የሃውቲ ትንኮሳ እና ቀይ ባሕር

0
99

አንሳር አላህ (የአላህ ደጋፊዎች) በመባል የሚታወቁት የሃውቲ አማጺ ቡድን አባላት የየመንን ዋና ከተማ ሳንአን ጨምሮ ከሳዑዲ አረቢያ አቅራቢያ የሚገኙ አንዳንድ የምዕራብና የሰሜን አካባቢዎች በቁጥጥራቸው ስር ናቸው፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው የየመን ታጣቂ ቡድን የሆኑት ሃውቲዎች መሠረታቸው ዛይዲስ በመባል የሚታወቀው የሀገሪቱ የሺዓ ሙስሊም ነው። ቡድኑ የየመን ፕሬዚዳንት በነበሩት አሊ አብደላህ ሳሌህ አገዛዝ የተንሰራፋውን ሙስና ለመዋጋት በሚል ነበር እ.አ.አ በ1990ዎቹ የተቋቋመው።

አማጺ ቡድኑ እ.አ.አ በ1990ዎቹ ብቅ ቢልም በ2014 ነበር በየመን መንግሥት ላይ ባመፀበት ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ መታወቅ የጀመረው። ከዚያም ቡድኑ ከኢራን በኩል ድጋፍ በማግኘቱ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራውን ወታደራዊ ጥምረት በመዋጋት ለዓመታት አሳልፏል። ይሁን እንጂ የዛይዲ የሺያ ቡድን እንደ ኢራናዊ ውክልና ተደርጎ መታየት እንደሌለበት ተንታኞች ይናገራሉ። የራሱ መሠረት፣ ፍላጎት እና ምኞት አለው ሲሉም ነው መከራከሪያ የሚያቀርቡት።

የሊባኖሱ አማጺ ቡድን ሄዝቦላህም ለሃውቲ አማጽያን ከአውሮፓዊያኑ 2014 ጀምሮ ሰፊ ወታደራዊ ስልጠናዎችን እየሰጣቸው መሆኑን ሽብርተኝነትን የሚዋጋው ‘ዘ ኮምባቲንግ ቴረሪዚም ሴንተር’ የተሰኘውን የአሜሪካውን የምርምር ተቋም ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

እ.አ.አ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሃማስ  በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ የመልሶ ማጥቃት ርምጃ እየወሰደች ትገኛለች፡፡ ታዲያ እስራኤል በሃማስ ላይ የምታደርገውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ እየተቃወመ   የሚገኘው የሃውቲ አማጺ ቡድን በእስራኤል፣ በቀይ ባሕር፣ በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ዒላማ በማድረግ  ጥቃቶችን እየሰነዘረ ከርሟል።

ባለፈው ዓመት በሃውቲ አማጽያን በቀይ ባሕር ላይ የተፈጠረው የደኅንነት ስጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ በነዳጅ እና በሌሎች ሸቀጦች ላይ  የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ ነው የተነገረው፤  ቀይ ባሕር ከፍጆታ ዕቃዎች በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ እና ጋዝ ምርት መተላለፊያ ነው፡፡

ቀይ ባሕር በሰሜናዊው ጫፍ የስዊዝ ካናል እና በደቡባዊው ባብ  አል – ማንደብ ስትሬት  ጫፍ ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ ይደርሳል። ከእስያ እና ከአውሮፓ ዕቃዎችን ለማምጣት የሱዊዝ ቦይን የሚያቋርጡ መርከቦች የሚጓጓዙበት  የተጨናነቀ የውኃ  መንገድ ነው። 40 በመቶ የሚሆነው የእስያ – አውሮፓ የንግድ ልውውጥ ይካሄድበታል፡፡ ከሰባት እስከ 10 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ እና ፓልም ዘይት፣  የተለያዩ ዕቃዎች እና  የምግብ ምርቶች ያልፉበታል፡፡ በአጠቃላይ 30 በመቶ የሚሆነው የዓለም ኮንቴይነሮች  እና ከአንድ ሚሊዮን በርሜል በላይ ድፍድፍ ዘይት በየቀኑ በስዊዝ ካናል ያልፋል፡፡

ቡድኑ በሚሰነዝረው ጥቃት ምክንያት ታዲያ ዕቃ የጫኑ መርከቦች ወደ እስያ በሚወስደው መንገድ በኬፕ ኦፍ ጉድ በኩል ዞረው ለመሄድ የተገደዱ ሲሆን ይህም ለአውሮፓ፣ አሜሪካ እና ለአንዳንድ የእስያ ኩባንያዎች ወጫቸው 50 በመቶ እንዲጨምር አድርጓል። ይህ ሁኔታም በቀይ ባሕር አካባቢ ለሚገኙ ሀገራት ተፅዕኖው የበለጠ ጉልህ ሆኗል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ የወጭ  እና የገቢ ንግዷን የምታካሂደው  በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው፡፡ ጅቡቲ ደግሞ የቀይ ባሕርን ነው የምትጠቀመው፡፡ በመሆኑም ቀይ ባሕር ላይ የሚደርሰው ችግር ሁሉ ኢትዮጵያ ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴ መጓተት ያስከትላል፡፡ በፍጥነት መድረስ የሚገባቸው ዕቃዎች ባለመድረሳቸው ለተፈለጉበት ዓላማ ሳይወሉ ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ቶሎ ባለመግባታቸው የባሕር ላይ የቆይታ ጊዚያቸው ስለሚጨምር ላልተፈለገ የነዳጅ ፍጆታ ይዳረጋሉ፡፡

በቀይ ባሕር ያለው የጸጥታ ቀውስ በዓመት 12 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን የኢትዮጵያ ጭነት  የሚጓጓዝበትን የጅቡቲ ወደብ አጠቃቀም ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በጥር ወር 2017 ዓ.ም ይዞት በወጣው ጽሑፍ አስነብቧል፤  በቀይ ባሕር የተረጋጋ ነገር አለመኖሩ በወደቡ ተጨማሪ መጓተት መፍጠሩንና በኢትዮጰያ – የጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር የመጓጓዛዣ ወጪ እንዲጨምር ማድረጉን የኢትዮጵያ ሎጅስቲክ ዘርፍ ማሕበራት መግለጹ በጽሑፉ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአማጽያኑ ጥቃቶች ምክንያት በእስያ እና በአውሮፓ አህጉራት መካከል ያለው ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ ተስተጓጉሏል፡፡ የሃውቲዎች ጥቃት ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው ሀገራት ላይ ለተመሠረቱ ላኪዎች ተጨማሪ ወጪዎችን አስከትሏል። ለአብነትም በጥቃቱ ምክንያት መርከቦች እስከ 17 ተጨማሪ ሰዓታትን ለመጓዝ እንደሚገደዱ ነው የሚነሳው፡፡

እ.አ.አ በ2024 በየመን ውስጥ በሚገኙ የሃውቲ ቦታዎች ላይ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ጥቃቶች መቀጠል በጋዛ የተኩስ አቁም ከማስቆም ባለፈ የቀይ ባሕር ጥቃት ሊራዘም ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር። እናም ግምቱ ትክክል ሆኖ አሁን ላይ ቦታው በሚሳኤል የሚታረስ ሆኗል፡፡

አሜሪካና ዐሥራ አንድ አጋሮቿ የየመን ሃውቲዎችን ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው። አሜሪካና አጋሮቿ ሃውቲዎችን ያስጠነቀቁት ከእንግዲህ በመርከቦች ላይ የሚደርስ ጥቃት ካለ የአጸፋ ምላሹ የዋዛ እንደማይሆን በማስገንዘብ ነበር።

አሜሪካ እና እንግሊዝን ያካተተው ጥምር ኀይል በቀይ ባሕር ደኅንነትን ለማስጠበቅ በጋራ እየሠሩ ነበር። ይህ ጥምር ኀይል የሃውቲ አማጺያን በመርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለመከላከል ቢሞክርም ጥቃቱ እንዲቆም አላደረገም፡፡ አሜሪካ ሃውቲ ለሚፈጽማቸው ጥቃቶች ዋንኛዋ ተጠያቂ ኢራን እንደሆነችም ትገልጻለች።

አሜሪካ እና እንግሊዝ በሃውቲ ላይ  የአጸፋ ጥቃት ከጀመሩ በኋላ አማጺ ቡድኑ በማጓጓዣ መርከቦች ላይ የሚያደርሰው ጥቃት ተባብሷል። ታዲያ ጥቃቱን ተከትሎ የመርከቦች ጉዞ የተስተጓጎለ ሲሆን ይህም የዓለምን የገበያ ሰንሰለት አውኮታል። የነዳጅ ዋጋ ሊያሻቅብ የቻለውም ሃውቲዎች ከሚያደርሱት ጥቃት ጋር ተያይዞ አንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡

የዓለም የንግድ መርከብ ኅብረትን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ ባወጣው መረጃ 20 በመቶ የዓለም የንግድ መርከቦች ቀይ ባሕርን እንደመሸጋገሪያ መጠቀም አቁመዋል፡፡ ይህም የሆነው የሃውቲን ጥቃት በመፍራት ነው። መርከቦቹ ቀይ ባሕር አካባቢ ሰላም ባለመሆኑ በደቡብ አፍሪካ ዳርቻ በኩል ዙርያ ጥምጥም ጉዞን ለማድረግ ተገደዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የዕቃ መዘግየትን እያስከተለ ነው።

ሃውቲዎች በዋናነት በባብ አል መንደብ ሰርጥ የሚያልፉ መርከቦችን ዒላማ በማድረግ ነው ጥቃት የሚፈጽሙት። ባብ አል መንደብ በእስያ እና አፍሪካ መሀል ጂቡቲን፣ የመንን እና ኤርትራን የሚነካ የ32 ኪሎ ሜትር የባሕር ክፋይ ነው።

አረብ ሴንተር ዲሲ ዶት ኦርግ (www.arabcenterdc.org) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው የሃውቲ እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ በ2004 የየመንን ዋና ከተማ ሰንዓንን ለመያዝ ጥቃት ከጀመረ በኋላ ቡድኑ በተለይ ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ለጉዳት የማይመች ወይም ለተለመደ ወታደራዊ ጥቃት የተጋለጠ እንዳልሆነ አሳይቷል። የሚጠቀሙበት መሣሪያ ቀላል እና ርካሽ ሲሆን በአሜሪካ የሚመራው የባሕር ኀይል ጥምረት ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች የማይገናኝ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ “የኢራን አመራሮች በሃውቲዎች ለሚተኮሰው ለእያንዳንዱ ሚሳዔል ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው” ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ አስጠንቅቀዋል፡፡

አሜሪካ በየመን ከባድ የአየር ድብደባ ከፈጸመች በኋላ የሃውቲ አማፂያን የአሜሪካ አየር ኀይል ንብረት በሆነው እና በቀይ ባሕር በሚገኘው አውሮፕላን ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ የተደረገ ግዙፍ ባለችው የአየር ጥቃት ከሰሞኑ በአንድ ቀን ብቻ በየመን 30 ዒላማ ያደረገቻቸውን  ቦታዎች  መደብደቧን ነው ያስታወቀችው።

አሜሪካ  ኢራንን ለአማጺ ቡድኑ የገንዘብ፣ የጦር መሣሪያ እና የመረጃ ድጋፍ ታደርጋለች በማለት  መከሰስ ከጀመረች ሰነባብቷል፡፡ ኢራን ግን ክሱን ከእውነት የራቀ በሚል አልተቀበለችውም፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራን ልዑክ ከሰሞኑ በድርጅቱ ለፀጥታው ምክር ቤት በፃፉት ደብዳቤ  የመንግሥታቱ ድርጅት በየመን ላይ የጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የጣሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  ሀገራቸው በቀጣናው ውስጥ አለመረጋጋትን የሚፈጥር ምንም አይነት ተግባር እንደሌላትም አረጋግጠዋል።።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here