የሉዝ ጦርነት

0
14

የአለማችን ሀገራት በተናጠልም ሆነ በህብረት እጅግ መራራ እና አስከፊ የሚባሉ ጦርነቶችን አካሂደዋል::

በእነዚህ የጦርነት አውድማዎች ምክንያት እጅግ በርካታ የሆኑ ሰዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለስደት እና ለጉስቁልና ተዳርገዋል::ከፍተኛ የሆነ ሀብትና ንብረትም ወድሟል::

በዓለማችን ከተናጠል ባለፈ በሁለት ጐራ ተከፍለው እጅግ ከባድና አሰቃቂ የሚባል ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉት ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ1914 እስከ 1918 ነበር::

ይህ ጦርነት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የዓለማችን ሀያል የነበሩት የአውሮፓ ሀገራት በሁለት ጐራ ተከፈሉ:: ጀርመን፣አውስትሮ-ሀንጋሪ እና ጣሊያን “ትሪፕል ኢንቴንት” በሚል ቡድን፤ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ ደግሞ “ትሪፕል አሊያንስ” በሚል ቡድን ነበር በሁለት ጐራ የተከፈሉት::

ሀያላኑ የአውሮፓ አገራት በሁለት ጐራ ተከፍለው (ቆይቶ ሁለቱንም ጐራ ሌሎች አገራት ተቀላቅለዋል) እ.ኤ.አ. ከ1914 እስከ 1918 ያደረጉት እጅግ ከባድና አሰቃቂ ጦርነት የአንደኛው የአለም ጦርነት ተብሎ በታሪክ መዝገብ ሰፍሮ እንደሚገኝ የሂስትሪ ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል::

ታዲያ በዚህ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እጅግ ዘግናኝ ጦርነቶች በተለያዩ የጦርነት አውድማዎች ተካሂደዋል::

ከነዚህ መካከል የሉዝ ጦርነት አንዱ ነው::

ታዲያ እኔም ለዛሬ ስለ ሉዝ ጦርነት በመጠኑ ላስነብባችሁ ወድጃለሁ::ሉዝ ሎንስ ከተባለችው የፈረንሳይ ከተማ አቅራቢያ የምትገኝ ከተማ ናት::

ይህች ከተማ የአንደኛው የዓለም ጦርነት ከሚካሄድባቸው አራቱም አቅጣጫዎች በምእራቡ ቀጣና ትገኛለች:: በዚህ በምእራቡ ቀጣና የጀርመን ጦር በአንድ ጎን የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ጦር ደግሞ በሌላ ጐን ተፋጠው ይገኙበት ነበር::

በአንደኛው የአለም ጦርነት ወቅት ከጅምሩ አንስቶ የጀርመን እና የአጋሮቿ የሀይል ሚዛን አይሎ ከምዕራቡም ከምስራቁም አቅጣጫ ድሎችን በመቀዳጀት በርከት ያሉ አካባቢዎችን በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ችለው ነበር::

በዚህ ሁኔታ ስጋት እና ቁጭት ያደረባቸው እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በሉዝ ጦርነት የጀርመንን ጦር ድባቅ ለመምታት እና ድል ለማስመዝገብ ወሰኑ::

በጀርመን ላይ ወሳኝ ድል ለማስመዝገብ ቆርጠው ሲዘጋጁ የከረሙት እንግሊዝና ፈረንሳይ እ.ኤ.አ. መስከረም 1915 አካባቢ በጠንካራ ምሽግ ውስጥ በሚገኘው የጀርመን ጦር ላይ ከፍተኛ የሆነ የማጥቃት ዘመቻ መጀመራቸውን የሂስትሪ ለርኒንግ ሳይት ዶት ኮም ዶት ዩኬ ድረ ገጽ መረጃ ያመለክታል::

የማጥቃት ዘመቻው የተጀመረው ጠንካራውን የጀርመን ምሽግ ለማፈራረስ በከባድ መሳሪያ ድብደባ ነበር::

በወቅቱ የእንግሊዝ ጦር አዛዥ የነበሩት ዳግላስ ሄግ ሲሆኑ የፈረንሳይን ጦር ደግሞ ጆሴፍ ጆፈሪ ይመሩት ነበር::በእነዚህ ሰዎች አዛዥነት የሚመራው የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ጦር እ.ኤ.አ. መስከረም 25/1915 የከባድ መሳሪያ ድብደባውን ጀመረ::

ለአራት ቀናት በቆየው በዚህ የከባድ መሳሪያ ድብደባ 250 ሺህ የሚደርሱ የከባድ መሳሪያ አረሮች ወደ ጀርመኖች ጠንካራ ምሽግ ተተኩሰዋል:: ይህ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ብዙም ውጤታማ ባለመሆኑ እ.ኤ.አ. ከመስከረም 28/1915 በኋላ እንዲቆም ተደረገ::

የከባድ መሳሪያ ድብደባው እንዲቆም የተደረገው ውጤታማ ባለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የከባድ መሳሪያ አረሮች እጥረት በመኖሩም ጭምር ነበር::

የአንደኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በተለይም እ.ኤ.አ. በ1915 የትሪፕል አሊያንስ ጦር (የህብረቱ ጦር) ድል አልቀናውም ነበር::

ከከባድ መሳሪያ ድብደባው ባሻገር በሰው ሀይል ቁጥር የበላይነት የነበራቸው የእንግሊዝና ፈረንሳይ ወታደሮች ይህ መሆኑ ለድል እንደሚያበቃቸው በመገመትም ነበር ድል ለማግኘት ተስፋ ያደረጉት::

የፈረንሳይ ጦር በተቃራኒው ከተሰለፈው የጀርመን ጦር ጋር ሲነፃፀር ሶስት ለአንድ ሲሆን የእንግሊዝ ጦር ከጀርመን ጦር ጋር ሲወዳደር ሰባት ለአንድ የሆነ ብልጫ እንደነበራቸው ፈርስት ወርልድ ዋርዶት ኮም የተባለው ድረ ገጽ አስነብቧል::

በከፍተኛ የወታደር ቁጥር ብልጫ ይዘው በከባድ መሳሪያ ድብደባ የጀርመን ጦርን ምሽግ ንደው ለመግባት ሙከራ ያደረጉት የእንግሊዝና የፈረንሳይ የጦር ሀይሎች ያሰቡትን ማሳካት አልቻሉም::

በመሆኑም የእንግሊዝ ጦር ሌላ አማራጭ እንዲጠቀም አዛዡ ዳግላስ ሄግስ ወሰኑ:: ይህ አዲስ አማራጭ ደግሞ አስደንጋጭና አረመኔያዊ ነበር:: በዚህ ውሳኔ መሰረት የእንግሊዝ ጦር የጋዝ መርዝ ወደ ጀርመን ምሽግ መተኮስ ነበር::

የእንግሊዝ ጦር በውሳኔው መሰረት አምስት ሺህ 100 የጋዝ መርዝ የያዙ ሲሊንደሮችን ወደ ጀርመን ምሽግ ተኮሱ::ይህ  ወደ ጀርመን ምሽግ የተተኮሰው ክሎሪን የተባለው የመርዝ ጋዝ ክብደቱ 140 ቶን የሚመዝን እንደነበረም መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ይህ ጋዝ በጀርመን ጦር በወቅቱ ይለበሱ የነበሩ የመርዝ ጋዝ መከላከያ ጭንብሎች እንዳይቋቋሙት ተደርጐ የተዘጋጀ ነበር::

እንግሊዞች የጀርመንን ጦር ለማውደም እና የሉዝ ከተማን ለመቆጣጠር የለቀቁት የመርዝ ጋዝ ጉዳቱ በጀርመን ጦር ላይ ብቻ አልነበረም:: ይልቁንም‹ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ ባፉ› እንደሚባለው የአገራችን አባባል የመርዝ ጋዙ በነፋስ አማካኝነት ወደ እንግሊዞች ምሽግ በመድረሱ ሁለት ሺህ 632 የእንግሊዝ ጦር አባላትን ለጉዳት ዳርጓል:: ከነዚህ መካከል ሰባቱ ለሞት ተዳርገዋል::

የእንግሊዝ ጦር በዚህ ጥቃት መሰረት የጀርመንን ጦር በማዳከም ወደ ፊት መገስገስ ችሎ ነበር:: ይሁን እንጂ ጀርመኖች ተጨማሪ ሀይል በማስመጣት መልሶ ማጥቃት ጀመሩ:: የእንግሊዝ ጦር ሊገታ የቻለው ጀርመኖች ካገኙት ድጋፍ ባሻገር ወደ ጀርመን የጦር ሰፈር  ይጓዙ የነበሩት ያለከባድ መሳሪያ ድጋፍ በመሆኑም ጭምር ነበር:: በዚህም የተነሳ ጀርመኖች ምንም አይነት ሽፋን ያልነበራቸውን የእንግሊዝ ወታደሮች እንደ መትረየስ ባሉ የቡድን መሳሪያዎች ከባድ ጥቃት አደረሱባቸው::

ጦሩ ከባድ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን የተመለከቱት የእንግሊዝ ጦር አዛዥ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ትእዛዝ አስተላለፉ:: ጥቃት ከማድረስ እንዲያፈገፍጉ የተደረጉት የእንግሊዝ ወታደሮች እንደገና ራሳቸውን ማደራጀት ጀመሩ::

ራሳቸውን ካደራጁ በኋላ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 13/1915 አዲስ ጥቃት ከፈቱ:: ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜም ከባድ ጉዳት ከመድረሱም በተጨማሪ አስቸጋሪ በሆነው አየር ሁኔታ ምክንያት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙ ተደረገ::

የሉዝ ከተማን ከጀርመኖች እጅ ለመንጠቅ መጠነ ሰፊ እና ከባድ ጥቃት በተደጋጋሚ የከፈቱት የእንግሊዝ የጦር ሀይል ያሰበውን ማሳካት ሳይችል ቀረ::በዚህ ያልተሳካ ጦርነት እንግሊዞች 50 ሺህ ጦር ለሞትና ለጉዳት ተዳርጐባቸዋል::በአንፃሩ የዚህ አሃዝ ግማሽ የሚሆኑት ጀርመኖች ለተመሳሳይ ጉዳት ተዳርገዋል::

በእንግሊዞች ላይ ከባድ ጉዳት ሲደርስ ጦሩን የመሩት ዳግላስ ሄግ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸውንም የፈርስት ወርልድ ዋር ዶት ኮም መረጃ ይጠቁማል::

 

ሳምንቱ በታሪክ

የአልጀሪያውያን መገደል

እ.አ.አ በ1961 የፈረንሳይ ፖሊስ በፓሪስ ጎዳናዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አልጄሪያውያንን ገደለ፡፡ ተጎጂዎቹ በአገራቸው የፈረንሳይ ቅኝ ገዥዎችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ፡፡ ከ10,000 የሚበልጡ ሰዎች ታስርዋል፣ አንዳንዶቹ በእስር ላይ እያሉ ሞተዋል፡፡ እ.አ.አ በ1962 አልጄሪያ ከ100 ዓመታት በላይ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት በኋላ ነፃ ሀገር ሆነች፡፡

 

በናዚ መሪዎች ላይ  ክስ እና ፍርድ

ኦክቶበር 18/1685- የኑረምበርግ የጦርነት ወንጀሎች ችሎት  ኽርማን ጎሪንግ እና አልበርት ስፐርን ጨምሮ በ24 የቀድሞ የናዚ መሪዎች ላይ ክስ በማቅረብ ተጀመረ፡፡ የፍርድ ሂደቱ ለ10 ወራት የፈጀ ሲሆን ፍርዱ በጥቅምት 1/1948 ተጠናቀቀ፡፡ 12 ናዚዎች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በሞት እንዲቀጡ፣ ሶስት የዕድሜ ልክ እስራት እና ሦስቱ በነፃ ተለቀቁ፡፡

(አዲሱ አያሌው)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here