ሰላም ልጆች እንዴት ሠነበታችሁ? የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት እንዴት ነበሩ? ጐበዞች! ለጠቅላላ እውቀት እንዲረዳችሁ፣ ‘ሮኬት’ እንዴት እንደሚሰራና ወደ ሰማይ እንደሚመጥቅ እናስነብባችኋለን::
ልጆች የሮኬት አሰራር ከሞላ ጐደል እንደጀት አይሮፕላን ነው::፡ ጄት አይሮፕላን የተጣራ ኬሮሲን ነዳጅን ይጠቀማል:: በሞተሩ አማካኝነት የአካባቢውን አየር እየሳበ ወደ ውስጥ አስተላልፎ ከኬሮሲኑ አቀላቅሎ ሲያቀጣጥለው ውጤቱ ከፍተኛ እምቅታ የሚፈጥር ጋዝ ይሆናል:: ይህ ወደ ኋላ እንዲፈተለክ ሲያደረግ አይሮፕላኑን ወደፊት ይገፋዋል:: ጥይት ወደ ፊት ሲተኮስ ጠመንጃው ወደ ኋላ እንደሚራገጥ ማለት ነው::
የሮኬትን አሰራር ለየት የሚያደርገው መሣሪያው አየር አልባ በሆነው ህዋ ውስጥ እንዲጓዝ የሚጠበቅበት በመሆኑ ከአካባቢው የሚስበው አየር አያገኝም:: ስለዚህ ነዳጁን ኬሚካል ብቻ ሳይሆን አንዳጁን (አቀጣጣይ) ኦክሲጂን ጭምር ይዞ ይነሳል:: ሮኬት በህዋ ሲጓዝ ወይም እንደሳተላይት መሬትን ለመዞር ከፍተኛ ፍጥነት ያስፈልገዋል:: በሰዓት እስከ 28 ሺህ ኪሎ ሜትር እና ከዚያም በላይ ይጓዛል:: እዚያ ፍጥነት ላይ ለመድረስ ደግሞ ብዙ ኃይል ይጠይቃል:: ለዚህ መፍትሔው ሮኬቱን በሦስት ክፍል መሥራት ነው:: የመጀመሪያው ክፍል ሮኬቱን ከመሬት አንቀሳቅሶ በአየሩ ውስጥ እየገፋ እስከተወሰነ ደረጃ በመውጣት አንድ ፍጥነት ላይ ያደርሰዋል:: ከዚያም ተላቆ (ተለያይቶ) ወደ መሬት ተመልሶ ይወድቃል፣ ወይም በአየር ሲወጣ ይቃጠላል:: አሁን ቀሪው መንኮራኩር (ሳተላይት) ክብደቱ ስለሚቀንስለት እና አየሩም ስለሚሳሳ በቀላሉ ይወነጨፋል፡፡ ሁለተኛው ክፍልም እንዲሁ ተግባሩን አከናውኖ ሲላቀቅ ቀሪው የሳተላይት ክፍል በቀላል ክብደት የበለጠ ፍጥነት ሊያገኝ ስለሚችል ወደ ታለመለት ግብ ይደረሳል::
የሮኬት ነዳጅ አብዛኛውን ጊዜ ፈሳሽ ሃይድሮጂን ነው። ሃይድሮጂኑ እና የንዳጅ (አቀጣጣይ) ኦክሲጅን ጐን ለጐን ወይም ላይ እና ታች ተደርገው ብቻ ለብቻ ይያያዛሉ:: ከዚያም በቱቦ አማካኝነት ወደ ማንደጃው ክፍል እየተወሰዱ ሲቀጣጠሉ ዘወትር በሳተላይት ማቃጠያ ጣቢያ በቴሌቪዥን እንደምናየው የተቃጠለው ጋዝ ወደ ታች እየተፈተለከ ሳተላይቱን ወደ ህዋ ያበረዋል:: ይህንን ግፊት እንዲረዳ ወይም እንዲያግዝ በጥጥር ነዳጅ የሚጠቀሙ ትናንሽ ሮኬቶች በሳተላይቱ ግራና ቀኝ ሊጨመሩ ይችላሉ:: ይህ እንደ ፈሳሽ ነዳጅ በቧምቧ ከፋች ዓይነት በመዝጋትና በመክፈት ሊቆጣጠሩት የሚችሉት ዓይነት ስለማይሆን በዘለቄታ ለመጠቀም አስቸጋሪ ነው::
ምንጭ፡- ናሳ
ተረት
ዶሮዋ እና ደሃው
አንድ በድህነት የሚኖር ሰው በጐጆው ውስጥ ዶሮዎችን እያረባ ይኖር ነበር፤ ከዶሮዎቹም የሚገኘውን እንቁላል እየሸጠ ይተዳደር ነበር:: ከዕለታት አንድ ቀን ከሚያረባቸው ዶሮዎች መካከል አንዷ የወርቅ እንቁላል መጣል ጀመረች:: ዶሮዋ የምትጥለውን የወርቅ እንቁላልም በውድ ዋጋ እየሸጠ ሃብታም ሆነ።
ዶሮዋ በየቀኑ አንዳንድ እንቁላል እየጣለች የምትሠጠው ሀብት አልበቃው አለና፣ “ለምን ግን ይህች ዶሮ በቀን አንድ እንቁላል ከመጣል ይልቅ ሁለት እና ሦስት የወርቅ እንቁላል አትጥልም” በማለት ብዙ እንቁላል በቀን እንድትጥልለት ተመኘ:: ለብዙ ጊዜም ዶሮዋን ሁለትና ሦስት እንቁላል እንድትጥልለት ቤት ውስጥ ዘግቶባት ይውል ጀመርር::
ዶሮዋ ግን በቀን አንድ የወርቅ እንቁላል ብቻ ነበር የምትጥለው:: በዚህም አልረካ ያለው ስግብግቡ ሰው ዶሮዋን አርዶ ከሆዷ ውስጥ ያለውን የወርቅ እንቁላል በሙሉ ለመውሰድ አሰበ:: ዶሮዋን አረዳት፤ ሆዷ ውስጥ ግን የወርቅ እንቁላል አልነበረም፤ ይልቁንም በወርቅ እንቁላል ፈንታ ትንንሽ የእንቁላል አስኳል አገኘ:: ስግብግቡም ሰው በአንዴ ለመክበር ሲቸኩል የዘላለም ሀብቱን አጣ::
ምንጭ፡- የኤዞፕ ተረቶች
ይሞአስቴር አስራሁለት ዶሮዎችን ይዛ ወደ ገበያ ሄደች፤ ሁለቱን ስትሸጥ ስንት ይቀራል?
በአፍሪካ ትልቁ ሀገር ማን ነው?
- በዓለም ትንሿ ሀገር ማን ናት? ክሩ
መልስ
ዜሮ
አልጄሪያ
ቫቲካን
ነገር በምሳሌ
- እባብ ያየ በልጥ በረየ፡-
መጥፎ ነገር የደረሰበት ሰው በትንሹ ነገር ሁሉ ይበረግጋል፡፡
- ሥራ ለሠሪው እሾህ ለአጣሪው፡-
ማንኛውም ነገር ለሚመለከተው ከሆነ ውጤት ያመጣል፡፡
- አሳን መብላት በብልሃት፡-
ማንኛውንም ነገር ማድረግ በጥበብ መሆን አለበት፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


