በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሕፃናትን መብቶች የመግፈፍ ተግባራትን ከመፈፀም ህብረተሰቡ ሊቆጠብ እንደሚገባ ተገለፀ።
በሀገራችን የህፃናት የመማር፣ የመኖር እና ጥበቃ የማግኘት መብት በተለያዬ መንገድ ሲገፈፍ ችላ ብሎ መመልከት የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት እና ፍትሃብሔር ሕግ እንደሚፃረር የፍትሕ ቢሮ ፍትሃብሔር ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ ሙሉነሽ ሞገስ ገልፀዋል፡፡
ሕፃናት በአዕምሯቸው፣ በአካላቸው እና በሥነ – ልቦናቸው ያልበሰሉ፣ የማመዛዘን እና ተገቢና ጠቃሚ ውሳኔ የማስተላለፍ አቅም የሌላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። በዚህም የተነሳ ለተለያዩ ችግሮች በቀላሉ ተጋላጭ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ እንደሆነ ነው ባለሙያዋ የገለፁት።
ይህንን ተጋላጭነታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎች ሰዎች ካሏቸው ጥበቃ ባሻገር ተጨማሪ ጥበቃዎችን እና ከለላዎች እና ለህጻናት መስጠት እንደሚያስፈልግ ነው ወ/ሮ ሙሉነሽ የገለፁት።
በተጨማሪም በሀገሪቱ የሕፃናትን መብትና ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚረዱ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎችን በመቀበልና በማጽደቅ የሀገሪቱ የሕግ አካል ቢደረግም ተግባራዊነታቸው ግን ክፍተት ይታይበታል። ለአብነትም ህፃናት የመማር መብታቸው ተጥሶ በየቤቱ በቤት ሠራተኝነት ሲገቡ ራሳቸውን መጠበቅ እና ለመብታቸው መከራከር ስለማይችሉ በደል እየደረሰባቸው ይገኛሉ ነው ያሉት።
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 36 ንኡስ ቁጥር አንድ (ሠ) ላይ ደግሞ ሕፃናት በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካላቸው ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢ – ሰብዓዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን መብት ያላቸው መሆኑን ይደነግጋል። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለውትድርና መመልመልና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለጦርነት ማሰለፍም ወንጀል ነው፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትን መሠረታዊ የህጻናት መብቶች በሀገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ሰነዶች የተቀመጠ ቢሆንም በተግባር እየተሠራበት አይደለም። የህጻናትን ሁለንተናዊ መብቶች በዘላቂነት ለማስጠበቅ በጋራ መትጋት፣ መጠቆም እና ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም