“የሀገር ፍቅር ስሜት በዜጎች ስነ ልቦና ውስጥ የግድ መኖር አለበት”

0
87

በኦጋዴን በረሀዎች፣ በካራ ማራ ተራራዎች ከተራ ወታደርነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ የጦር አመራርነት ለሀገራቸው ታግለዋል። ከስመጥሩው ጀግና አብዲሳ አጋ ጎን ቆመው ታላላቅ ጀብዱዎችን የፈጸሙት ጄኔራል የጀግና ሜዳይ ተሸልመዋል፤ ለሀገራቸውም ከፍተኛ ውለታ የዋሉት ጀግና ያለፍርድ 10 ዓመታት ታስረዋል- ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ።

 

ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ በቀድሞው የወለጋ ጠቅላይ ግዛት በጉዱሩ አውራጃ ቦሶ ሶቅዬ የገጠር መንደር ነሐሴ 16 ቀን 1933  ነው የተወለዱት፤ ከጃለታ ወዪሶ እና ከወርቂቱ ሁሶ።

 

እድሜያቸው ለትምህርት ቢደርስም በአካባቢያቸው ዘመናዊ ትምህርት ባለመኖሩ ዘመናዊ ትምህርት ፍለጋ ወደ ሻምቡ ለማምራት ተገደዋል። በገነት ጦር ትምህርት ቤት በነበራቸው ቆይታ በቂ እውቀትና መልካም ጠባይ የነበራቸው ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ፣ ለአመራርነት የሚያበቃቸውን መሠረት የጣሉት በዚሁ የጦር ትምህርት ቤት ነበር።

 

ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ በጦር አውድማ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈተኑት 1956 ዓ.ም ሶማሊያ ኢትዮጵያን በኦጋዴን በኩል በወረረችበት ወቅት ነው። በወቅቱ ምክትል መቶ አለቃ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራሉ፣ እንደነ አብዲሳ አጋ ካሉ የጦር ጀግኖች ጋር በመሰለፍ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ወረራውን መቀልበስ ችለዋል። ጦሩን ተቆጣጥሮ አመራር በመስጠት፣ በማዋጋት እና በመዋጋት ባሳዩት የላቀ ጀብዱ ከቀዳማዊ  ኃይለ ሥላሴ የጀግና ሜዳይ አግኝተዋል። ባሳዩት የጀግንነት ብቃት በወቅቱ በአውሮፕላን ላይ የሚደረጉ የጠለፋ ሙከራዎችን ለመከላከል የበረራ ደህንነት ስልጠና ለመውሰድ ከተመረጡት መኮንኖች መካከል አንዱ ናቸው።

 

በተለያዩ ግንባሮች ተሳትፈው ለሀገራቸው ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉት  ጄኔራሉ፣ በ1983 ዓ.ም የኢሕአዴግ ሰራዊት አዲስ አበባን መቆጣጠሩን ተከትሎ ወደ እስር ቤት ተግዘው ለ10 ዓመታት ያለ ፍርድ ቆይተዋል። ከእስር ከተፈቱ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች እያገለገሉ ሲሆን የሕይወት ተሞክሯቸውን እና ልምዳቸውን የያዙ እጣ ፈንታ፣ መስዋዕትነት እና ያልታደለች ሀገር፣ ሕዝብ እና ሠራዊት የሚሉ ሦስት መጽሐፎችን ለአንባቢያንም አበርክተዋል።  የሀገር ፍቅርን በማሳደግ፣ የሀገርን ሕልውናን በማቆየት፣ ሀገራዊ አንድነተን በማጠናከር እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳባቸውን አካፍለውናል፡፡

 

መልካም ንባብ!

 

በአንድ ሀገር አብሮነት እና አንድነት እንዴት ይሰፍናሉ?

የሀገር ፍቅር ስሜት በዜጎች ስነ ልቦና ውስጥ የግድ መኖር አለበት፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብቱ ከተከበረለት ግዴታውንም መወጣት አለበት፤ የሀገር ፍቅር በዚህ ይለካል፡፡ ሀገርን የሚመራው መንግሥትም እኩልነትን እና ፍትህን አስፍኖ መምራት አለበት፤ በዚህም አንድነትን ማስፈን ይቻለል፡፡

ፍትሕ እና ርትዕ የግድ ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ እና ሕግ ማክበር አለበት፡፡ ሕዝብ ደግሞ የመንግሥትን ሕግ እና ትዕዛዝ ማክበር አለበት፡፡ ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ሰላም፣ አንድነት እና አብሮነት ይሰፍናል፡፡ አንድ ሀገር ነጻ ነው የሚባለው የእያንዳንዱ ዜጋ መብት ሲጠበቅ ነው፡፡ ሕዝብ የመንግሥትን ሥርዓት እና ሕግ ካከበረ፣ መንግሥትም እኩልነትን ካሰፈነ እና ጭቆና ከሌለ በአብሮነት እና በሰላም መኖር ይቻላል፡፡

 

አብሮነትን እንዴት ወደ ሕዝብ ማስረጽ ይቻላል?

 

ከመበታተን ይልቅ አንድነት የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው የሕዝብን ንቃተ ሕሊና ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ ከጦርነት ይልቅ ሰላም መልካሙ አማራጭ እንደሆነ ሕዝብ መገንዘብ አለበት፡፡ ለጥያቄው ማጠናከሪያ ይሆናል ብየ የማስበውን ልናገር፤ በ1969 ዓ.ም ወደ ራሺያ ሄደን ነበር፤ ክሬምሊንን እና ሌሎች ቦታዎችን ጎብኝተናል፡፡ በቆይታችን እንዳስረዱን እ.አ.አ በ1917 በራሺያ አብዮት ጊዜ ሁለት ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ ቦልሸቪክ እና ሜንሼቪክ ይባላሉ፡፡ ሜንሸቪኮች እንደ ኢሕአፓ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው እና የቦልሼቪኮች ተቃዋሚ ነበሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ጆሴፍ ስታሊን ሜንሼቪኮችን ለማጥፋት ግድያ ይፈጽም ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቭላድሚር ሌኒን ስታሊንን “እስከ መቼ ነው የሜንሼቪኮችን ጭፍጨፋ ምትቀጥለው?” ይለዋል፤ ስታሊንም “አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ይቀጥላል” አለው፤ ሌኒን ግን መግደል ሳይሆን አሁንም አሁንም አስተምራቸው አለው፡፡ መብት እና ግዴታውን እንዲያውቅ ሕዝብን ማስተማር ወሳኝ መሆኑን ከዚህ እናያለን፡፡

 

በየቦታው ስለ አንድነት፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አብሮነት ጥቅም በየደረጃው ለህብረተሰቡ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ቢያንስ በወር አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን በማስተማር ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ቢሠራ ጠቀሜታው የጎላ ነው፤ እያስተማሩ ሕግን የሚጥስ ካለ ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ወይም ሌላ ብሔር ስለሆነ ሳይሆን እንደ ጥፋቱ ብሔር ሳይለይ የእርምት እርምጃ ያስፈልጋል፡፡

 

ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ህግን ማስከበር ያስፈልጋል፤ ሕግስ እንዴት ይከበራል?

ሕግን ከማስከበር አኳያ የግሌን ገጠመኝ ልናገር፤ በ1978 ዓ.ም በራያ አዘቦ ነበርኩ፡፡ አንድ ገበሬ በሬ ሸጦ ወደ ቤቱ ሲመለስ ከወታደሮቼ አንዱ ያገኘዋል፡፡ ሲፈትሸው 25 ሺህ ብር ያገኝበታል፡፡ ገበሬውን ገድሎ ብሩን ይዞ ይሰወራል፡፡ በአጋጣሚ አንድ ሌላ ገበሬ ከሩቅ ክስተቱን አይቶ ኖሮ ለቤተሰቦቹ ይነግራል፤ ቤተሰቦቹም ለእኔ ያመለክታሉ፡፡ በባላ ከተማ በኩል የወጡ ወታደሮችን አጣራን፤ ምስክሩን ገበሬ ጠርተንም እንዲለይ አደረግን፤ ገበሬውም ገዳዩን አጋለጠ፡፡ ወታደሩም “ገንዘቡ አጓጉቶኝ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ” ብሎ አመነ፡፡ በወቅቱ ወታደራዊ ሕግ ጥብቅ ነበር፤ ሌሎቹ እንዲማሩበት እርምጃ ተወሰደ፡፡ የአካባቢው ህዝብ አቢዮታዊ ሠራዊቱ መጣልን እንጂ መጣብን ሊል አይገባም፤ ማንም ወታደር ይህን መሰል ግፍ በሕዝብ ላይ እንዳይፈጽም በሚል ትምህርት ሰጠን፡፡ ከአካባቢው ለቀን እስክንወጣ ድረስ አንድም ሰው አልተገደለም፤ የበደል አቤቱታም አልቀረበም፡፡ እርምጃዎች ሲወሰዱ በቂ ማስረጃ እና ከባድ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ግን መረሳት የለበትም፡፡ ከሕግ በላይ የሆነውን፣ ወንጀል የሚፈጽመውን ግን እንደ ሀረር ሰንጋ ዝምብለን የምንቀልብበት ሁኔታ አይታየኝም፡፡ ለሥርዓት አልበኝነት እና ለግርግር የሚያጋልጠው ሕግ ማስከበርን ችላ ሲሉ ነው፡፡

 

ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን መምረጥ ምን ጉዳት አለው?

ሕግን ከማውጣት ባሻገር ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ ፍትሕን ማስፈን ያስፈልጋል፤ ተግባራዊነቱን መቆጣጠርም ወሳኝ ነው፡፡ ይህ አብሮነትን ያመጣል፡፡ አብሮነት እና አንድነት ደግሞ ለሰላም እና ለእድገት ቁልፍ ናቸው፡፡ ሱዳንን በምሳሌነት ብናነሳ መከፋፈል፣ መለያየት እና መናናቅ ጥቅም እንደሌለው እንገነዘባለን፡፡ በጦርነቱ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ አልቋል፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደግሞ የረሃብ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ሕዝቡን እያስተማሩ እና እርምጃ እየወሰዱ ከመለያየት አብሮነት አስፈላጊ መሆኑን ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በመለያየት የሚገኘው ጉዳት ነው፤ በመለያየት አቅምን መበተን እና ለሌላ ውጪ አካል ጣልቃ ገብነት ይዳርጋል፤ ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ መስጠትም ይመጣል፡፡ በአንድ እጅ አይጨበጨብም፡፡

 

ለአብሮነት ፈተና የሆነው ምንድን ነው?

መንግሥት በእውነቱ የሰላም ጥሪዎችን ያደርጋል፤ ስብሰባዎች በሃይማኖት አባቶች እና  በሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በመንግሥት አካለት ይደረጋሉ፡፡ ከአዳራሽ ከተወጣ በኋላ ግን የምክክሩ ሃሳብ ተግባራዊ አይደረግም፡፡ ስለ እውነት በእውነት መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁርአን እንደሚሉት ወንድማማቾች ነን፡፡ ትዕዛዛቱ የሚሉትም አትግደል፣ ወንድምህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፣ አብረህ በሰላም ኑር ነው፡፡ ስለዚህ ተከታታይ የሆነ ትምህርት መሰጠት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእውነቱ የሚነገረውን ይሰማል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ተፈጥሮ የበደላቸው እና ጀብደኛ ሰዎች አሉ፤ እነሱ ይበጠብጣሉ፤ መለያየትን ይሰብካሉ፤ ሕዝቡን ግራ ያጋባሉ፡፡ ዝርዝር ውስጥ ባልገባም ሕዝቡን እያባሉ ያሉ እነሱ ናቸው፡፡ ጦርነት አይጠቅምም፡፡ ችግሮችን በውይይት መፍታት ዋናው አማራጭ ነው፡፡

 

በእኛ ሀገር 86 ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፤ ልዩነታቸው ውበት እንጂ የመጋጫ ምንጭ መሆን የለበትም፡፡ የቻይናው ማኦ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ቻይናን ጎብኝቻለሁ፡፡ ዘረኛ የሆነ ሰው ከተገኘ አንገቱ ይቀላ ነበር፤ ነገር ግን እንደ ሌኒን ሁሉ ማኦም በቅድሚያ በማስተማር ነው የሚያምነው፤ አልሆን ሲል መረር ያለ እርምጃ ይወስዳል፡፡ አንድ አስተማሪ ታሪክ ልናገር፤ በማኦ ጊዜ የለውጥ ሃሳቦችን የሻውሊን ቄሶች (የክርስትና እምነት አይደለም) ለውጡን ተቀበሉ አላቸው እምቢ አሉ፡፡ ያኔ ወደ መግደል አይደለም የገባው፤ ለውጡን ተቀብለው ቁጭ ብሎ ከመዋል ወደ መሥራት ለገቡ ቄሶች ገንዘብ መክፈል ጀመረ፤ የሚሠሩትም ኑሯቸው ተሻሻለ፤ በዚህ ጊዜ የማይሠሩት የሚሠሩትን ተጠቃሚነት አይተው ወደ ሥራ ገቡ፤ የኃይል እርምጃም ሳይወሰድ የሰላም አማራጭን ማኦ ተጠቅሟል፡፡ ስለሆነም ማስተማር እና የሰላም ስልቶችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

 

የወደፊቷን ኢትዮጵያ እንዴት ይስሏታል?

በእኔ እምነት ሀገር ውስጥ ያለው የብሔር ግጭት ይቀራል፤ ይልቁንም ኤርትራ ሳይቀር ወደ ኢትዮጵያ መዋህዷ አይቀርም ብየ አስባለሁ፡፡ ኤርትራ በመለየቷ ያተረፈችው ድህነትን ነው፡፡ ኢሳያስ አፈወርቄም የመንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ፎቶ አውርዶ የራሱን ከመስቀል ውጪ ለኤርትራ ሕዝብ ያደረገው አስተዋጽኦ የለም፡፡ ጤፍ እንኳ የሚገባው ከኢትዮጵያ ነው፡፡ ወጣቱ የሁለቱም ሀገር ትውልድ አንድነት ነው የሚፈልገው፤ አብሮነቱም ወደፊት እውን ይሆናል፡፡ አንድነት ለሁለቱ ሀገር ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ወሳኝ ነው፡፡ የሊቢያው የቀድሞ ፕሬዝደንት ሙአሙር ጋዳፊ አፍሪካ አንድ እንድትሆን በመሥራቱ ነው ለሞት የተዳረገው፡፡

 

የቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ እኛ የተሾምነው ሕዝብን ልናገለግል እንጂ በሕዝብ ልንገለገል አይደለም ብሏል፡፡ አመራሩ በአግባቡ ሕዝቡን ማገልገል አለበት፡፡ ማስተማር እና ሕግን ማስከበር ይገባዋል፡፡ ልማትን ማፋጠን እና ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ከአመራሩ ይጠበቃል፡፡ ወጣቱም የሰላምን አስፈላጊነት መረዳት ያሻዋል፡፡ ለሀገሩ እና ለራሱ እድገት በርትቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ታጣቂዎችም ወደ ሰላም አማራጭ እና ውይይት መምጣት አለባቸው፡፡ በውጪ ያሉት ዳያስፖራዎችም ስለ ሰላም መስበክ አለባቸው፡፡ ከሰላም የበለጠ ነገር የለም፡፡ ግጭት ቆሞ የሀሳብ ልዩነትን በንግግር መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ አይገኝም፡፡

 

ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here