋል መጽደቅ ነው የሚቀረው:: መመሪያ ባለመኖሩ ብዙ የህብረተሰባችን ክፍል ሲበዘበዝ ኖሯል:: ብዙ ሰዎች ቤት የማግኘት ፍላጎት ስላላቸው ሪል ስቴት ድርጅት ነን በሚሉ ተቋማት ገንዘባቸውን ተበልተዋል:: ሪል ስቴት ነን በማለት ገንዘብ ሰብስበው የሚጠፉ አካላት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም:: በጥቂት ዓመታት እናደርሳለን ብለው ቃላቸውን ያልጠበቁ ሪል ስቴቶችም ቁጥራቸው ብዙ ነው:: መንግሥትም ማግኘት ያለበትን ድርሻ እያገኘ አይደለም::
አዲሱ መመሪያ ማንም ተነስቶ ገንዘብ ሰብስቦ እንዳይሰወር ያደርጋል:: ሕጋዊ እውቅና ያገኘ ድርጅትም የሚሰበስበውን ገንዘብ በዝግ አካውንት (ደብተር) እንዲያስቀምጥ ያስገድዳል:: ይሄም ገንዘብን ይዞ ከመሰወር ያድናል:: አሁን ላይ ሪል ስቴት 300 እና 400 በመቶ የሚተረፍበት ሀገር ላይ ነው ያለነው:: የእኛ ድርጅት ግን ከአንድ ቤት 15 በመቶ ትርፍ ብቻ እናስባለን::
ብዙ ሪል ስቴት ነን የሚሉ እናለማለን በሚል ከሕዝቡ ገንዘብ እየሰበሰቡ ተሰውረዋል:: ይህ ጉዳይ ወደፊት ይደገማል የሚል እሳቤ የለኝም:: መንግሥትም አቋም በመያዝ የሚያለማውን እና የሚያጭበረብረውን በመለየት ወደ እርምጃ የገባበት ሁኔታ አለ:: በዚሁ አቋም ቢቀጥል እና የወጣውን መመሪያ ወደ ተግባር ቢቀይር፤ ሕዝቡ ጥሮ ግሮ ያገኘውን ገንዘብ እንዳይበላ ያደርጋል የሚል አስተያየት አለኝ::
ማይክሮ ፋይናንስ አቋቁማችኋል፤ ፋይዳው ምንድን ነው?
የእኛ ሀገር የባንክ አሠራር ትንሽ ወጣ ያለ ነው:: ከባንክ ብድር ጋር ተያይዞ ችግር ስለገጠመን የራሳችንን ማይክሮ ባንክ ለማቋቋም ተገደናል:: ያቋቋምነው ባንክ አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ይባላል:: ይህንን ማይክሮ ፋይናንስ ወደ ባንክ ለማሳደግ ጠንክረን እየሠራን ነው ያለነው:: ህብረተሰቡ በቻለው አቅሙ በአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ እየቆጠበ የቤት ባለቤት እንዲሆን ሪል ስቴታችን በጋራ እየሠራ ይገኛል:: ለቤት ገንቢዎች የብድር አገልግሎት ማመቻቸት የአኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ ዓላማ ነው::
የመካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማካተት ምን እየሠራችሁ ነው?
ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ከፍል የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሠራን ነው:: ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በተለይም የመንግሥት ሠራተኞችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ሪል ስቴታችን ፓኬጅ አካቷል:: በዚህም መሠረት አረርቲ ከተማ ለይ የግንባታ ወጪን እና የካሳ ክፍያን ብቻ ታሳቢ በማድረግ ያለምንም ትርፍ ለ34 የመንግሥት ሠራተኞች 120 ካሬ ቤት እየገነባን ነው:: ቀስ በቀስ በሁሉም የከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት ሠራተኞች በደሞዛቸው ቤት የሚገነቡበትን እድል እንዲያገኙ እቅድ ይዘናል::
አሁን ባለው የሀገራቸን ሁኔታ አንድ አፓርታማ እስከ 11 ሚሊየን ይሸጣል፤ እኛ ደግሞ በሦስት ሚሊየን አካባቢ ነው የምናስረክበው፤ ከዚህ ውስጥ ከአጠቃላይ አራት በመቶውን ለመንግሥት ሠራተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰባችን ክፍሎች ያለምንም ትርፍ ድርሻ እንሰጣለን:: በዚህ መሠረት እንደየ አቅሙ ከ50 ካሬ ጀምሮ ማኅበረሰቡ የቤት ባለቤት መሆን ይችላል:: ይህም ደግሞ ከማይክሮ ፋይናንስ ጋር የረጂም ጊዜ ብድር በማመቻቸት የሚፈጸም ነው::
ከውጪ ሀገራት የወሰዳችሁት ተሞክሮ አለ?
የእኛ ሪል ስቴት በተለያዩ የዓለም አካባበቢዎች የሚሠሩ ሪል ስቴቶችን ተሞክሮ እንደ አርአያ የወሰደ ነው:: ለምሳሌ ደንበኛው፣ የእኛ ሪል ስቴት እና ባንክ በአንድ ላይ ነው ገንዘብ የምንቆጥበው፤ እኛ ገንዘብ አንሰበስብም፤ ይህም ለደንበኛው ደህንነት ሲባል ነው:: ይህን ልመድ የወሰድነው ከዱባይ ሪል ስቴቶች ነው:: ከዚህ ባሻገር የግል አሰልጣኞች አሉን፤ ሁሉንም ሠራተኞቻችንን ለሁለት ወራት ያክል ስለ ሪል ስቴት ዘርፍ ጥልቅ ስልጠና እንዲያገኙ አድርገናል::
በውጭ ሀገራት በተለይ ቻይና፣ ዱባይ እና ባንኮክ የሪል ስቴት አሠራር ምን ይመስላል የሚለውን ወጣ ብለን በተደጋጋሚ አጥንተናል:: ስለዚህ የእኛ ሪል ስቴት በውጭ ሀገራት ያሉትን ተሞክሮ ተግባራዊ ያደረገ ነው:: ይህ ደግሞ በዋናነት ለደንበኞች ደህንነት እና ጥቅም ሲባል የተደረገ ነው:: በተጠቀሱት እና በሌሎች ሀገራት ያሉ የዲያስፖራ ደንበኞቻችን ጋር ውይይት እናደርጋለን፤ ትልቅ ድጋፍም አድርገውልናል::
አረርቲ ከተማ ላይ ብቻ ከ117 በላይ የዲያስፖራ ደንበኞች አሉን:: እነሱ በውጪ ሀገር የሚያውቁትን የሪል ስቴት ተሞክሮ እንዲያጋሩን እና እንዲያማክሩን እድሉን እንሰጣቸዋለን:: ይህም ጥሩ ውጤት አምጥቶልናል::
በቀጣይ እቅዳችሁ ምንድን ነው?
በቀጣይ በባሕር ዳር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን፣ ቡልጋ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት፣ አርባ ምንጭ እና ሌሎች በክልላችን እና ከክልላችን ውጪ ባሉ የሀገራችን ክፍሎች በ15 በመቶ ትርፍ ብቻ ሕዝባችንን የቤት ባለቤት ለማድረግ እየሠራን ነው:: ለዚህ ደግሞ በሕግ፣ በምህንድስና፣ በፋይናንስ እና ሌሎች መስኮች በቂ የሆነ ቋሚ የሰው ኃይል አለን:: ከዚህ ባሻገር በጊዜያዊነት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንቀጥራለን:: ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው አካባቢዎች መንግሥት ፈቃድ የሚሰጠን ከሆነ ቀጥታ ወደ ሥራ ለመግባት በእኛ በኩል ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅተን ጨርሰናል::
በአረርቲ ከተማ ብቻ በ23 ሄክታር መሬት ላይ ከ1100 በላይ ቤቶች ለመገንባት ታስቦ ከ500 በላይ ቤቶች ወደ ማለቅ ደረጃ ደርሰዋል:: የሚገነባው መንደር የራሱ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ የሃይማኖት ማምለኪያ፣ ሱቆች፣ መናፈሻ፣ እንዲሁም የመጠጥ ውኃ አገልግሎት ያለው ነው- ይህም ማኅበረሰቡ በተሻለ ሁኔታ የሚኖርበት አካባቢን የሚፈጥር ነው::
አዲስ አበባ ላይ ሁለት የግንባታ ቦታ አሉን:: እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ውስጥ ቦታ ማግኘት ከባድ ነው:: በመሆኑም አንድ ሺህ አራት መቶ ካሬ ሜትር ላይ አፓርታማ ለመገንባት ዝግጅት አጠናቀናል:: በሌሎች አካባቢዎች ለመንግሥት የማልማት ጥያቄዎቻችንን አቅርበን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው::
ደብረ ብርሃን ትልቅ ሆቴል ለመስራት ቦታ ተረክበናል:: በማይክሮ ፋይናንሱም ጠንክሮ በመሥራት ወደ ባንክ ለማሳደግ እየሠራን ነው:: እንዲሁም በአስመጪ እና ላኪነት ዘርፉም ለመግባት እንቅስቃሴ ጀምረናል:: በክልላችን ያለው የሰላም ሁኔታ ለጊዜው እንቅፋት ሆኖብናል::
ሪል ስቴታችሁን እንዴት ታስተዋውቃላችሁ?
ራሳችንን ለማስተዋወቅ የተለያዩ መገናኛዎችን እንጠቀማለን:: ባለንበት ሁኔታ የኔትዎርክ ችግር ቢኖርም በተቻለው አቅም በፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም እና ሌሎች ማሕበራዊ መገናኛዎች ሪል ስቴቱ የደረሰበትን ደረጃ እና የሚከተላቸውን ሂደቶች ለደንበኞቻችን እንዲሁም ለሌላው ማኅረሰብ እናስተዋውቃለን:: ከዚህ ባሻገር ዋና የመገናኛ ዘዴዎችን እንጠቀማለን፤ ከእነዚህ ውስጥ ከአሚኮ ጋር ለብዙ ጊዜ አብረን ስንሠራ ቆይተናል::
ለወጣቱ የሚመክሩት ካለ?
የሰው ልጅ በእቅድ ነው መመራት ያለበት፤ የአንድ ቀን፣ የሳምንት፣ የወር፣ የዓመት እቅድ እያቀዱ በዛ መንንቀሳቀስ ያስፈልጋል:: ትምህርት ያለው በትምህርቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል:: አጉል ሱስ እና ተስፋ መቁረጥ የመሰሉ የሚያዘናጉ ነገሮች ላይ ሳያተኩሩ ለስኬት መትጋት ያስፈልጋል:: ማንም ሰው የያዘውን ሥራ ጠንክሮ ከሠራ የሚፈልገው ደረጃ ላይ መድረስ ይችላል:: እውቀት ያለው ገንዘብ ካለው ጋር በመጣመር አብሮ መሥራትን ቢለምድ መልካም ነው ብዬ እላለሁ::
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም