ዝነኛዉ የደቡብ አፍሪካ ስፖርት

0
219

የ2023ቱ የራግቢ የዓለም ዋንጫ በፈረንሳይ ፓሪስ ተደርጎ ሲጠናቀቅ ደቡብ አፍሪካ ለአራተኛ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት አዲስ ታሪክ ጽፋለች:: ኒውዝላንድ ሁለተኛ፣ እንግሊዝ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል፡፡በውድድሩ 20 ሀገራት የተሳተፉ ሲሆን ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ ብቻ በመድረኩ ተካፍለዋል::

ውድድሩ ከ20 በላይ ሀገራት በቀጥታ የቴሌቭዥን መስኮት ተላልፏል:: በየጨዋታውም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች በቀጥታ በቴሊቭዥን ጨዋታዎችን መመልከታቸውን ዓለም አቀፉ የራግቢ ማሕበር ዘግቦታል:: ለአሸናፊ ሀገራት የሚሰጠው ሽልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል:: ዘንድሮ ለአሸናፊው ቡድን ስድስት ሚሊዮን ዶላር፣ ሁለተኛ ደረጃን ለያዘው ሦስት ሚልዮን ዶላር፣ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ለጨረሰው አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል:: ሌሎችም ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች በየደረጃቸው የሽልማቱ ተቋዳሽ ሆነዋል::

የራግቢ ስፖርት ፍጥነት እና ጠንካራ የአካል ብቃት የሚጠይቅ ስፖርት ነው:: በአንድ ቡድን 15 ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ የሚገቡ ይሆናል:: እነዚህ ተጫዋቾች በሁለቱ የሜዳ ክፍል ማለትም በተከላካይ እና በአጥቂ ስፍራ ቦታቸውን ይይዛሉ::

በአጥቂ ስፍራ 8 ተጫዋቾች በተከላካይ ቦታ ደግሞ 7 ተጫዋቾች ናቸው ወደ ሜዳ የሚገቡት:: አጠቃላይ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ 80 ደቂቃ ሲሆን እኩል ለሁለት ተከፍሎ በሁለት አጋማሽ ይከናውናል:: በመሀልም የ10 ደቂቃ የእርፍት ጊዜ ይሰጣል::

የመጫዎቻ ኳሱንም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በእጅ ይዞ ሮጦ ማስገባት አምስት ነጥብ ያሸልማል:: ቅጣት ምት እና ፍጹም ቅጣት ምትም ነጥብ ያሰጣል:: ሁለቱም በእግር የሚመቱ ሲሆን ለቅጣት ምት ሁለት ነጥብ ለፍጹም ቅጣት ምት ደግሞ ሦስት ነጥቦች ነው የሚያሰጠው::
አንድ ቡድን እስከ ሰባት ተጫዋቾችንም ቀይሮ ወደ ሜዳ ማስገባት እንደሚችል የዓለም አቀፉ የራግቢ ማሕበር ሕግ ያስረዳል::

በዚህ ሕግ እየተመሩ የዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ በ1983 እ.አ.አ በእንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ስኮትላንድ እና ዌልስ መካከል ተደርጎ እንደነበረ መረጃው ያሳያል:: በኋላም ዓለማቀፉ የራግቢ ማሕበር ተመስርቶ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል::

የራግቢ ስፖርት ከቅኝ ግዛት ጋር የተሳሰረ ታሪክ አለው:: አሁን ላይ ስፖርቱ በስፋት የሚዘወተረው በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር በነበሩት ሀገራት እንደሆነ Match Rport የተባለ ድረገፅ መረጃ ያመለክታል:: አውስትራሊያ፣ ኒውዝላንድ፣ አሜሪካ፣ ህንድ እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ እና የዚህ ስፖርት አዘውታሪ ሀገራት ናቸው::

እንደ ፊጂ ደሴት ያሉ ሀገራት ደግሞ በዓለማችን በአራቱም አቅጣጫ የሚወደደውን የእግር ኳስ ጨዋታን እንኳ ጭራሽ የማያውቁ፣ ራግቢን ግን አብዝተው የሚወዱ ናቸው::
በፓስፊክ ውቅያኖስ የምትገኘዋ ፊጂ ደሴት በሀገሪቱ የስፖርት ታሪክ ውጤት ያስመዘገበችበት ስፖርትም ነው ራግቢ:: በአፍሪካ ዚምባቡዌ፣ ዛምቢያ፣ቦትስዋና፣ ጋና፣ ናይጀሪያ፣ ዩጋንዳ እና ኬኒያ የራግቢ ስፖርት እንቅስቃሴ በስፋት የሚታይባቸው ሀገራት ናቸው:: በእስያ ሀገራትም ስፖርቱ የተስፋፋ ሲሆን በተለይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሀገራት ስፖርቱ በሚገባ ይዘወተሩባቸዋል::

በደቡብ አፍሪካ ስፖርቱ የነጮችን የበላይነትን አስቀርቷል፡፡ በአፓርታይድ ሥርዓት የነበረውን ቂም በቀል ሽሮታል፡፡የተለያዩትን እጅ ለእጅ አጨባብጦ ለሀገራቸው በአንድ እንዲቆሙ አድርጓል::

ይህ ስፖርት በደቡብ አፍሪካ ባህልም የሆነ አንድነትን፣ ሰላምን እና ፍቅርን የሰበከ ጭምር ነው የራግቢ ስፖርት:: በአብዛኛው የዓለማችን ክፍል ስፖርቱ የገዢው መደብ ነው ተብሎ ይታወቅ የነበረ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ግን ታች ባሉት የሠራተኛው መደብ ይታወቃል፡፡ የራግቢ ስፖርት ታሪክ እ.አ.አ በ1823 ይጀምራል:: ስፖርቱ በእንግሊዝ ምድር እንደተጀመረም የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ::

የራግቢ ስፖርት በእንግሊዝ ተወልዶ ቀድሞ ይጀመር እንጂ አሁን ላይ ደቡብ አፍሪካውያን እንዳሳደጉት ከሚናገሩት በላይ ውጤታቸው ያስተጋባል:: በሀገሪቱ እንደ ራግቢ ስኬታማ የሆነ ስፖርት ማግኘትም ይከብዳል::

ከእግር ኳስ እና ከክሪኬትም በላይ ተወዳጅ ስፖርት ነው:: ይህ ስፖርት በደቡብ አፍሪካ የተዋወቀው በ1875 እ.አ.አ ገደማ መሆኑን መረጃዎች አመልክተውል::

በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች ሲሆን እንግሊዛውያን ወታደሮች፣ ሰፋሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው ስፖርቱን ያዘወትሩ እንደነበረ መረጃዎች አመልክተዋል:: ከዛ በኋላም ብዙ ጊዜ ሳይፈጅ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተወዳጅ እና ተዘውታሪ መሆን ችሏል:: የአትሌቲክስ ስፖርት ሲነሳ ኢትዮጵያ እና ኬኒያ ስማቸው ቀድሞ እንደሚነሳ ሁሉ አሁን ላይ ራግቢም የደቡብ አፍሪካ ምልክት ሆኗል::
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የሀገሪቱን ባህል፣ ወግ እና እሴት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስተዋወቀ ይገኛል:: ደቡብ አፍሪካም በዚህ የስፖርት ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም እያገኝችበትም ነው::

ከትኬት ሽያጭ፣ ከማስታወቂያ፣ ከቴሌቪዥን መብት እና መሰል ነገሮች ደቡብ አፍሪካውያን በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች በየዓመቱ ያገኙበታል:: ሀገሪቱ በትምህርት እና በጤና እየሰራች ላለችው ሥራ ትልቁ የገንዘብ ምንጭ የራግቢ ስፖርትም ነው ::
በደቡብ አፍሪካ የነጮች የበላይነት በመኖሩ እስከ 1990ዎቹ እ.አ.አ መጀመሪያ ከዘረኝነት የፀዳ የራግቢ ማሕበር ለመመስረት አስቸጋሪ ነበር:: ከ1964 እስከ 1992 እ.አ.አ በአፓርታይድ ምክንያት ከኦሎምፒክ ጨዋታዎች መገለል ደርሶባቸውም ነበር ደቡብ አፍሪካውያን::
መጋቢት 1992 እ.አ.አ ግን የቆዳ ቀለምን መሰረት ያላደረገ ሁሉንም በፍትሐዊነት የሚያሳትፍ አዲስ ብሔራዊ ቡድንም የተዋቀረበት ወቅት ነው:: አሁን ላይም ሁሉም በሚባል ደረጃ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያላቸው ተጫዋቾች በመሆናቸው 90 በመቶ የሚሆነውን ህዝብ እንደሚወክሉ የRugby world መረጃ ያሳያል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑም ስያሜ እስካሁን ድረስ የሚጠቀሙበት ሲሆን ስፕሪንግ ቡክስም ይባላል:: በደቡብ አፍሪካ የነፃነት መብት ታጋዮች በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት የተለያዩትን ህዝቦች አንድ ለማድረግ ይህን ስፖርት እንደ ትልቅ መሳሪያ ተጠቅመውበት አልፈዋል::
በ1995 እ.አ.አ ደቡብ አፍሪካ ተሳክቶላት 3ኛውን የዓለም ራግቢ ዋንጫ በማዘጋጀት በሀገሯ ማስቀረት ችላለች:: በወቅቱ የአፓርታይድ ሥርዓት ከደቡብ አፍሪካ ምድር የተቀበረበት በመሆኑ ጭምር ትልቅ ፌሽታ እና ደስታ ሆነ:: የጥላቻ ግንቡም ተንዶ ስፖርቱ እጅ ለእጅ እንዲያያዙ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል::

የነፃነት ታጋዩ እና የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ “አምርረው በጥላቻ ተለያይተው የነበሩት የአንድ ሀገር ሕዝቦች አንድ ሆኑ” የሚል ንግግር በራግቢው የዓለም ዋንጫ በመዝጊያ ሥነ ስርዓቱ ንግግራቸው አሰምተዋል::
“አንድ ብሔራዊ ቡድን አንድ ሀገር” እንዲሁም “ስፖርት ዓለምን አንድ የሚያደርግ፣ ሰላም እና ፍትሕን የማምጣት ኃይል አለው” በሚለው ዝነኛ ንግግራቸው እስካሁን በስፖርቱ ታሪክ ጎልቶ የሚስተጋባ ድምጽ ነው::

Bekur /በኲር, [11/13/2023 8:40 AM]
ከታላቁ ፌሽታ በኋላም የነፃነት ታጋዩ እና ፕሬዚዳንቱ ኔልሰን ማንዴላ የብሔራዊ ቡድኑን አምበል ፍራንሷ ፔናርን በቤተ መንግስታቸው ጋብዘው ባነጋገሩበት ወቅት የራግቢው ተጫዋች እንዲህ ብሎ ነበር:: “ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የራግቢ ስፖርትን ለመመልከት ስቴዲየም አይገቡም ቢገቡ እንኳ ለነጭ ያደላውን ብሔራዊ ቡድን ለመደገፍ ሳይሆን ተቃራኒ ቡድንን ለማበረታት እና ለመደገፍ ነው:: የብሔራዊ ቡድኑ ሰንደቅ ዓላማውን፣ መዝሙሩን እና መለያውን በጣም ይጠሉታል::” በማለት ለነፃነት ታጋዩ መናገሩን ያመለክታል::

ካዛ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ምድር ሁሉም ነገር ተስተካክሎ በታላቁ የራግቢ መድረክ በተደጋጋሚ ውጤታማ ለመሆን በቅታለች:: በሁለቱም ፆታዎች ከታች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ክለቦች እንዲመሰረቱ በማድርግ እየሠሩ ይገኛሉ:: ታዳጊዎችን ከስምንት ዓመታቸው ጀምረው በፕሮጀክት ውስጥ በማሳደግ ውጤታማ ሥራ ከሚሠሩ ሀገራት መካከልም ናት ደቡብ አፍሪካ፡፡

ደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያዋን የራግቢ የዓለም ዋንጫ በወንዶች ብሔራዊ ቡድን ካሳካች በኋላ የሴቶች ቡድንንም አቋቁማለች:: የሴቶቹ በሔራዊ ቡድን በ2006 እ.አ.አ የተመሰረተ ሲሆን በዓለማችን ከሚገኙ ምርጥ 10 የራግቢ ብሔራዊ ቡድኖች መካከልም ነው፡፡
በተለይ ደግሞ የወጣት ቡድኖችን ማቋቋሟ እና በተለያየ እርከን የውድድር ሥርዓቶችን በመዘርጋቷ አሁን ለውጤት በቅታለች:: ደቡብ አፍሪካውያን የራግቢ ተጫዋቾች በአውሮፓ ምድር እጅግ ተፈላጊዎችም ሆነዋል፡፡ በአካል ብቃት ጠንካራ መሆናቸው፣ አዕምሯቸው ስፖርቱን በቀላሉ የሚቀበል መሆኑ፣ ለሙያቸው ያላቸው የገዘፈ አመለካከት በአሰልጣኞቹ ዘንድ ተፈላጊ እንዳደረጋቸው Rugby pass.com የተባለ ድረገጽ አስነብቧል፡፡

አሁን ላይ በደቡብ አፍሪካ በፒሪሜራ ዲቪዞን እና በመጀመሪያው የራግቢ የሊግ እርከን በርካታ የራግቢ ቡደኖች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቡድኖችም በዓለም አቀፍ መድረክ የነገሱ ታላላቅ ተጫዋቾችን አፍርተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የራግቢ ማህበር የሀገራትን ወቅታዊ ደረጃ ባወጣው መሰረት ደቡብ አፈሪካ ቀዳሚውን ቦታ በመያዝ እየመራች ተገኛለች፡፡
ራግቢ ወርልድ ማች ሪፖሪት እና ራግቢ ፓስ ዶት ኮምን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል

(ስለሽ ተሾመ)
በኲር ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here