በጃፓን – ሁናን ግዛት፣ ሰሜን ምዕራብ ቀጣና ነው የሚገኘው- ዣንጂያጂ የደን ብሔራዊ ፓርክ፡፡ በሀገሪቱ በ1882 እ.አ.አ የተመሰረተ የመጀመሪያ ፓርክም ነው፡፡ ጠቅላላ ስፋቱ 130 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ተለክቷል፡፡
በ1992 እ.አ.አ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ አካባቢ እና ባህል ድርጅት በዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ እውቅና ተችሮታል፡፡ በ2004 እ.አ.አ የዓለም “ጂኦ ፓርክ” ደረጃን መቀዳጀትም ችሏል፡፡
ፓርኩ ከዣንጂያጂ ከተማ በስተሰሜን 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ከከተማዋ ወደ ፓርኩ ቀጣና ለመድረስ በታክሲ 40 ደቂቃ አሊያም በአውቶቡስ የአንድ ሰዓት ጊዜን ይወስዳል፡፡
ፓርኩ ከቻንግሻ 320 ኪሎ ሜትር፣ ከቾንግ ኪንግ 510 ኪሎ ሜትር፣ ከሻንጋይ 1280 ኪሎ ሜትር፣ ከዣንግጂያጂ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው፡፡
በፓርኩ ቀጣና ውስጥ አምስት የተለያዩ የጉብኝት መዳረሻዎች አሉት፡፡ ከነዚህ መካከል ፡- 3000 በነፋስ እና ዝናብ የተጠረቡ ተፈጥራዊ የአሽዋ ቋጥኞች፣ በደን የተሸፈነ ቀጣና፣ የቲያንዥ ተራራ፣ በዓየር ላይ በተወጠረ የብረት ገመድ ላይ በሚንሸራተት መጓጓዣ ሳጥን ቀጣናውን መጐብኛ እና ረዢም ጊዜን ያስቆጠሩ እድሜ ጠገብ ጥንታዊ ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ፓርኩን በክብ ቅርፅ ዙሪያውን የሚያስቃኝ የተከለለ ፍርግርግ የተመታበት ከፍ ያለ ማማም ይገኛል፡፡ በሀገራቱም ማእዘን ተፈጥሮ -ነፋስ፣ ዝናብ እና ፀሀይን በማፈራረቅ የቀረፀቻቸው 3000 ቀጥ ብለው የቆሙ አምዶች ተሰድረውበታል- በፓርኩ፡፡
ፓርኩን ለመጐብኘት ተመራጩ ወር ጥቅምት ሲሆን ጐብኚዎች አስቀድመው አቅደው መዘጋጀት እና ከአስጐብኝዎች ጋር መገናኘት ይኖርባቸዋል፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት፡- ዘወርልድ ትራቭል ጋይ፣ ቻይና ቲያንቱር እና ቢቢሲ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም