የሀገር ውስጥ ምርት፦ መኩሪያም መሻገሪያም

0
356
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምድ እየዳበረ ሲመጣ አምራች ኢንዱስትሪዎች ይበረታታሉ:: በተጨማሪም ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል::
አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ምርት ቢያመርቱና ዜጐች የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምዳቸው ቢያድግ የምጣኔሀብት ዕድገት እንደሚኖር ነው የሚናገሩት:: ይሁን እንጂ በሀገራችን የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ልምድ ዝቅተኛ ነው፤ የሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም ያለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለመረዳትና ለማሳደግ ጠንካራ ሥራ ማከናወንን ይጠይቃል::
አቶ በላይነህ አስማረ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔሀብት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ናቸው፤ የሀገር ውስጥ ምርት አጠቃቀም እና አበርክቶውን በተመለከተ ከበኩር ጋር ቆይታ አድርገው ሙያዊ ማብራያ ሰጥተውናል::
የሀገር ውስጥ ምርት አለመጠቀም ለምጣኔሀብታዊ ቀውስ ምክንያት መሆኑን ይገራሉ:: ይህም ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ጠቁመዋል::
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት (2015 ዓ.ም) ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ምርት ወደ ውጭ ሀገር ስትልክ፤ ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የገባው ደግሞ 18 ቢሊዮን ዶላር ያህል ነው:: ይህም የኢትዮጵያ የንግድ ስርዓት የተዛባ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል የምጣኔሀብት መምህሩ::
ኢትዮጵያ በአብዛኛው ወደ ወጭ ሀገር የምትልከው የግብርና ምርቶችን ነው፤ የግብርና ምርቶች ደግሞ በዓለም ገበያ ላይ ያላቸው ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑ በጣም ብዙ ምርት ቢላክም የሚገኘው ዶላር አነስተኛ መሆኑን ያስረዳሉ::
በተቃራኒው ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባቸው ምርቶች የኢንዱስትሪ ውጤቶች በመሆናቸው የሀገርን ምጣኔሀብት ያዛባሉ ይለሉ::
እነዚህ ምርቶች በገበያ ላይ ያላቸው ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ የወጭና የገቢ አለመመጣጠን ይከሰታል:: መሰል ችግሮችን ለማቃለል ታዲያ በሀገር ውስጥ ያሉ ምርቶችን በብዛት እና በጥራት ማምረትና መጠቀም ዋናው መፍትሔ መሆኑን ያነሳሉ፤ ይህን ልምድ በማሳደግም የሀገርን ምጣኔሀብት መገንባት እንደሚገባ ያስረዳሉ::
የሀገር ውስጥን ምርት የመጠቀም አመለካከትና ፍለጎት ዝቅተኛ ነው፤ ይህም ብዙዎቻችንን የውጭ ሀገር ምርትን ናፍቂዎች እና ጥገኛዎች አድርጎናል:: በመሆኑም ይህን አመለካከት ለመቀየር እና የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባሕላችንን ለማሳደግ ግንዛቤ መፍጠር ይገባል:: ይህን በማድረግም የተዛባውን የንግድ ሰንሰለት ማስተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል::
“በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል ሲመለከቱ ዜጐች ምርቱ ጥራት ያለው የማይመስላቸው ብዙዎች ናቸው” የሚሉት መምህሩ፤ ይህ አመለካከት መለወጥ እንዳለበት ተናግረዋል:: “የሀገር ውስጥ ምርትን ስንጠቀም አምራቾችን እናበረታታለን፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የራሳችንን አሻራ እናሳርፍለን:: ሌሎች ሀገሮች ለሀገር ምጣኔሀብት ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ሁሉ እኛም የሀገራችንን ምርት የመጠቀም ልምዳችን ቢዳብር መልካም ነው” ብለዋል::
እንደ መምህሩ ገለፃ የውጭ ምርት ናፋቂ መሆናችን ሌላም ጉዳት ይዞ የሚመጣ ነው፤ ትውልዱ በውጭ ባሕል እንዲበረዝ ያደርገዋል:: በመሆኑም ትውልዱ ወደ ቀልቡ መመለስ አለበት::
የሀገርን ምርት መጠቀም ለምጣኔሀብትና ለሀገር ዕድገት ያለውን ፋይዳ፣ በትምህርት ሥርዓቱ ተቀርፆ መሠራት እንዳለበት ሐሳባቸውን ለበኲር አጋርተዋል::
አቶ በላይነህ እንዳሉት የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም የሀገር ውስጥ ምርቶች ፍላጐት እንዲያድግ ያደርጋል:: ፍላጎቱን ለማርካት ደግሞ አምራቾች በብዛት ለማምረት ይነሳሳሉ፣ ይበረታታሉ:: በዚህም የተሻለ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ:: አምራቾች የተሻለ ገቢ ያገኛሉ:: አቅማቸውን ያሳድጋሉ:: ለውጭ ሀገር ምርት ግዢ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረትም ድርሻው ከፍተኛ ነው:: የተዛባው የንግድ ሚዛንም ይስተካከላል::
ተጠቃሚዎች ሁልጊዜም የሚፈልጉት የተሻለ እርካታ የሚሰጣቸውን፣ የተሻለ ደስታ የሚያገኙበትን፣ ተመጣጣኝ ዋጋ መኖሩን እና ጥራት ያለው ምርት መሆኑን ነው፤ በመሆኑም አምራች ድርጅቶች የተሻለና ጥራት ያለው ምርት ለገበያ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል::
በተለይ ደግሞ ተንቀሳቅሶ ምርቶችን ለማግኘት ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ፍላጎትን ለማሟላት የአካባቢን ብሎም የሀገርን ምርት የመጠቀም ባሕልን ማዳበር ለችግሩ መውጯ መንገድ ነው:: መንግሥት ለአምራች ድርጅቶች የፋይናንስ፣ የቦታ፣ የግብዓትና የቴክኖሎጂ እገዛ በማድረግ ማብረታታት ይጠበቅበታል ይላሉ::
ከውጭ ሀገር የራሳቸውን ሀብት ወይም መዋዕለ ንዋይ ይዘው መጥተው በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በር መክፈት፣ የፈጠራ ክህሎትን ማዳበር፣ ለቴክኖሎጂ ትኩረት መስጠት፣ አዳዲስ ግኝቶችን ማፍለቅ ያስፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ ትምህርት ላይ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን መምህር በላይነህ ያስረዳሉ፤ የዓለም ምጣኔሀብት (ያደጉ ሀገራት) የተቀየረው በትምህርትና አዳዲስ ነገሮችን ማፍለቅ መቻላቸው መሆኑን በማከል::
የተለያዩ ሀገራት ዜጐቻቸው የሀገርን ምርት እንዲጠቀሙ የተለያዩ አዋጅና ፓሊሲዎችን በአስገዳጅነት እንዳስቀመጡ አቶ በላይነህ ይጠቅሳሉ:: ለአብነትም አሜሪካ በ1933 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ አስገዳጅ ሕግ ተግባራዊ ማድረጓን አንስተዋል:: በድንጋጌውም በሀገር ውስጥ ያሉ አምራቾች ሁሉንም ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ እንዳያመጡ ዕቀባ ያደርጋል::
በዚህም በሀገር ውስጥ ያሉ ሀብቶችን ብቻ እንዲጠቀሙ አድርገዋል:: የውጭ ምርቶች ወደ ሀገር ቤት እንዳይገቡ ከልክለዋል:: የሀገር ፍቅርን ለዜጐች በሚገባ እንዲሰጥ በማድረግ ምጣኔሀብታቸው እንዲያድግ ብርቱ ጥረት አድርገዋል:: ኢትዮጵያም መሰል ተሞክሮዎችን መቀመር እና መጠቀም እንዳለባት ነው ሙያዊ ሐሳባቸውን ያጋሩን::
የውጭ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ማዕቀብ የሚጥሉ ሀገራት፦ ታዳጊ ኢንዱስትሪዎችን ለማጠናከርና ለማበረታታት፣ ብዙ የሰው ኃይል ለመቅጠርና የንግድ ሚዛኑን ለማስጠበቅ እንደሆነ አቶ በላይነህ አስረድተዋል::
የሀገራቸውን ምርት በመጠቀም ግንባር ቀደም ሀገሮች ቻይና እና ህንድ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል:: ከሀገራቸው ወደ ሌሎች ሀገራት ለሥራም ሆነ ለጉብኝት ሲንቀሳቀሱ የሀገራቸውን ምርት ይዘው ወይም የሀገራቸውን ምርት በገበያ ላይ ፈልገው እንደሚገዙ ያብራራሉ:: ይህም ከሀገር ፍቅር ባሻገር አምራቾችን ለማበረታታት መሆኑን ይናገራሉ::
ሀገር ያለችበትን ሁኔታ መረዳት፣ ነገን እንድናስብ የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው::
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here