ልጆች የሚያድጉበት እና የሚቀረፁበት መንገድ አዋቂ ሆነው ከሰው ጋር በሚኖራቸውን ግንኙነት፣ የትዳር ህይወት፣ ስኬት፣ በራስ መተማመን ላይ ትልቅ ሚና አለው:: በልጆች አስተዳደግ ዙሪያ ጃፓናዊያን በመልካም ይታወቃሉ:: የጃፓናዊያንን የልጅ አስተዳደግ እናስቃኛችሁ::
ወላጆች ለልጆች ምሳሌ መሆን
ጃፓናዊያን የሥነ ምግባር መሠረትነት ያለው አርአያነትን ለልጆች የማመላከት ሚና በቀዳሚነት የወላጆች ድርሻ እንደሆነ ያምናሉ። ልጅ ቀጥተኛ እና የቅርብ ግንኙነት የሚኖረው ከወላጁ ጋር ስለሆነ ወላጅ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል። የሀገርን ታሪክና መልካም ባሕልን ማስተማር፣ የልጅን አጠቃላይ እንቅስቃሴ መከታተል፣ ፍላጐትና ዝንባሌውን መገምገም፣ አስፈላጊ ነገሮችን በአግባቡ ማቅረብ፣ ለመንፈሣዊ፣ አካላዊ እና ማኅበራዊ እድገቱ ሳይታክቱ መትጋት ከሁሉም በላይ ወላጅን ይመለከታል፤ ቤተሰብ የመጀመሪያው ት/ቤት ነው ነው ብለው ያምናሉ።
ልጆችን ወደቤተእምነት መውሰድ
ጃፓናዊያን ቤተእምነት እና ሥርዓት በሚታይ ክንውን የሚገለጽ በመሆኑ ልጆች ወደ ቤተእምነት ሲመጡ በቃል ከሚማሩት ይልቅ በማየት የሚማሩት ይበልጣል ብለው ያምናሉ።
ለልጆች ጊዜ መስጠት
ልጆች በሕይወታቸው ከሚያስደስታቸው ነገሮች አንዱ ከወላጆች ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ እንደሆነ ጃፓኖች ይገልፃሉ። በተለይ ሁለቱም ወላጆች አንድ ላይ ሆነው ሲጫወቱ፣ ሲስቁ፣ ሲመገቡ እና ሲያወሩ ማየት በጣም ይናፍቃቸዋል ይላሉ። በአንድ ላይ መጻሕፍትን ማንበብ፣ ፊልምችን አብሮ ማየትን ጃኖች ይተገብራሉ። ከቤት ውጪም ልጆችን የተለያዩ ቦታዎች ይዞ ወጥቶ ማሳለፍ፣ መጫወቻ ቦታ፣ የእንስሳት ግቢ፣ ታሪካዊ ቦታ፣ ሙዚየም፣ ገበያ እና ወደ ቤተ ዘመድ ቤት አብሮ መሔድ ይገባል ላሉ። ከዚህም ልጆች መልካም ጠባይን እና ጠቃሚ ማኅበራዊ እሴቶችን ይቀስማሉ።
በወላጆች ፍቅር አርአያነት
ልጆች ወላጆቻቸው እርስ በእርሳቸው ሲዋደዱ እና ሲተሳሰቡ ሲያዩ የደስታ ስሜት ይታይባቸዋል። በወላጆች መካከል አለመግባባት ቢኖር እንኳ ልጆች በሌሉበት መወያየት ያስፈልጋል ይላሉ። የመላው ቤተሰብ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ በጋራ መወያየት ልጆች ለወደፊት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጥሩ ተሞክሮ ይሆናቸዋል። ወላጆች በልጆቻቸው ፊት እውነተኛ መሆን ይገባቸዋል።
ልጅን በመምከር እና በመገሰጽ
ጃፓናዊያን ልጆች መደበኛ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የስነ ምግባር ትምህርትን በደንብ ይማራሉ:: ልጅን መምከር የአዎንታዊ ጠባያት መገንቢያ እና ከመጥፎ ሥነ ምግባር ማረሚያ ነው። ልጆችን ሀይማኖት እና ሥነ ምግባር ይዘው እንዲያድጉ ልንገስጻቸው እና ልንቀጣቸው ይገባል ብለው ያምናሉ። ቅጣት ሲባል ብዙ ጊዜ ወደ አእምሯችን የሚመጣው አካላዊ ቅጣት ነው። ከጃፓን የልጆች አያያዝ ሕግ አንጻር ግን ይህ አግባብ ላይሆን ይችላል። አካላዊ ቅጣት ሳንቀጣ የሚወደውን ነገር የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ መከልከል ነው ይላሉ። ፊልም ማየት፣ መዝናኛ ሥፍራ መሔድ፣ ዘመድ መጠየቅ፣ . . . በጥፋቱ ምክንያት ከነዚህ ነገሮች ማዕቀብ መጣል ነው ቅጣቱ።
የዘመኑን ቴክኖሎጂ ልጆች በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ
በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ዓለምን በጣም አቀራርቧታል። በድምጽ እና በምስል ጠቃሚውም ጎጂውም ነገር በቴሌቪዥን፣ በድረ ገጽ፣ በእጅ ስልክ፣ በመጽሔትና በጋዜጣ በየትኛውም ቦታ ይገኛል። ልጆች የሚያዩትን፣ የሚሰሙትን እና የሚያነቡትን ነገር ጠንቅቆ ማወቅ እና መቆጣጠር እንደሚገባ ጃፓኖች ጽኑ እምነታቸው ነው።
ምንጭ፡ ሳቪ ቶኪዮ ድረ ገጽ
ተረት
ልዑሉ እና ባላገሩ
አንድ ልዑል ከቤተ-መንግስት ራቅ ብሎ ወደሚገኝ አንድ ትልቅ ጫካ ሄዶ አደን ሲያድን ውሎ ወደ ቤተ-መንግሥቱ ሲመለስ አንድ ባላገር ያገኛል:: ባላገሩ ልዑሉ ማን እንደሆነ አያውቅም ነበርና አንዳችም እጅ- ሳይነሳ፣ ሰላምታም ሳይሰጥ ዝም ብሎ መንገዱን ይቀጥላል:: ልዑሉም የባላገሩ ነገር ገርሞት፣ “ሰማህ ወይ ወዳጄ፣ ለመሆኑ እኔ ማን እንደሆንኩ ታውቃለህ ወይ?” ሲል ይጠይቀዋል::
ባላገሩም፤ “በመንደራችን ባለው ጫካ ውስጥ በገዛ-ፈቃድህ ገብተህ አደን ስታድን እንደቆየህ አይቻለሁ:: በሰላም የተቀመጡትን አዕዋፋት ስትረብሻቸው፣ እንስሳቱንም መጠጊያ ስታሳጣቸው የነበርክ ሰው መሆንህንም ተመልክቻለሁ” አለው:: ልዑሉም፤ “ምን ስሠራ እንደቆየሁ ማወቅህ መልካም:: ማንነቴንስ አውቀሃል ወይ?” ባላገር፤ “አላውቅም::”
ልዑሉ፤ “እንግዲያው ና ፈረሴ ላይ ውጣና አብረን ወደ ከተማ እንሂድ:: ንጉሥ ማለት ምን እንደሆነ እዚያ ታውቃለህ” አለው:: ልዑሉ ባላገሩን አሳፍሮ ወደ ከተማ ይዞት ሄደ:: በመንገድ ላይም “ንጉሥ ማለት የተከበረ፣ በሄደበት ቦታ ሁሉ ህዝብ እጅ የሚነሳው፣ መንገደኛው ሁሉ ቆሞ የሚያሳልፈው ትልቅ ሰው” ነው አለው::
ከተማ ሲደርሱ፤ ህዝቡ ልዑሉን ሲያይ እየቆመ፣ እጅ እየነሳ አሳለፈው:: ግማሹም አቤቱታውን አሰማ:: ይሄኔ ልዑሉ ወደ ባላገሩ ዞሮ፤ “አሁንስ ንጉሡ ማን እንደሆነ አወቅህ?” ንጉሡ ማን ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው:: ባላገሩም፤ “እንግዲህ ወይ እኔ ወይ አንተ መሆናችን ነዋ” ሲል መለሰ ይባላል:: አንዳንድ ነገሮች ግራ የሚያጋባ ደረጃ ቢደርሱም በደንብ መርምሮ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ከተረቱ እንማራለን::
ምንጭ ፦ ልጆች እና ተረት
ሞክሩ
- አንድን የቤት ግድግዳ ለመገንባት ስምንት ሰዎች አራት ሰዓት ቢፈጅባቸው አስራስድስት ሰዎች ስንት ሰዓት ይፈጅባቸዋል?
- ከላባ የቀለልኩ ነኝ:: ነገር ግን አንድ ጠንካራ ሰው ለአምስት ደቂቃ አፍኖ ሊያቆዬኝ
አይችልም:: እኔ ማን ነኝ?
- ጥርስ አለኝ፤ ነገር ግን መብላት አልችልም:: እኔ ማን ነኝ?
መልስ
- ምንም፤ ምክንያቱም ግድግዳው ተሰርቶ አልቋል
- ትንፋሽ
- ማበጠሪያ
ነገር በምሳሌ
- አባት ያበጀው ለልጅ ይበጀው፡-ዛሬ የሰራነው ይጠቅማል ለነገ ፡፡
- የሺህ ኪሎ ሜትር ሩጫ በአንድ እርምጃ ይጀመራል፡-ሁሉም የስኬት ግስጋሴ ካለበት
ይጀመራል፡፡
- ሲያከሩት ይበጠሳል፤ ሁሉን በልክና በመጠኑ መያዝ ይበጃል፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም