ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል “the impact of corruption on growth and inequality” በሚል ርዕስ እ.አ.አ በ2014 ባካሄደው ጥናት ሙስና ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ሥርዓትን ፣ ሕግን ፣ ደንብን፣ አሠራርን እና መርህን መጣስ ማለት ነው ሲል ገልጾታል። ማጥፋት፣ ማበላሸት እና ሕግን ጥሶ አምባገነናዊ አሠራርን መከተል ዋናዎቹ የሙስና መገለጫዎች እንደሆኑም ጥናቱ አመላክቷል:: ሙስና ዓለምን ከጦርነት፣ ከረሀብ፣ ከበሽታ እና ከተፈጥሮ አደጋ ባልተናነሰ ኢኮኖሚዋን እያደቀቀባት እንደሆነም የጥናት ውጤቱ ጠቁሟል::
ሙስና በተፈጥሮ ሀብት የታደለችውን አፍሪካም ገሚሱ ሕዝቧ ኑሮው ከድህነት ወለል በታች እንዲሆን አድርጎታል። ምክንያቱ ደግሞ አፍሪካ በራሷ ገዥዎች ፈላጭ ቆራጭነት፣ የፍትሕ እጦት፣ ስግብግብነት፣ የተዛባ የሀገር ሀብት አያያዝ እና አከፋፈል በመሳሰሉ ሰው ሠራሽ እንቅፋቶች ዕድገቷ ተገትቷል፤ ይህን ተከትሎም ሕዝቧ ለረሃብ፣ ለበሽታ እና ለሌሎች አስከፊ ችግሮች ተዳርገዋል።
የሙስና /ሳይሠሩ መበልፀግ/ ችግር ዜጎች በእኩልነት የማይኖሩባት ዓለም እንድትፈጠር በማድረግ ለኢኮኖሚ ልማቱ እንቅፋት መሆኑንም ጥናቱ አመላክቷል። በዚህም የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር እንዲበራከት ዋና ምክንያት ሆኗል:: እነዚህ ወጣቶች በሚመጡት ጥቂት ዓመታት ቁጥራቸው ከፍ ማለቱ እንደማይቀርም ጥናቱ አመላክቷል:: ይህን ተከትሎ ደግሞ ወጣቶች ለብስጭት እና ለቁጣ ተዳርገዋል:: ለአብነት በዓረቡ ዓለም በአንድ ወቅት ገንፍሎ የታየው የወጣቶች ለለውጥ መነሳሳት አንዱ ምክንያት ሙስና ባስከተለው የኢኮኖሚ ድቀት ፍትሐዊ የሥራ እድል አለመፈጠሩ ነው።
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የባለድርሻ አካላት ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ሐረጎት አብረሃ ለሪፖርተር ጋዜጣ እ.አ.አ ግንቦት 21 ቀን 2023 በሰጡት መረጃ የሙስናን ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተወሳሰቡ በመምጣታቸው መቆጣጠር እና መከላከል እንዳልተቻለ የሚያሳዩ ጥናቶች መኖራቸውን አንስተዋል:: ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም የተደረገው ሀገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናት ሙስና በሦስተኛ ደረጃ ሀገራዊ ችግር መሆኑን አሳይቷል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ጥናቶች የሚያሳዩትም ሙስና አሁንም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት አስጊ መሆኑን ነው::
እንደ አቶ ሐረጎት ገለፃ ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነት እና እምነት ትቶ ለግል ጥቅም የሚሄድ አመራር፣ ባለሙያ እና አገልጋይ ይኖራል:: በዚህም ከሕዝብ የተሰጠን ሥልጣን እና ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት የሕዝብ እምነት የሚሸረሽሩ አሠራሮች ሊኖሩ ይችላሉ:: ከዚህ አንፃር ማኅበረሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲከሰት… የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው::
የኢኮኖሚ ጉዳት ከውጭ አሊያም ከሕዝብ ተሰብስቦ ለተለያዩ ሀገራዊ ልማት መዋል የነበረበትን ውስን የሕዝብ ሀብት መንጠቅ፣ እምነት ማጉደል እና ያለውን ሀብት ለግል ጥቅም ማዋል ሌሎች የሙስና መገለጫዎች ናቸው::
የሙስና ጉዳት ከኢኮኖሚ ጉዳት የላቀ እንደሆነም አቶ ሐረጎት ሌላው መገለጫው መሆኑን ጠቁመዋል:: እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ “የሙስና ውጤት ንብረትን ከመዝረፍ ጋር ብቻ አያይዘን የምናየው አይደለም:: ዘርፋው ብዙ ፖለቲካዊ ቀውስ ያስከትላል:: የተረጋጋ ማኅበረሰብ እና የፖለቲካ አስተዳደር እንዳይኖር አሉታዊ አስተዋጽኦ አለው:: ለምሳሌ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት የነበሩ ጦርነቶች በየአቅጣጫው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከጀርባቸው ሙስና አለ ተብሎ ይታሰባል::
“ከዚህ አንፃር ደምረን ብናስቀምጠው ሙስናን መታገል ካልቻልን፣ በእንጭጩ የሚያስከትለውን ጉዳት ካልገታነው እና ካልቀነስነው በሀገራችን ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው:: ከዚህ አንፃር መንግሥት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ወደተከሰቱ ጦርነት እና ሌሎች ችግሮች ላይ ትኩረቱን ባደረገበት ጊዜ የሙስና ድርጊቶች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተበራክተዋል:: በመንግሥት አገልግሎት አሳጣጥ ላይ በተፈጠረ ተፅዕኖም ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች በርካታ ናቸው:: ይህንን ሁኔታ መንግሥት መቆጣጠር ካልቻለ ደግሞ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ሀገር ሆኖ ለመቀጠል አደጋው የከፋ ነው::”
በአማራ ክልል ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት የክልሉ ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና ፍትሕ ቢሮ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ሙስናን ለመታገል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ታኅሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል። ተቋማቱ በውይይታቸው ተቀራርቦ እና ተቀናጅቶ በመሥራት ሙስናን መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ ተነጋግረዋል፤ በቀጣይም ለሀገር እድገት፣ ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ… መሰናክል እየፈጠረ ያለውን ሙስናን ለመታገል የሚያስችል የትብብር ሥምምነት ተፈራርመዋል።
የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሐብታሙ ሞገስ እንዳሉት ሙስናን ለመከላከል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በመከላከሉ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው:: ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ግን በዋናነት በመደራጀት ድርጊቱ ሲፈፀም ከመከላከል አልፎ ተጠያቂነትን ማስፈን ካልተቻለ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አይቻለም::
“ከራሳችን ጀምረን ሃብት ማስመዝገብ አለብን!” ያሉት ኮሚሽነር ሐብታሙ የፍትሕ አካላትም ሃብታቸውን የማያስመዘግቡ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ተባባሪ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። ይህ ሲሆን ነው የራስን ተቋም ንጹህ አድርጎ አርአያ መሆን የሚቻለው ብለዋል::
በርካታ የኮሚሽኑ ምርመራዎች ወደ ፖሊስ ተቋም ከሄዱ በኋላ አልያም አቃቤ ሕግ ሲደርሱ ተከታትሎ በማስፈፀም በኩል ችግር መኖሩን የኮሚሽኑን ሪፖርት መነሻ አድርገው ምክትል ኮሚሽነሩ አንስተዋል:: በተቋማቱ መካከል ያለው የላላ ግንኙነት የሙስና ድርጊት በሚፈጽሙት መካከል ተገማች እንዲሆኑ ማድረጉን አንስተዋል:: ለአብነት በሀብት ማስመዝገብ ረገድ ከፍተኛ ሥራ ቢሠራም በምዝገባው ወቅት ብዙዎች ከገቢው በላይ ሃብት እየፈጠሩ መሆኑን ቢያሳዩም ተከታትሎ ርምጃ ካልተወሰደ ችግሩ የሚቀጥል በመሆኑ ተባብሮ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል::
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን በበኩላቸው ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ጭምር በሙስና ስለሚዘፈቁ ከፍተኛ የስብዕና መጓደል፣ ዘረፋ እና ምዝበራ መስፋፋቱን ተናግረዋል:: ዘረፋን የሚያበረታቱ አመለካከቶችም እየተስፋፉ ናቸው:: በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ስለሙስና ያላቸውን አመለካከት መቀየር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
“በአመራር ከተመደቡት ጀምሮ ችግሩ አለ” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አሁንም የወቅቱን የጸጥታ ችግር እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከፍተኛ የሀብት ምዝበራ እየተፈጸመ ነው:: ሕዝቡ ያለ እጅ መንሻ አገልግሎት እያገኘ አይደለም፤ መንገድ እና መሬትን ጨምሮ በሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ምዝበራ እየታየ ነው:: በሀብት አመላለስ በኩልም በሰላማዊ ጊዜም ችግር ነበረበት፤ አሁን ደግሞ የበለጠ ልንቸገር እንችላለ እና በትኩረት መሥራትን ይጠይቃል” በማለት አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ብርሐኑ ጎሽም (ዶ/ር) ሙስና እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመዋል:: እንደ ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ የሚቋረጡ የጸረ ሙስና የክስ መዝገቦች መብዛት ከሙስና ድርጊት ውስብስብነት ባህሪ የሚመጣ ነው:: በመሆኑም በሰው ምስክር ብቻ ጉዳዩን እልባት ለመስጠት አስቸጋሪ በመሆኑ ዘመኑን የዋጀ አሠራር ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል:: የሚቋረጡ የክስ መዝገቦችም የሚያሳዩት ይህንኑ እንደሆነ ነው ቢሮ ኃላፊው ያብራሩት። በቀጣይ በስምምነቱ መሰረት በተቋማት መካከል የሚፈጠረው የመረጃ መጣረስ ሌላኛው ሊፈታ የሚገባው ችግር እንደሆነም አመላክተዋል።
ገና በምርመራ ላይ ቢሆንም በመሬት ወረራ እና ሃብት ማፍራት የሙስና ወንጀል ከፖለቲካ አመራሩም ሆነ ከፀጥታ አካሉ ሳይቀር እየተሳተፈ እንደሆነ ኃላፊው አንስተዋል:: አሁን ባለው ሁኔታ አዝማሚያው እና ስጋቱ ከባድ ስለሆነ መረጃ በመቀባበል እና በቅንጅት በመሥራት ራስን ንፁህ አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል:: የሙስና ጉዳይ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሥርዓትም ጭምር በመሆኑ የተወሰደን ሀብት በማስመለስ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ጠይቀዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም