ካለፈው የቀጠለ
ልጅነት የበርካታ ትዝታዎች ስንቅ ነው፤ እየተመነዘረ የሚኖሩት፥ ለመናገር ብዙ የማይመች። የልጅነት ሌላኛው ገጹ አብሮነት እና መልካምነት፣ የዋህነት ነው። የዋህነቶቹ ብዙ ናቸው፥ ለዝርዝር ዘለግ የሚሉ። እስኪ ከአቡሻ ጋር ትናንትን ተጋርተን ትዝታወቹን እናንሳ።
አቡሻ የደስደስ ያለው ፀጉረ ሉጫ ህንድ መሳይ ልጅ ነው። ሲያወራ አፍ አፉን የሚታይ ምነው ንግግሩን ባልጨረሰ የሚባልለት ተናፋቂ ባለወግ ልጅ ነው። ትምህርት ቤት ለመግባት የነበረው ጉጉት “የቸር ያድርግልህ” የሚባል ዓይነት ነበር። በትእግስት ከጠበቁት የማይደርስ የለም ጊዜው ደረሰና ትምህርት ቤት ገባ። ከቁመቱ እኩል የሆነ ምሳ ዕቃ ተሸክሞ መመላለስ ጀመረ። ደብተሩ ላይ የሚስላቸው የብርጭቆ ስዕሎችና የሚፅፋቸው የላቲንም ሆነ የአማርኛ ፊደላት ቅርፃቸው እኩል በመሆኑ ‘ፊደል የመጣው ከስዕል ይሆን እንዴ’ የሚያስብል የሊንጉስቲክ ንድፈ ሃሳብ ያጭራል።
አቡሻ ስለዚህ ሁሉ አይገደውም። ተጽፏል ተጽፏል ነው። “ሞኝ እና ወረቀት የያዘውን አይለቅም የሚለው” ሃገርኛ አባባል ለአቡሻ የእርሳስ ጽሁፍ አይሰራም። አቡሻ የሞኝን መልቀቅ አለመልቀቅ ባያውቅም የወረቀቱን መልቀቅ በደምብ የውቃል፤ ታድያ በእርሳስ የተፃፈ እንደሆነ ነው። በመሞነጫጨር የቀለመ ወረቀት በላጲስ ሲታሽ እልም ይላል። ለሰው ልጅ ንስሃ እንደተሰጠው ሁሉ ለወረቀትም ላጲስ የተሰጠው ይመስላል። ያለፈው ይደመሰስና አዲስነት ብቅ ይላል። ባዶነት ሳይሆን ንጹህነት ያብባል።
ሁሉም ትምህርቶች በአንድ ደብተር ይፃፋሉ። የትምህርቶቹ ልዩነት ለአቡሻ እምብዛም አያስጨንቀውም፤ እንዴውም የአቡሻን ሚስጢር ለመጠበቅ ካልተባለ በቀር ልዩነት ያላቸው አይመስለውም። ይልቅ ትምህርትነታቸው፣ አንድነታቸው ይጎላበታል። የሰው ልጅም እንዲህ እንደዛሬው ለቁጥር ሳያዳግት በፊት አንድ ቤተሰብ ነበር። ትምህርቶች ሁሉስ እንደዛሬው ስያሜያቸው ቢሉ ይዘታቸው የትዬለሌ ሳይሆን አንድ ቤት ተጋርተው እንደሆንስ ማን ያውቃል? ያዎቀም ካለ ደግ ነው ያላወቀም ካለ ጥያቄው ሽልማት አልባ በመሆኑ መጨነቅና ሆድ ሆዱን እንደ ኮሶ ትል ሲበላው ማደር የለበትም።
አቡሻ ከሁሉም የአማርኛ ፊደላት የምታስገርመው ‘ቀ’ ስትሆን የምታናድደው ደግሞ ‘ጨ’ ናት። ‘ቀ’ በሁለት እጆቿ ወገቧን ይዛ የቆመች ይመስለውና ፈገግ ይላል። እውነቱን ነው ከመቆሟ አቋቋሟ ይገርማል። አንዱን እጇን ደክሟት ድንገት ብትለቀው ምናይነት ቅርጽ ሊኖራት እንደሚችል አስባችሁታል? ወይ ዘናጯ ‘ቀ’! አይበለውና ሁለት እጇን ደክሟት የለቀቀችው እንደሆንስ? በቃ… መለመላዋን ትቀርና አንድ ቁጥር ትሆናለች፥ አስባችሁታል? አቡሻ ‘ቀ’ን ሲያያት ሌላው ትዝ የሚለው የሰፈር የእግር ኳስ ቡድኖች ሲጋጠሙ ደጋፊዎች የሚሏት ሁለት ስንኝ ግጥም ናት።
“ቀ ቁ ቂ ቃ
ይገባል በደቂቃ”
ቢገባም ባይገባም እንዲህ እየተባለ ይጨፈራል። ታዲያ አንድም ግብ ሳይቆጠር ደቂቃ አልፎ ሰዓት ይቆጠራል። ደጋፊ ሆዬ አሁንም ቀ ቁ ቂ ቃ እያለ ነው። አቡሻ አብዝቶ ይገርመዋል ወይ ‘ቀ’ የማትገባበት የለ ደሞ’ኮ ሁለት እጇን አሁንም እንደሰቀለች ነው። በጣም ታሳዝነውና በያዘው ላጲስ አሸት አሸት አድርጎ ሁለት እጆቿን ያወርድና ወደ አንድ ቁጥር ይቀይራታል። እንዴ ሚዛናዊ ከሆኑ ለሁሉም ሚዛናዊ መሆን ነው አንድ ቁጥርስ ይሄን ሁሉ ዘመን ቁሞ አንድ “ኖር ይቀመጡ” የሚል የልብ ወዳጅ ኧረ ይሄም ይቅርና አንድ ፈጣሪን የሚፈራ ሰው ይጣ? ያሳዝናል አቡሻም የተጨነቀው ስለ ዘናጯ ‘ቀ’ ነው እንጅ አንድ ቁጥርን አላቋጠረውም።
ሁሉም ቁጥር ሲጀምር በአማርኛ አንድ ቢል በግዕዝ አሃዱ ብሎ በእንግሊዝኛ ዋን ሊልም ላይልም ይችላል፥ እንደየምርጫው። ታዲያ ምን ዋጋ አለው ሁሉም ተራምደውት አልፈውት ሄዱ። አስራ አንድ ላይ ሲደርሱ ለማስታወስ ሞክረው እምብዛም ሳያስተውሉ ጭራሽ ደባል አድርገውት አለፉ። አይይ… አንድ ቁጥር ብቻውን መቆም ሲመረው አስራ አንድ ላይ “አንድነት ሃይል ነው” በሚል ስሜት ከሌላ አንድ ቁጥር ጋር መሳ ለመሳ ቆመ። ይሄንም እንተወውና ሃያ አንድ ላይ ሁለት ለራሷ ተቀምጣ አንድ ቁጥርን ቀና እያለች ታየዋለች፤ አንገቷ እስኪሰበር። አቡሻ ይሄን መሰል ‘ቀ’ን እና አንድ ቁጥርን መሰረት ያደረገ ሃሳብ ሲያውጠነጥን ለምሳ የዕረፍት ደዎሉን የትምህርት ቤቱ ጥበቃ ጋሽ አቤ በዘነዘና ያለርህራሄ ይነርቱታል፤ ደዎሉም ይጮሃል ሰሚ የለውም በዚያው ቅጽበት ተማሪዎች”ረፍት” እያሉ ካለ ቅጥ ስለሚንጫጩ።
ሌላኛዋ የአቡሻ የግርምት ሰበብ ‘ጨ’ ናት። ወይ ‘ጨ’! ባለ ሶስት ቀለበቷ ‘ጨ’! ይሄ ሁሉ ቀለበት ምን ሊያደርግላት ነው የደረደረችው? አግብቻለሁ ለማት አንዱ አይበቃም ነበር? ይላል ምስኪኑ አቡሻ። ‘ጨ’ን መፃፍ ለአቡሻ የዳገት ያክል ይከብደዋል። ቢሆንም ግን ተረጋግቶ ይጽፋትና እያያት መገረሙን ይቀጥላል።
አቡሻ ለጽሑፉ ማማር እምብዛም አይጨነቅም። ምክኒያቱም የጎበዝ ተማሪ ጽሑፍ አያምርም እያሉ ሲያወሩ በመስማቱ ነው። ይሄን ሃሳብ ማን እንደፈለሰፈው፣ ማንስ እውቅና እንደሰጠው ባይታወቅም ውስጥ ውስጡን ግን ትምህርት ቤት ውስጥ ይወራል።
ሌላው አቡሻ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ቢኖር የፊርማ ጉዳይ ነው። ደብተሩ እስኪሞላ ኋላም መልሶ በላጲስ ንጹሕ እስኪያደርገው ድረስ ፊርማ ይለማመዳል። በርግጥ ፊርማ አንድ ቢሉ መለያ ማህተም፣ ሁለት ቢሉም የአሰራር ማረጋገጫ መለዮ ነውና ትኩረት መሰጠቱ አይከፋም። አቡሻ የአባቱን ፊርማ አብዝቶ ይወደዋል።
ብዙ ጊዜ የአባቱን የሚመስል ፊርማ ለመፈረም አስቦ መሳል ይጀምርና መሃል ላይ ይጠፋዋል ከዛም ድንገት የመጣለት ፈጠራ ይጨምርና ሁለት በአንድ ይሉት ዓይነት ፊርማ ይፈርማል፣ በአባቱ ጀምሮ በራሱ ግምት ይጨርሰዋል። ፈርሞ ከጨረሰ በኋላ አስተውሎ በመመልከት ግምገማ ያካሂዳል። አንዳንዴ ከአባቱ የበለጠ ፊርማ እንደፈረመ ቢሰማውም ግን የአባቱን ፊርማ ባለመምሰሉ ይናደዳል። ብዙ ዓለምን ያስደነቁ፣ ሕይዎትን በሚገባ ያቀለሉ የሳይንስም ሆኑ የኪነ-ጥበብ ፈጨራዎች የተገኙት ካላሰለሰ ጥረት እና ሙከራ በመሆኑ ደጋግሞ መሞከር የሚጠላ አይደለም፤ ይልቁንም የሚበረታታ እንጂ።
አቡሻ ታታ መሬም የተናገሩትን ንግግር እያስታወሰ መፈረም በመቻሉ ኩራት ይሰማዋል። ታታ መሬም “ልጆቼ፣ ከፋም በጄም መማር መመራመርን፣ ማወቅን የመሰለ ሃብት የለም ባስር ጣት እንደልብ ስክርቢቶ አንስቶ መፈረምን የሚያህል ኩራት የት ይገኛል? የተፃፈ ማንበቡንም አያህል! እኔ አሁን ትሸለም ቢሉ ትገደል ምኑን አንብቤ እረዳዋለሁ? መቼም ግን አልሃምዱሊላህ እኔ ባልማር ልጆቼን አስተምሬያለሁ! እውቀት መገብየትን የመሰለ የለም! ‘ተማር ልጄ’ አለ ዘፋኝ!” ይላሉ ፀሃይ ለመሞቅ ደጅ ሲቀመጡ ለሚከቧቸው ልጆች። አቡሻ ይሄን የታታ መሬምን ንግግር ይወድላቸዋል።
አቡሻ ቀለም እየዘለቀው በመምጣቱ እየተንተባተበም ቢሆን ማንበብ ጀመረ። ማንበብ በመቻሉ ደስታው ለጉድ ነው። በየመንገዱ የተሰቀሉ የማስታዎቂያ ልጥፎችን አንዱንም ሳይዘል ያነባቸዋል። በዚሁ አጋጣሚ የአብዛኞቹን ነጋዴ ስም በአጭር ጊዜ መሸምደድ ቻለ። ይሄም ሽምደዳ የተለዬ ዕድል ይዞለት ከተፍ ባይልም ለክፉ ቀን ያገለግለው ይሆናል። ማን ያውቃል? ይህ የማስታዎቂያ ንባብ እንደወትሮው ተልኮ ቶሎ የልብ አድርሶ መመለስ እንዳይችል የቀደመ ፍጥነቱን ገታበት። ቤተሰብም ሆኑ ጎረቤት የሄን ዳተኛነቱን እምብዛም አልወደዱለትም። ነገሩ “አዲስ ስፖርተኛ፣ ተከርብቶ ተኛ፤” ነውና አሽሟጠው አልፈውታል።
ሌላው አንድ ነገር ውሸታሙ እረኛ፣ ድኩላ እና ነብር፣ ውሻውን የከዳ ውሻ ይሆናል፣ ዔሊ እና ጥንቸል፣ ላሜ ቦራ የመሳሰሉ ታሪኮችን የንባቡ ማሟሻ አደረጋቸው፤ ከመደጋገም ብዛትም በቃሉ አጠናቸው። ዘወትር እነዚህን ታሪኮች ሲያነበንብ የሚሰሙ ሁሉ እኩል አብረው ታሪኩን ሸመደዱ። ‘ውሻውን የከዳ ውሻ ይሆናል’ የሚለውን ታሪክ ዘወትር ሲያነብ የሰሙ ሁሉ ስለ ውሻ ያላቸው አረዳድ በመቀየሩ ‘መቻል’ ለተባለው የሰፈር ውሻ ቀን ወጣለት። ዳቦ የሚወረውርለት መንደርተኛ በረከተ። የአቡሻ ንባብ ማህበረሰባዊ ተጽዕኖ መፍጠር ጀመረ።
ታታ መሬም ያሉት ነገር ደረሰ፤ አቡሻ ባቅሙ አውቆ ማሳወቅ ጀመረ። አንብቦ መረዳትን ያህል ጠቀሜታ ከወዴት ይገኛል? ከምንም።
(ደረጀ ደርበው)
በኲር የሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም