ውብ፣ ሀብታም፣ ለኑሮ ምቹ እና የደስተኞች ሀገር ናት፡፡ በሚገርም ሁኔታ በሰሜናዊው ግዛቷ ፀሐይ ለስድስት ወራት አትጠልቅም፡፡ በዚህም በእኩለ ሌሊት ፀሐይ የሚወጣባት ሀገር እያሉ ይጠሯታል፡፡
አንዳንድ ሀገራት የተፈጥሮ ሀብት በገፍ ይታደላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የሰለጠነ የሰው ሀብት ይኖራቸዋል፡፡ ይህች ሀገር ግን የተፈጥሮ ሀብት፤ ከተማረ የሰው ኃይል ጋር አጣምራ የያዘች የምድር ገነት ናት ማለት ይቻላል ሲል ዎርልድ ትራቭለርስ ሪካርተን የተሰኘ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡ በዛሬው ሽርሽራችን የሰሜን አውሮፓዋን ኖርዌይን እናስጎብኛችሁ፡፡ ኖርዌይ ዋና ከተማዋ ኦስሎ ትባላለች፡፡
አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯም አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ነው፡፡ የቆዳ ስፋቷ 385‚207 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የኖርዌይ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ከ500 ቢለዮን ዶላር በላይ ነው፤ በዚህም ከዓለም ስድስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ የነፍስ ወከፍ ገቢዋም 90 ሺህ ዶላር ገደማ ነው፡፡
ኖርዌይ የነዳጅ ሀብቷ አጃኢብ የሚያስብል ነው፤ የነዳጅ ክምችቱም የሚገኘው ከባሕር በታች ነው፡፡ ይህ የነዳጅ ክምችት መኖሩ የታወቀው በ1960ዎቹ ነበር፤ በወቅቱ ኖሮዌያዊያን የነዳጅ መጠኑን በውል አያውቁትም ነበር፤ ለማውጣትም የተማረ የሰው ኃይል እና አቅሙ አልነበራቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ 50 በመቶ ድርሻ ለስዊድን መንግሥት በመስጠት እንዲያወጡላቸው ሙከራ አድርገው ነበር፤ በምትኩ ደግሞ ስዊድን ቮልቮ ከተሰኘው ግዙፍ መኪና ማምረቻ ፋብሪካ 50 በመቶ ድርሻ ለኖርዌይ እንድትሰጥ ጠየቁ፡፡
ስዊድናዊያን የቮልቮን 50 በመቶ ድርሻ መስጠት ስላልፈለጉ ጥያቄውን ውድቅ አደረጉ፡፡ የኋላ ኋላ ኖርዌ በራሷ ዜጎች ሀብቷን አውጥታ መጠቀም ችላለች፡፡ አሁን ይህን ሀብታቸውን በጥንቃቄ መጪውን ትውልድ ሳይቀር ታሳቢ በማድረግ ነው የሚጠቀሙት፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1970ዎቹ ነበር ኖርዌይ ነዳጅ ማውጣት የጀመረችው፡፡
ከነዳጅ የሚገኘው ገቢ እ.አ.አ በ1990 በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምር ለቀጣዩ ትውልድ ከነዳጅ ከሚገኘው ገንዘብ ተቆጥቦ መቀመጥ እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ ወጣ፡፡ ነዳጅ እየሸጠች ለቀጣይ ትውልድ የቆጠበችው ገንዘብ አንድ ነጥብ አራት ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን የኖርዌይ ኢንቨስትመንት ባንክ አስታውቋል፡፡ ይህ ባንክ የተመሠረተውም ገንዘቡ በሀገሪቱ ተሰራጭቶ የዋጋ ማናር እና የገንዘብ ዋጋ መውደቅ እንዳያጋጥም ሲሆን ችግሩንም ለመፍታት ገንዘቡ በውጪ ሀገራት ባሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ፈሰስ ይደረጋል፡፡ ከተጠራቀመው ገንዘብ 70 በመቶው ኢንቨስት የተደረገው በውጪ ሀገራት ነው፡፡
ኖርዌይ ከአውሮፓ ሁለተኛ፤ በመላው ዓለም ደግሞ 11ኛዋ ነዳጅ አምራች ሀገር ናት፡፡ ከነዳጅ ሀብቷ ባሻገር የነዳጅ ሀብት አጠቃቀሟ እጅግ ተደናቂ ነው፡፡ ኖርዌይ እንደ አብዛኞቹ መካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ አምራች ሀገራት ሀብቷን አታባክንም፡፡ ነዳጅ በምታመርትበት ጊዜ በተመጠነ መንገድ ሲሆን ከመጠን በላይ አውጥቶ በነዳጅ መስከር የሚሉት እሳቤ በሀገሪቱ የለም፡፡ መሪዎቿም ሆነ የተማሩት ዜጎቿ በዚህ ድርድር የላቸውም፡፡ ከነዳጅ የሚገኝ ገቢ ዘላለማዊ እንዳልሆነ ስለሚያውቁ ኢኮኖሚያቸው በነዳጅ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዳይሆን ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል፡፡
ኖርዌይ በምትገኝበት ሥፍራ ከ11 ሺህ ዓመታት ጀምሮ ሰዎች ይኖሩበት እንደነበር የታሪክ ተመራማሪዎች ይጠቅሳሉ፡፡ የኖርዌይ ታሪክ በደንብ የሚታወቀው ግን በቫይኪንጎች ዘመን ነው፡፡ ቫይኪንጎች ወደ እንግሊዝ እና ሌሎች ሀገራት በመንቀሳቀስ ወረራ ሲፈጽሙ የነበሩ ኃይለኛ ሕዝብ ናቸው፡፡ ከቫይኪንጎች በኋላ ኖርዌይ በስዊድን ስር ተካታ ነበር፤ በኋላም ሩሲያዊያን በወረራ ይዘዋት ቆይተዋል፡፡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1905 ነጻነቷን አግኝታ ራሷን ችላ ቆመች፡፡
ውብ ሸለቆዎቿ፣ ከሰማይ የሚወርዱ የሚመስሉት ረጃጅም ፏፏቴዎቿ እና ሰማይን ደግፈው የያዙ የሚመስሉት ትላልቅ የድንጋይ ተራራዎቿ ለኖርዌይ መለያዎቿ ሲሆኑ ከፍተኛ ውበትንም አላብሰዋታል፡፡ ዜጎቿ ጥሩ ኑሮ የሚኖሩባት፣ ለዜጎቿ ሀብቷን እኩል የምታከፋፍል እና እጅግ አነስተኛ የወንጀል መጠን ያለባት፣ የሥራ አጥ ቁጥር ጥቂት የሆነባት ሀገር ናት፡፡ ኖርዌይ ከዓለማችን ደስተኛ ሕዝብ ካላቸው ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች፤ ለሕጻናት፣ ለሴቶች እና አረጋዊን ምቹ ከሚባሉት ሀገራትም አንዷ ናት፡፡ ሕጻናት የተሻለ አስተዳደግ ትምህርት እና እንክብካቤ አግኝተው የሚያድጉባት ናት፡፡ አረጋዊያንም አገልግሎታችሁ አልቋል ተብለው የሚጣሉባት አይደለችም፤ ይልቁንም በስርዓቱ ተከብረው ይጦራሉ፡፡ ሴቶችም በእኛ ሀገር አሁንስ በዛ እስኪባል ድረስ መብት ተጎናጽፈዋል፡፡
የኖርዌይ ዜጎች በዓለም ቡና ይወዳሉ ከሚባሉት ውስጥ ናቸው፡፡ አንድ ኖሮዌያዊ በቀን በአማካኝ አምስት ሲኒ ቡና ይጠጣል፤ የፊላንድ እና የሉግዘምበርግ ዜጎች ብቻ ናቸው ቡና በመጠጣት የሚበልጧቸው ሲል የቡና ጠጪዎች መዲና ሲል ባወጣው ጽሑፍ ጀርመን ድምጽ አንድ ጥናትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ቡና ታስገባለች፤ ለሕዝቧ ደስተኛነት የኢትዮጵያ ቡና አስተዋጽኦ ሳይኖረው አይቀርም፡፡
ኖርዌይ እጅግ ቀዝቃዛ ከሚባሉት ሀገራት ውስጥ ናት፤ ይህ ቅዝቃዜዋ ግን እንደኛ ዓመቱን በሙሉ ፀሐይ ከሚወጣባቸው ሀገራት ለመጡ ሰዎች ከባድ ነው፡፡ ወደ ሰሜን ከፍ እያሉ በሄዱ ቁጥር ከዜሮ በታች 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል፡፡ ሀገሪቷን ለማየት ከታደሉ ሰዎች ውስጥ ከቅዝቃዜዋ በስተቀር ኖርዌይ ለኑሮ ምቹ ሀገር መሆኗን ይናገራሉ፡፡ ኖሮዌያዊያን ግን ይህን ቅዝቃዜ ይወዱታል፡፡ ከተወለዱ ሁለት ሳምንት የሞላቸውን ሕጻናት ሳይቀር በሀይለኛ ቅዝቃዜ ከውጪ አውጥተው ያስተኟቸዋል፡፡ ቅዝቃዜ በሽታ የመከላከል ኃይልን ይጨምራል፤ በበሽታ ከተያዙም የትኛውንም በሽታ ይፈውሳል ይላሉ፡፡ ሕጻናትም በቅዝቀዜ ንጹህ አየር እንዲያገኙ እና ሳያቆራርጡ ረዥም ሰዓት መተኛት እንደሚችሉም ይናገራሉ፡፡
ኖርዌያዊያን በአፍሪካዊያን እና በሌሎች ሕዝብ ዘንድ ኃይለኛ እና አደገኛ የሚባልን ተፈጥሮ እንዴት ወደ ገንዘብ መቀየር እንደሚችሉ ያውቃሉ፡፡ ለአብነት ሰሜናዊ ለንደን ውስጥ በሚገኝ ኪርከን መንደር ውስጥ አንድ ሆቴል አለ፡፡ ሆቴሉ ጎብኝዎች የሚያርፉበት ሲሆን ሙሉ በሙሉ ከበረዶ ነው የተሠራው፡፡ በሆቴሉ ካንሶላ እና ብርድልብስ ውጪ ሁሉም ነገር ከግግር በረዶ የተሠራ ነው፡፡ መጸዳጃ ቤቱ ሳይቀር ከበረዶ የተሠራ ነው፡፡ “ሁሉም አካባቢዎች የየራሳቸው የተፈጥሮ ሀብት አላቸው። እኛ ደግሞ በረዶ አንዱ የታደልነው ሀብት ነው” ሲሉ ኖሮዌያዊያን በረዶ እንደ ነዳጅ እና ወርቅ ያለ ሀብታቸው እንደሆነ ሁሉ ይኮራሉ፡፡
ኖርዌይ መታረስ የሚችለው መሬቷ ከአጠቃላይ ስፋቷ ሁለት ነጥብ ሁለት ከመቶ ብቻ ነው፡፡ ሀገሪቷ 83 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ዳርቻ አላት፡፡ ይህም ከአውሮፓ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ከካናዳ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሀገር ያደርጋታል፡፡ ኖርዌይ በሸለቆ ውስጥ በሚፈሱ ወንዞቿ ትታወቃለች፡፡ የንጹህ የመጠጥ ውኃ ሀብቷም ከፍተኛ ነው፡፡
ኖርዌይ መልከዓ ምድሯ መንገዶችን እና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ ከፍተኛ ጥራት ባላቸው መንገዶቿ እና መሠረተ ልማቶቿ ነው የምትታወቀው፡፡ በምድር፣ በየብስ እና በውኃ የተሟላ የመጓጓዣ ሥርዓት ዘርግታለች፡፡ ሀገር አቋራጭ ጉዞን የሚያሳጥር የጥልቅ ውቅያኖስ ዋሻ መንገድም እየገነባች ነው፤ ይህ መንገድ እስከ ስድስት ሰዓት የሚወስደውን ጉዞ ወደ 40 ደቂቃ ዝቅ ያደርጋል፡፡ በኖርዌይ የኤሌክትሪክ መኪናዎች በስፋት ይገኛሉ፤ በሀገሪቱ 94 ከመቶ የሚሆኑት መኪኖች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህም ከፍተኛ የነዳጅ አምራች ሀገር ሆና ለምን የኤሌክትሪክ መኪና በስፋት ትጠቀማለች? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ምክንያቱ ኖርዌይ ከፍተኛ የበረዶ ግግር በሚገኝበት ሰሜን ንፍቀ ክበብ ነው የምትገኘው፡፡ ከነዳጅ የሚወጣው በካይ ጋዝ ይህን ግግር በረዶ አቅልጦ ወደ ውቂያኖስነት ይቀይረዋል፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ኖርዌይ ያሉ በሰሜን ንፍቀ ክበብ የሚገኙ ሀገራትን ጠራርጎ ያጠፋል፡፡ ስለዚህ ኖርዌይ ለርካሽ የነዳጅ ትርፍ ስትል ህልውናዋን አደጋ ላይ ላለመጣል እና ራሷን ለማትርፍ የአየር ንብረት ብክለትን ትከላከላለች፡፡ በቅርቡም መቶ በመቶ ኤሌክትሪክ መኪኖችን ለመጠቀም አቅዳለች፡፡
ኖርዌይ እ.አ.አ በ2019 በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የጉዞ እና የቱሪዝም ተወዳዳሪነት ሪፖርት መሠረት በመጎብኘት 20ኛ ሆናለች። በኖርዌይ የቱሪዝም ዘርፉ እ.አ.አ በ2016 ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አራት ነጥብ ሁለት በመቶ አስተዋፅኦ አድርጓል። በመላ ሀገሪቱ ከ15 ሰዎች ውስጥ አንዱ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ይሠራል። ከጠቅላላ ጎብኝዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በግንቦት እና ነሐሴ ወራት መካከል ይጎበኛሉ። የኖርዌይ ዋና ዋና መስህቦች በአርክቲክ ክበብ ውስጥ የተዘረጉ የተለያዩ መልክዓ ምድሮች ናቸው።
በባህር ዳርቻዋ እና በተራሮቿ፣ በበረዶ መንሸራተቻዎቿ፣ በሐይቆቿ እና በጫካዎቿ ታዋቂ ናት። በኖርዌይ ውስጥ ታዋቂ የሆኑ የጎብኝ መዳረሻዎች ኦስሎ፣ አሌሱድ፣ በርገን፣ ስታቫንገር፣ ትሮንድሄም፣ ክርስቲያንሳንድ፣ አሬንዳል፣ ትሮምሶ፣ ፍሬድሪክስታድ እና ቶንስበርግ ያካትታሉ። አብዛኛው የኖርዌይ ተፈጥሮ በሰው ሠራሽ ሁኔታ የተጎዳ አይደለም፤ በደንብ የተጠበቀ ነው፤ ይህም ብዙ ተጓዦችን እና የበረዶ ተንሸራታቾችን ይስባል። በምዕራብ ኖርዌይ እና ሰሜናዊ ኖርዌይ የሚገኙት ተራሮች እና ፏፏቴዎች በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ጎብኝዎችን ይስባሉ። በከተሞች ውስጥ እንደ ሆልመንኮለን የበረዶ ሸርተቴ ዝላይ እና በቶንስበርግ ሳጋ ኦሴበርግ ያሉ ባሕላዊ እሴቶች ብዙ ጎብኝዎችን ይስባሉ፡፡ የኖርዌይ ጉብኝታችንን በዚሁ አበቃን፡፡፡፡
አጭር እውነታ
ኖርዌይ
ኖርዌይ ዋና ከተማዋ ኦስሎ ትባላለች፡፡
የሕዝብ ቁጥሯ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ነው፡፡
የቆዳ ስፋቷ 385‚207 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፡፡
የኖርዌይ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ከ500 ቢለዮን ዶላር በላይ ነው፡፡
የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 90 ሺህ ዶላር ገደማ ነው፡፡
ኖርዌይ ከአውሮፓ ሁለተኛ፤ በመላው ዓለም ደግሞ 11ኛዋ ነዳጅ አምራች ሀገር ናት፡፡
የኖርዌይ ታሪክ በደንብ የሚታወቀው ግን በቫይኪንጎች ዘመን ነው፡፡
ቫይኪንጎች ወደ እንግሊዝ እና ሌሎች ሀገራት በመንቀሳቀስ ወረራ ሲፈጽሙ የነበሩ ኃይለኛ ሕዝብ
ናቸው፡፡
ኖርዌይ ከዓለማችን ደስተኛ ሕዝብ ካላቸው ሀገራት በቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች፡፡
የኖርዌይ ዜጎች በዓለም ቡና ይወዳሉ ከሚባሉት ውስጥ ናቸው፡፡
ኖርዌይ እጅግ ቀዝቃዛ ከሚባሉት ሀገራት ውስጥ ናት፡፡
ኖርዌይ መታረስ የሚችለው መሬቷ ከአጠቃላይ ስፋቷ ሁለት ነጥብ ሁለት ከመቶ ብቻ ነው፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም