ወደ ንግድ ዓለም የገባችው በ2000 ዓ.ም ነው:: የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዋ ትርንጎ የሺዋስ ያኔ ገና በ16 ዓመቷ ነበር:: ትርንጎ በለጋ እድሜዋ ወደ ንግድ የገባችው አዋጭ መሆኑን ተገንዝባ ወይም የመሥራት ፍላጎቷ ከፍተኛ ሆኖ ሳይሆን ወላጆቿን በሞት በመነጠቋ ምክንያት ራሷን ማስተዳደር የግድ ስለሆነባት ነበር::
በወቅቱም ሥራዋን ለመጀመር የሚያስችላትን የልብስ ስፌት ስልጠና እና የመሥሪያ ማሽን ከአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አገኘች:: ባገኘችው የልብስ ስፌት ማሽን እና ሙያዊ ስልጠና ራሷን በማብቃት የተቀደዱ ልብሶችን መስፋት ጀመረች:: አልፋ በራሷ ዲዛይን በማድረግ ቀሚሶችን እና ቦርሳዎችን ማምረት ቻለች::
ትርንጎ ለቀጣይ ስኬቷ የስልጠና እና የብድር አገልግሎት ለማግኘት እና ከመሰሎቿ ጋር ሀሳብ ለመለዋወጥ የነጋዴ ሴቶች ማሕበር አባል ሆነች:: በአባልነቷም ከማህበሩ ብድር በመውሰድ ሥራዋን አስፍታለች:: አሁን ላይ ሰባት የልብስ ስፌት ማሽን በመግዛት ሥራዋን ታከናውናለች:: ከስፌት ስራዋ ጎን ለጎንም በዘርፉ ስልጠና በመስጠት ገቢዋን ማሳደግ ችላለች:: ለእድገቷም በዋናነት ማህበሩ እንደሆነ መስክራለች::
”የነጋዴ ሴቶች ማሕበር አባል በመሆኔ ብዙ ጥቅሞችን አግኝቻለሁ” ያሉን ደግሞ ሌላዋ የማህበሩ አባል ወ/ሮ አዛለች መኮንን ናቸው:: የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ አዛለች የማሕበሩ አባል የሆኑት በ2007 ዓ.ም ነበር:: በማህበሩም የገንዘብ ቁጠባን ጨምሮ የተለያዩ ሙያዊ ሥልጠና እንደተሰጣቸው ነው የገለጹት::
በማሕበሩ የብድር እና ቁጠባ ተቋምም ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሰማሩበትን የቆዳ ውጤቶች የማምረት ሥራ ማስፋት ችለዋል:: በየጊዜው የ40 ሺህ፣ የ100 ሺህ እና አሁን እየከፈሉ የሚገኙትን የሦስት መቶ ሺህ ብር የብድር አገልግሎት አግኝተዋል:: ወ/ሮ አዛለች እንደሚሉት ማሕበሩ የንግድ ትስስርም ፈጥሮላቸዋል::
ትርንጎ የሺዋስን እና ወ/ሮ አዛለች መኮንንን በንግዱ ዘርፍ እንዲዘልቁ በብድር፣ በስልጠና…በማገዝ ዛሬ ድረስ እንዲዘልቁ ያስቻላቸው የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማሕበር ”የነጋዴ ሴቶችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር እንዲሁም ድምጽ ለማሰማት” በሚል በ1992 ዓ.ም መቋቋሙን የማሕበሩ ፕሬዝዳንት ሲስተር ትቅደም ወርቁ ለበኵር ጋዜጣ ገልጸዋል:: በወቅቱ የንግድ ማሕበራት ምክር ቤት/የንግድ ቻምበር / ሁሉንም ነጋዴዎች በጅምላ ሴቱንም ወንዱንም ያቀፈ በመሆኑ ማህበሩ የሴት ነጋዴዎችን መብት እና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እና ለማስከበር ይሞከር ነበረው:: ይሁንና ይሰጥ የነበረው መፍትሔ በቂ ባለመሆኑ ብዙ ችግር ያጋጥማቸው ነበር:: ለምንድነው ሴት ነጋዴዎች ለብቻችን የራሳችንን ማሕበር በማቋቋም መብታችንን እና ጥቅማችንን ማስከበር የማንችለው” በሚል ሀሳብ 60 ነጋዴ ሴቶች ማሕበሩን በ1992 ዓ.ም መመሥረት ችለዋል::
መስራቾቹም ከባሕር ዳር፣ ደሴ ፣ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ የተውጣጡ በሸቀጣሸቀጥ ፣ በባልትና እና በመሳሰሉ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች መስክ የተሰማሩ ነጋዴ ሴቶች ነበሩ:: አሁን ላይ የማህበሩ አባላት 152ሺህ 236 ደርሰዋል:: በ121 ከተሞች እና ወረዳዎችም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: በፊት አብዛኛዎቹ የማሕበሩ አባላት የደረጃ ሐ ግበር ከፋይ የነበሩ ሲሆን አሁን እስከ ከደረጃ ሀ ድረስ ከፍተኛ ግብር የሚከፍሉ አባላት ተፈጥረዋል::
ፕሬዝዳንቷ እንደሚሉት ማሕበሩ ሥራ ማስኬጃውን በአባላት መዋጮ ነበር የሚያከናውነው:: ማሕበሩ በተቋቋመ ጊዜ የአባለት ዓመታዊ መዋጮ ሁለት ብር ነበር:: ከዚያም 10 እያለ አሁን ላይ 300 ብር ደርሷል::
ሕጋዊ የምዝገባ እና የንግድ ፈቃድ ያላት፣ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራች፣ የማሕበሩን ዓላማ እና መተዳደሪያ ደንብ የተቀበለች፣ በተሰማራችበት የንግድ ዘርፍ የንግድ ፈቃዷን ያደሰች፣ የማሕበሩን መብት እና ጥቅም የምታሰከብር፣ የመምረጥ እና የመመረጥ መብቷ በሕግ ያልተገደበ እና መዋጮ ማዋጣት የማሕበሩ አባል ለመሆንም የሚጠየቁ መስፈርቶች መሆናቸውን ሲስተር ትቅደም ጠቁመዋል::
ማሕበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያበረከታቸውን አስተዋጽኦ ፕሬዝዳንቷ ሲገልጹ፤ በወቅቱ ነጋዴ ሴቶች የግልም ሆነ የጋራ የመሥሪያ ቦታ፣ የገንዘብ እና የእውቀት ክፍተቶች/ በተለይም አብዛኛውን ጊዜ ነጋዴ የሚሆነው በልምድ እንጂ በዘርፉ ስልጠና እና ክህሎት አግኝተው አልነበረም ወደ ሥራ የሚገቡት/ ነበሩባቸው:: ታዲያ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል:: በተለይም የጋራ የመሥሪያ ቦታ ለማግኘት በአክሲዮን እንዲደራጁ ተደርጓል:: ለአብነትም በባሕር ዳር ከተማ ሁለት መንታ ሕንጻዎችን ወደ 236 ሴቶች አንድ ላይ ተደራጅተው ገንብተዋል:: እንደ ክልል ደግሞ 47 የሚደርሱ አክሲዮን ማሕበራት ተደራጅተው የራሳቸውን ግንባታ ያከናወኑ ነጋዴ ሴቶች አሉ::
ሌላው አባላቱ ሥራቸውን ለማስፋት ገንዘብ እየፈለጉ አላንቀሳቅስ ያላቸውን የቢሮክራሲ፣ የብድር እና የወለድ ችግሮችን ለመቅረፍ በማሕበሩ የቁጠባ እና የብድር አክሲዮን ማሕበር ተቋቁሟል:: በዚህም የሚበደሩትን ገንዘብ አንድ ሦስተኛ የቆጠቡ ነጋዴ ሴቶች እርስ በርስ በመዋዋስ ከ50ሺህ እስከ 400ሺህ የሚደርስ ብድር ማግኘት ችለዋል:: አሁን ላይ እስከ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የደረሱ አበዳሪ አክሲዮኖችም ተፈጥረዋል:: ወለዱም ከስድስት እስከ 10 በመቶ የሚደርስ ሲሆን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚከፈልበት ሂደት ተመቻችቷል:: ይህንን ሥራ የሚያከናውኑም 42 የቁጠባ እና ብድር አክሲዮን ማሕበራት አሉ::
ሌላው ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ስልጠናን የተመለከተ ሲሆን በሥራ ፈጠራ/ኢንተርፕርነርሺፕ/፣ በሒሳብ አያያዝ፣ በቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀት፣ በደንበኛ አያያዝ፣ ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር የዋጁ ነጋዴ ሴት እንዲሆኑ የዲጂታላይዜሽን ስልጠናዎችም እያገኙ እንዳሉ ነው ፕሬዜዳንቷ የገለጹልን:: ማሕበሩ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጦችን ያካሄደ ሲሆን ተሞክሮዎችን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመሄድ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ተችሏል:: የማሕበሩ አባላት እነዚህን ስልጠናዎች የሚያገኙት በተራ ቅደም ተከተል ነው ::
ሲስተር ትቅደም እንዳሉት እንደ ጀርመን ተራድኦ ድርጅት እና የስዊዲን ኢምባሲ ከመሳሰሉ አጋር ድርጅቶች ጋር ፕሮፖዛል ቀርጾ በማስገባት በሚያደርጉት ድጋፍ ሥልጠናዎችን አግኝተዋል:: በተለይም የስዊድን ኢምባሲ ባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን የማሕበሩን ባለአራት ፎቅ ሕንጻ ግንባታ ወጪ ከ70 በመቶ በላይ መሸፈኑን ነው የገለጹት:: ሕንጻውም ለማሕበሩ ቢሮ እና ለሌሎች ድርጅቶች በማዋል በክልሉ የሚገኙ 56 የሚደርሱ የማሕበሩን ሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ ይሸፍናል:: ይህም ማሕበሩ እንደማሕበር እንዲቀጥል ያስቻለ ሆኗል::
የስዊዲን ኢምባሲ ለ12 ዓመታት ማሕበሩን በተለያዩ መንገዶች ሲደግፍ መቆየቱን ነው ፕሬዝዳንቷ የገለጹት:: የምግብ አዘገጃጀት እና የልብስ ስፌት የመሳሰሉ የሙያ ስልጠናዎችን ይሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል:: ይህ እገዛ ባይደረግላቸው ኖሮ በማሕበሩ አባላት ዓመታዊ ወጪ ስለጠናዎችን መስጠት አዳጋች ያደርገው እንደነበርም አንስተዋል::
ከመንግሥት በኩል በሊዝ መነሻ ዋጋ የመሥሪያ ቦታ መሰጠቱን፣በሴቶች እና ሕጻናት ፌዴሬሽን እና በሕግ ባለሙያ ማሕበር በኩል ስልጠናዎችን ማግኘታቸውንም ተናግረዋል:: ከንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ጋር፣ ከግብር ኮሚቴዎች ጋር አብሮ የመሥራት ሁኔታዎች እንዳሉም ነው የጠቀሱት:: በአሁኑ ወቅት ማንኛዋም ሴት ወደ ንግድ ዓለም እንድትገባ ስልጠናዎችን እያካፈሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል::
ፕሬዝዳንቷ ‘‘የንግድ ሥራ ዝም ብሎ ዘው ተብሎ የሚገባበት ሳይሆን ራሱን የቻለ መንገድ አለው:: እውቀት ያስፈልገዋል፤ ከንግድ ቢሮ ባገኘነው መረጃ በዓመት ውስጥ ብዙ ንግድ ፈቃዶች ይወጣሉ፤ ከዚያም ከስረው የሚመለሱበት ሁኔታ ነው ያለው:: ምንድን ነው መነገድ ያለብኝ? ምንድን ነው ሊያዋጣኝ የሚችለው? ምን ያስፈልገኛል? የሚለውን ወደ ንግድ ሥራው ከመሰማራታቸው በፊት ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው:: ወደ ንግዱ ከተገባ በኋላ ደግሞ ቀልድ አይደለም የተያዘው፤ ብዙ ጊዜ እንደቀልድ እንደጨዋታ የትርፍ ሥራ ተደርጎ መታየት የለበትም፤ገንዘብ እስከወጣበት ድረስ የግለሰብም የሀገርም ሀብት ስለወጣበት በትኩረት ልንሠራ ይገባል’’ በማለትም ለነጋዴ ሴቶች ምክራቸውን ለግሰዋል::
በተጨማሪም ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለነገ የሚባል ነገር አለመሆኑን ያሳሰቡት ሲስተር ትቅደም፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ዘመኑ እየሰለጠነ በመምጣቱ ነጋዴዋ ራሷን ከቴክኖሎጂ ጋር ማዘመን እንደሚኖርባት ጠቁመዋል:: ምክንያም ኢትዮጵያ የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣናን ፈርማለች፤ ይህ ማለት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነጋዴዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ይነግዳሉ ማለት ነው:: ስለዚህ ከነሱ ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን መብቃት አለብን፤ አለበለዚያ መወዳደር ሳንችል የነሱ ተቀጣሪ ልንሆን እንችላለን፤ እናም ነጋዴ ሴቶች ራሳቸውን ከዘመኑ የግብይት ሥርዓት ጋር ሊዋጁ ይገባል ነው ያሉት:: በቀጣይ ማሕበሩ ያለበትን የብድር ችግር ለመቅረፍ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት::
መረጃ
የአማራ ክልል ነጋዴ ሴቶች ማህበር መስራቾች ከባሕር ዳር፣ ደሴ ፣ጎንደር እና ደብረ ማርቆስ የተውጣጡ በሸቀጣሸቀጥ ፣ በባልትና እና በመሳሰሉ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች መስክ የተሰማሩ ነጋዴ ሴቶች ነበሩ:: አሁን ላይ የማህበሩ አባላት 152ሺህ 236 ደርሰዋል:: በ121 ከተሞች እና ወረዳዎችም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: በፊት አብዛኛዎቹ የማሕበሩ አባላት የደረጃ ሐ ግበር ከፋይ የነበሩ ሲሆን አሁን እስከ ከደረጃ ሀ ድረስ ከፍተኛ ግብር የሚከፍሉ አባላት ተፈጥረዋል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም