የሀሞት ጠጠር

0
123

የሀሞት ከረጢት ጠጠር በሀሞት ከረጢት ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ጠጣር የሀሞት ክምችት ነው። የሀሞት ከረጢት ጠጠሮች መጠናቸው ከትንንሽ የአሸዋ ቅንጣቶች እስከ የ“ጎልፍ” ኳሶች ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ብዙ የሀሞት  ከረጢት ጠጠር ያለባቸው ሰዎች ምንም ምልክት ባይኖራቸውም የሀሞት ጠጠር ወደ አንጀት የሚወስደውን ቱቦ በመዝጋት ድንገተኛና ከባድ የሆድ ሕመም ሊያስከትልባቸው እንደሚችል የጤና ጉዳዮችን በብዛት በመተንተን የሚታወቀው ዓለም ዓቀፉ ዊቢ ኤ ምዲ (www.WebMD.com) ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

ታዲያ እኛም በዚህ ሳምንት የጤና አምዳችን ስለ ሀሞት ጠጠር የበለጠ ግንዛቤ ይፈጥርልን ዘንድ በእያስታ የጤና መዕከል የአጠቃላይ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት እና የጉበት፣ የቆሽትና የሀሞት ከረጢት ሳብ ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶ/ር ዘበናይ  ውቤ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

ዶ/ር ዘበናይ እንዳሉት ሀሞት በጉበት ተመርቶ በሀሞት ከረጢት ተጠራቅሞ እና አስፈላጊ ሲሆን ወደ ትንሹ አንጀት የሚረጪ ፈሳሽ ነው፡፡

በዋናነት ቅባታማ ምግቦች /ጮማ/ በምንመገብበት ጊዜ የምግብ ሥርዓት ስብስቡን ያሳልጣል፡፡ ይህ ማለት ምግብ በምንመገብበት ጊዜ (በተለይ ቅባታማ ምግቦችን)  ሀሞት ይረጫል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ቆሻሻዎችን ከሰውነት እንዲወገዱ እና አላስፈላጊ ባክቴሪያዎች ከአንጀት እንዲወገዱ ያደርጋል፡፡

የሀሞት ከረጢት ጠጠር የሚፈጠረው በሦስት መንገዶች እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ዘበናይ አንደኛው በሀሞት ብክለት (ኢንፌክሽን)  ሲሆን ሁለተኛው የሀሞት ከረጢት እንቅስቃሴ በሚቀንስበት እና ሦስተኛው ደግሞ የቀይ ደም ሕዋሳት በብዛት በሚመረቱበት ጊዜ ነው፡፡

የሀሞት ከረጢት ጠጠር እንዲፈጠር ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል ዕድሜ (ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች) ፣ በእርግዝና ወቅት፣ የሆርሞን ሕክምና በሚያደርጉ ሰዎች፣ ከዚህ በፊት በቤተሰብ የሀሞት ከረጢት ጠጠር ያለባቸው ሰዎች፣ አንዳንድ መድኃኒቶች (ለአብነትም ኮሌስትሮል ያለባቸው ሰዎች የሚወስዱት መድኃኒት) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አትክልትና ፍራፍሬ አለማዘውተር፣ ቅባታማ መግቦችን ማዘውተር፣ በቂ ፈሳሽ አለመውሰድ፣ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ አልኮል በብዛት መውሰድ፣ ክብደት በፍጥነት መጨመር እና በፍጠነት መቀነስ ለሀሞት ጠጠር መከሰት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩም ዶ/ር ዘበናይ አብራርተዋል።

ባለሙያው እንደተናገሩት በአብዛኛው ሰዎች (80 በመቶ የሚሆኑት) የሀሞት ከረጢት ጠጠሩ ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ሳይፈጥርባቸው ለረዥም ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ወይም ፈፅሞ ሕመም ላይኖራቸው ይችላል። የሀሞት ከረጢት ጠጠር እንዳለባቸው የሚታወቀው በሌላ ሕመም ምክንያት አሊያም ለሕክምና ክትትል በሚታዘዝ የአልትራሳውንድ ምርመራ ነው፡፡

የሀሞት ከረጢት ጠጠር ያለባቸው ሰዎች ምናልባት ምልክት በሚኖራቸው ጊዜ በብዛት የሚስተዋሉት በቀኝ በኩል ከጎድን አጥንት ዝቅ ብሎ ውጋት፣ አልፎ አልፎ ከሕመሙ ጋር የተያያዘ መጠነኛ ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ እንዲሁም የዓይን ቢጫ መሆን ናቸው። ብዙ ጊዜ ሕመሙ ምግብ ከተበላ ከ30 እና 40 ደቂቃ በኋላ የሚጀምር ሲሆን ሕመሙም ከአንድና ከሁለት ሰዓት በኋላ ተመልሶ የሚጠፋ ይሆናል  ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ዘበናይ ማብራሪያ አንዳንድ ጊዜ የሀሞት ከረጢት ጠጠር ኖሮም ሌሎች ተያያዥ  ሕመሞች (ለምሳሌ የጨጓራ ሕመም) ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ሕመሙን መለየት ይገባል። ከላይ ከተገለጹት የሕመሙ ምልክቶች ባሻገር የተለዬ ነገር ከተሰማን በሕክምና መረጋገጥ አለበት ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

የጨጓራ ሕመማቸው የሚመላለስ (በተደጋጋሚ የሚከሰት) እና መፍትሔ ከሌለው የሀሞት ጠጠር ሊሆን ስለሚችል ቢታዩት መልካም ነው ሲሉም ይመክራሉ።

የሀሞት ከረጢት ከጠጠሩ ጋር ተያይዞ ብክለት (ኢንፌክሽን) በሚኖርበት ጊዜ ልትፈነዳ ትችላለች፡፡ ይህ ሁኔታ በፍጥነት ካልታከመ ለሞት እንደሚዳርግ ነው የሕክምና ባለሙያው የሚናገሩት፡፡ ኢንፌክሽን ሲፈጠር በፊት ለአንድ ስዓት እና ለሁለት ስዓት ያህል ይቆይ የነበረው ሕመም እስከ ሁለት ቀናት ሊቆይ እንደሚችልም ጠቁመዋል። ከዚህ በሻገር ከፍተኛ ሙቀት (ትኩሳት)፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስና ማቅለሽለሽ ይኖረዋል፡፡ እንዲሁም ሕመሙ በፊት ከነበረው በጣም ጠንካራ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋም ከተደረሰ የሀሞት ከረጢት ሳትፈነዳ ማከም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በዋናነት የሀሞት ከረጢት ጠጠር ሕክምና ጠጠሩን ከነሀሞት ከረጢቱ በቀዶ ጥገና ሕክምና ማስወገድ ሲሆን ይኸውም ሆድን በመክፈት አሊያም በሆድ ግድግዳ ላይ ትንንሽ ቀዳዳዎች በማበጀት በካሜራ ዕይታ እየታገዘ ሊሠራ ይችላል። ይህም ሕክምና ላፓራስኮፒ እንደሚባል ነው ዶ/ር ዘላለም የገለጹልን፡፡

ላፓራስኮፒ ያልተወሳሰበ የሀሞት ከረጢት ጠጠር በሚኖርበት ጊዜ ተመራጪ ሲሆን የሚፈጠረው ክፍተት ከአንድ ሴንቲ ሜትር አይበልጥም፡፡ በላፓራስኮፒ የሚደረግ ቀዶ ጥገና ታካሚዎች ቶሎ እንዲያገግሙ ስለሚያደርግና  አነስተኛ ማስታገሻዎችን እንዲወስዱ ስለሚያስችል ተመራጭ ነው፡፡ ሁለተኛው ሕክምና ከአራት እስከ አምስት ሴንቲ ሜትር ሰውነትን በመክፈት የሚከናወን ቀዶ ጥገና ነው፡፡ ይህም የሚከናወነው የላፓራስኮፒ መንገድ ውስብስብ ከሆነ ነው። እንዲሁም ኢንፌክሽን ሲኖር ተመራጩ ቀዶ ጥገና ነው፡፡

የሀሞት ከረጢት አለመኖር ብዙም የሚያመጣው ችግር የለም፡፡ ሆኖም የሀሞት ከረጢቷ ከተወገደች በኋላ ቅባታማ ምግብ እና እስክንጠግብ ስንመገብ የሕመም ስሜት ሊኖር እንደሚችል ነው የሕክምና ባለሙያው የጠቆሙት፡፡  በተለይ የሀሞት ከረጢቷ ከተወገደች በኋላ ባሉት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት በአንድ ጊዜ እስክንጠግብ  እና እንዲሁም ቅባታማ ምግቦችንም መመገብ አይመከርም ይላሉ፡፡

ባለሙያው አክለውም አንዳንድ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችን በማድረግ የሀሞት ጠጠርን እንዳይከሰት ማድረግ እንደሚቻል ያብራራሉ። ለአብነትም አትክልትና የጥራጥሬ እህሎችን፣ ብዙ ፋይበር እና አነስተኛ ቅባት ያላቸውን ምግቦች (ለውዝ፣ ስንዴ፣ አጃ፣ የወይራ ዘይት እና አሳ) አዘውትሮ መመገብ ይመከራል። ይህም ፋይበር ከመጠን በላይ ኮሌስትሮል ከሰውነት ውስጥ ለማስወገድ ይረዳል።

ከዚህ በተጨማሪም መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በቀን ቢያንስ ለ30 ደቂቃዎች ማከናወን ተመራጭ መሆኑን የጤና ባለሙያው ይመክራሉ። “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” ነውና ብሂሉ ይተግብሩት መልዕክታችን ነው።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here