የለውጥ እና ውበት ሙግት  

0
46

በሥነ-ጽሑፍ እና በሥነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ ለዘመናት ሲያከራክር የኖረውና ዛሬም ድረስ መቋጫ ያላገኘው ትልቁ ጥያቄ “ጥበብ ለምን ዓላማ ትኑር?” የሚለው ነው:: ይህ ክርክር በሁለት ዋና ዋና ጎራዎች ይከፈላል:: ጎራዎቹ “ጥበብ ለጥበብ” እና “ጥበብ ለህይወት/ለማህበራዊ ለውጥ” የሚሉት ናቸው::

ጥበብ ለጥበብ/ጥበብ ለጠቢባን በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ በተለይም በፈረንሳይ እና እንግሊዝ ጎልቶ የወጣ እንቅስቃሴ ነው። ጥበብ በራሷ የምትቆም፣ ከፖለቲካ፣ ከሞራል ወይም ከማህበራዊ ትምህርት ነጻ የሆነች መሆን አለባት የሚለው ዋና ሐሳቡ ነው::

የጥበብ ዋናው ግብ ውበት እና የፈጠራ ልቀት ብቻ ነው:: ግጥም ወይም ስዕል ስለ እውነት ወይም ስለ ፍትህ መስበክ የለበትም፤ በቃ ውብ ሆኖ የስሜት እርካታን መስጠት ብቻ ነው የሚጠበቅበት የሚል ሙግት ይቀርብበታል::

ኦስካር ዋይልድ “ዘ ፒክቸር ኦፍ ዶሪያን ግሬይ” በተሰኘው መጽሐፉ  ላይ “ጥበብ ሙሉ በሙሉ ጥቅም የለሽ ነው” ብሏል:: ይህ ማለት ጥበብ እንደ መዶሻ ወይም ማጭድ ተግባራዊ ጥቅም ሊኖራት አይገባም፤ መኖር ያለባት ለራሷ ክብር እና ውበት ብቻ ነው ለማለት ነው::

አሜሪካዊው ደራሲ ኤድጋር አለን ግጥም ዓላማው ውበትን መፍጠር እንጂ እውነትን ማስተማር አይደለም ብሎ ያምን ነበር:: ጥበብ ለጠቢባን የሚለው ሐሳብ ለአርቲስቱ ፍጹም የሆነ የፈጠራ ነጻነት ይሰጣል:: የጥበብን ጥራት እና ውበት (ክብር) ይጠብቃል:: ሰዎች ከጭንቀት እና ከህይወት አስቀያሚ ገጽታዎች አርፈው በመዝናናት መንፈሳዊ እርካታን እንዲያገኙ ይረዳል ተብሎ ይታመንበታል::

ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ/ጥበብ ለህይወት የሚለው አመለካከት ደግሞ “ጥበብ ዝም ብሎ ለቅንጦት ወይም ለመዝናኛ የሚሰራ ነገር አይደለም፤ የህብረተሰብ መስታወትና መሳሪያ ነው” ብሎ ያምና::

አርቲስቱ የህብረተሰቡ አካል እንደመሆኑ በስራው ውስጥ የህዝቡን ብሶት፣ ጭቆና፣ ታሪክ እና ተስፋ ማንጸባረቅ አለበት የሚለው ዋና ማጠንጠኛ ሐሳቡ ነው:: ጥበብ ማስተማር፣ መውቀስ፣ አቅጣጫ ማሳየት እና ለውጥ ማምጣት አለባት ይላል::

ሊዮ ቶልስቶይ “ዋት ኢዝ አርት” በተሰኘው መጽሐፉ ጥበብ ማለት የአንድን ሰው ስሜት ለሌሎች ማጋሪያ እና ሰዎችን ወደ አንድነት ማምጫ መሳሪያ ነው ይላል:: ለህዝብ የማይጠቅም፤ የቅንጦት ጥበብን አጥብቆ ይቃወማል::

ናይጀሪያዊው  “የቲንግስ ፎል አፓርት” ደራሲ ቼኖ አቸቤ  ጥበብ ለጥበብ የሚባለው ሐሳብን በብርቱ ይቃወማል:: አርቲስት አስተማሪ መሆን አለበት ብሎ ያምናል::

የደራሲ በዓሉ ግርማ ኦሮማይ የተሰኘው መጽሐፉ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል:: ጥበብን ተጠቅሞ የነበረውን የፖለቲካ እና የማህበራዊ ውድቀት በማጋለጡ ህይወቱን ጭምር አሳልፎ ሰጥቷል::  ይህም ጥበብ ለለውጥ መሳሪያ መሆኑን ያሳያል::

ጥበብ ለለውጥ ሐሳብ መዋሉ የራሱ የሆኑ ጥቅሞች አሉት:: ማህበራዊ ችግሮችን ያጋልጣል፤ ለውጥን ያነሳሳል፤ ታሪክን እና ባህልን ለትውልድ ያስተላልፋል:: የተጨቆኑ ድምፆች እንዲሰሙ ያደርጋል::

ሁለቱም ዕይታዎች የራሳቸው ምክንያት አላቸው:: ስለዚህም አንዱን ከሌላው ማበላለጥ ወይም ማሳነስ ሚዛን አይደፋም:: አንዱ ከሌላው ይሻላልም ብሎ ለመወሰን  ያስቸግራል:: ምክንያቱም እንደ ዘመኑ እና እንደ ሁኔታው ይወሰናል::

ጥበብ ለለውጥ የሚለው ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሲውል አደገኛ ነው:: ጥበብ ለፖለቲካ ወይም ለርዕዮተ ዓለም ማራመጃ ብቻ ሲውል፤ ውበቱን አጥቶ ወደ ተራ ፕሮፖጋንዳነት ይወርዳል:: ሰዎች መፈክር መስማት ስለሚሰለቻቸው ጥበቡን ይተዉታል::

በአንጻሩ ጥበብ ለጠቢባን የሚለው ዕይታም ከተዛባ ትርጉም ያጣ:: ጥበብ ከሰው ልጅ ህመም እና እውነት ሲርቅ ትርጉም አልባ እና ባዶ ይሆናል:: የቃላት ጨዋታ ብቻ ሆኖ ይቀራል::

ምሁራኑ በሁለት የጥበብ ዓላማ ጎራዎች ለዘመናት ተከራክረዋል። ይህ የሚሆነው ጉዳዩ ትክክል ወይም ስህተት የሚባል የሂሳብ ቀመር ስላልሆነ ነው:: የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሁለት ተቃራኒ ፍላጎቶች አሉት።

በአንድ በኩል፣ ሰው ስሜታዊ ፍጡር ነው:: ውበትን፣ ደስታን፣ መዝናናትን እና ከጭንቀት ማረፍን ይፈልጋል:: ለዚህ ፍላጎቱ ጥበብ ለጠቢባን መልስ ይሰጠዋል::

በሌላ በኩል ሰው ማህበራዊ እና ሞራላዊ ፍጡር ነው:: ፍትህ እንዲሰፍን፣ እውነት እንዲነገር እና ችግሮች እንዲፈቱ ይፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ ጥበብ ለለውጥ  ያስፈልገዋል::

ምሁራን የሚከራከሩት “ከሁለቱ የቱ ይቅደም?” በሚለው ላይ ነው። የሰው ልጅ ሁለቱም ስለሚያስፈልጉት እና  አንዱን መርጦ ሌላውን መጣል ስለማይቻል ክርክሩ ይቀጥላል:: የነጻነት እና ኀላፊነት ግጭት አለ:: ይህ የአርቲስቱ ማንነት ላይ የሚፈጠር ውዝግብ ነው:: የነጻነት ወገኖች (ጥበብ ለጥበብ የሚሉት) “አርቲስት ለአዕምሮው ወይም ለምናቡ እንጂ ለማንም ተጠሪ መሆን የለበትም:: ፖለቲካ ወይም ማህበረሰቡ እንዲህ ካልሰራህ ካለው ያ ባርነት ነው፤ ጥበብ ደግሞ በባርነት ቤት አይሰራም” ይላሉ::

የኀላፊነት ወገኖች (ጥበብ ለለውጥ የሚሉት) “አርቲስት ከሰማይ አልወረደም፤ የሚኖረው በህዝብ ውስጥ ነው:: የህዝብን እንጀራ እየበላ፣ የህዝብን ቋንቋ እየተጠቀመ ለህዝብ ግድ የለኝም ማለት የሞራል ውድቀት ነው:: ነጻነት ያለ ኀላፊነት አይኖርም” ይላሉ::ይህ በግለሰባዊ መብት እና በማህበራዊ ግዴታ መካከል ያለ ዘላለማዊ ግጭት ነው::

ከታሪክ እና ዘመን መቀያየር ጋር አብሮ ክርክሩም ቀጥሏል:: ህዝቡ ሲጠግብ እና ሰላም ሲሆን ጥልቅ ፍልስፍናዎችን ወይም የቅንጦት ውበቶችን ይፈልጋል:: በዚህ ጊዜ  ጥበብ ለጥበብ አሸናፊ ይሆናል::

ህዝቡ ሲራብ፣ ሲገደል ወይም መብቱ ሲነካ፤ ስለ አበባ ውበት የሚያወራ ግጥም ይሰለቸዋል:: ድምፅ ሁነኝ ይላል። በዚህ ጊዜ “ጥበብ ለለውጥ” አሸናፊ ይሆናል::

ታሪክ ራሱን እየደገመ ስለሚመጣ፤ ምሁራንም እንደየዘመኑ ሁኔታ ክርክሩን ያድሱታል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ በ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት “ጥበብ ለህዝብ” የሚለው እሳቤ ገዝፎ ነበር፤ አሁን ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ወደ መዝናኛ ያዘነበለ ጥበብ አለ።

ጥበብ ለለውጥ ይሁን የሚሉ ምሁራን ጥበብ ወደ ፖለቲካ መሳሪያነት እና ወደ ፕሮፖጋንዳ እንዳትቀየር ይሰጋሉ። ሂትለር እና ስታሊን ጥበብን ለርዕዮተ-ዓለማቸው ማራመጃ ተጠቅመውበታል:: አንድ ጥበብ ማስተማር ሲጀምር ስብከት የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። ይህንን ለመከላከል ሲባል ብቻ፤ ሌላኛው ወገን ጥበብ ከፖለቲካ እና ከትምህርት የጸዳች ትሁን ብሎ አጥብቆ ይከራከራል::

ምሁራን የሚከራከሩት አንዱ አላዋቂ ሌላው አዋቂ ስለሆነ አይደለም:: ጥበብ እንደ ሳንቲም ሁለት ገጽ ስላላት ነው::  አንደኛው ገጽ ውበት እና ደስታ ሲሆን ሌላኛው ገጽ እውነት እና ትርጉም ነው::

የሰው ልጅ ሁለቱም ያስፈልጉታል:: ነገር ግን ሁለቱን በአንድ ጊዜ አጣጥሞ ማግኘት ስለሚከብድ፣ አንዱ ወገን ወደ አንዱ ሲያደላ ሌላኛው ይከራከራል::

ስለዚህ ክርክሩ ራሱ ለጥበብ እድገት ጠቃሚ ነው፤ ሁለቱም ወገኖች አንዱ ሌላውን እንዲቆጣጠር  ያደርጉታል የሚሉ አሉ::

ብዙ የዘርፉ ሊቃውንት እንደሚስማሙት  ፍጹም የሆነው ጥበብ ሁለቱን ያጣመረ ነው:: መልዕክቱ ማህበራዊ ለውጥን የሚያልም ሆኖ፤ አቀራረቡ ግን እጅግ የተዋበ እና የጥበብ ለዛውን የጠበቀ ሲሆን ተፅዕኖው ከፍተኛ ይሆናል::

የሐዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ለዚህ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል። ይህ መጽሐፍ በቋንቋ ውበቱ፣ በገለጻው እና በምናቡ ወደር የለውም:: ጥበብ ለጥበብ የሚለውን ያሟላል። በሌላ በኩል ደግሞ የፊውዳሉን ስርዓት ኋላቀርነት፣ የመደብ ልዩነትን እና የሴቶችን ጭቆና አጥብቆ ይተቻል:: ጥበብ ለለውጥ የሚለውን ያሟላል:: ለዚህም ነው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተወዳጅ ሆኖ የዘለቀው::

አንድ ሰዓሊ የሳለው ስዕል የአበባ ምስል ከሆነና ውበቱ አይን የሚማርክ ከሆነ፤ ያ ለተመልካቹ የአእምሮ እረፍት በመስጠቱ ብቻ ጥቅሙ ጥበብ ለጠቢባን ይሆናል:: ያው ሰዓሊ ግን የተራቡ ህጻናትን ስዕል በኪነ-ጥበባዊ መንገድ ከሳለ፤ ተመልካቹን ወደ መፍትሄ ስለሚገፋ “ጥበብ ለለውጥ” ይሆናል። ሁለቱም ለሰው ልጅ ያስፈልጋሉ::

ማረፊያ

ኀዘንሽ አመመኝ

ውል አልነበረንም የፍቅር ቀጠሮ

ቃልም አላኖርንም በወግ ተቀምሮ፤

እኔ አንቺን እንዳላይ

አንቺ እኔን እንዳታይ አምባችን ተቃጽሮ

ዕጣችን ተካሮ፤

ቀለምሽ ከዐይኔ አሻራሽ ከጣቴ ባይጠፋ ተማትሮ

(እትብት እምብርት ሁኖ እንዲኖር ደድሮ)

ይኸው አካሄደን በድንገት ዘንድሮ፡፡

የገጽሽ ብርሃን ቢጠይም ፀዳሉ

ድምፅሽ ቢቀጥንብኝ ቢሠልብኝ ቃሉ

ወዘናሽ ቢማስን ዛሬ ያለውሉ

በእጆችሽ ጨበጠኝ ኀዘንሽ ሥዕሉ

ኀዘንሽ አመመኝ

ብሶትሽ ጠቀሰኝ፡፡

ጀንበር ነሽ አበባ ሕይወት ተስፋ ዘቦ

ፋሲካ ዕንቁጣጣሽ ማኅሌተ ገንቦ

ብዬ ያወደስኩበት ታዘበኝ ዘመኔ የትላንታት ቀኔ

ዛሬ ሊጮህብኝ ቅኔ እንዳይደል እውኔ፤

ኀዘንሽ አመመኝ

ብሶትሽ ጠቀሰኝ፡፡

የገደል ማሚቶን ታዘብኳት ተኝታ

በጩኽትሽ ማየል አኩርፋና ታክታ

ላንቃዋ ይታየኛል ደም ለብሶ ደም ጐርሶ

ቃልሽ ያለፈበት በጭንቅ ተለውሶ፤

ኀዘንሽ አመመኝ

ብሶትሽ ጠቀሰኝ፡፡

ጽጌሬዳይቱ ንቦችሽ አለቁ ሰዎችሽ ደቀቁ

ጨፌ ላይ ተኝተው ባድማ ላይ ነቁ፤

ዐዋይን ሰማኋት ስታለቅስ በይፋ

ከጐጆሽ ስትወጣ ትቢያዋን አራግፋ፤

ኀዘንሽ አመመኝ

ብሶትሽ ጠቀሰኝ፡፡

አላውቅልሽ ብዬ አታውቂልኝ ብዬ

እምነትሽን ጥዬ ፍቅርሽን ገድዬ

አኩርፌሽ ስቀመጥ ያው እንደ ባላንጣ

ይኸው ነጭ ማተብሽ ሊያስታርቀን መጣ፤

ኀዘን ነው ውበትሽ ውበት ነው ፍቅርሽ

ብርሃን ጥለት አልቦ ከል ነጠላሽ

ዐይኔን የገለጠው ጥቁር ጨለማሽ፤

ኀዘንሽ አመመኝ

ብሶትሽ ጠቀሰኝ፡፡

 

ግንቦት 1966ዓ.ም

ደበበ

ሰይፉ

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የህዳር  29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here