የሕብረቱ ጉዞ

0
121

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ቤልጂየም፣ ጣልያን እና ጀርመን አቅማቸው የፈቀደውን ያህል አፍሪካን በመቆጣጠር  ሀብቷን ተቀራምተዋል፡፡ እንዲሁም አፍሪካዊያንን በባርነት ሲያሰቃዩ እና ባሕር አሻግረው ለጉልበት ሥራ ወደ አውሮፓ በመውድ እንደ እንስሳት ሲሸጧቸው ነበር፡፡ ታዲያ ለበርካታ ዘመን በዚህ ድርጊታቸው የተማረሩ አንዳንድ አፍሪካዊያን መሪዎች አውሮፓዊያኑ  የዘረጉትን የቅኝ አገዛዝ መዋቅርን በጣጥሶ ለመጣል ብቅ አሉ፡፡ መሪዎቹ አንድ የሚያደርጋቸውን ሕብረት ለመመሥረት ፍላጎት ቢኖራቸውም ሀሳባቸው አንድ ባለመሆኑ ግን ሁለት ቡድን እንዲፈጠር ምክንያት ሆነ።

ቡድኖቹ የካዛብላንካ ቡድን እና የሞኖሮቪያ ቡድኖች  በመባል ይታወቃሉ፡፡ የካዛብላንካ ቡድን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሀገራቱ በፍጥነት ተዋህደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚል ሀሳብ ያለው ሲሆን  የሞኖሮቪያ ቡድን ደግሞ አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል የሚል ሀሳብን ያነገበ ነበር፡፡ ታዲያ ሁለቱም ቡድኖች የአፍሪካ አንድነት እንዲመሠረት  ቢፈልጉም  እንዴት ነው መመስረት ያለበት? የሚለው ጥያቄ ግን ልዩነታቸውን አስፍቶት ነበር፡፡

በጋናዊው ኩዋሜ ኑኩርማህ እ.አ.አ በ1961 የተመሰረተው የካዛብላንካው ቡድን  ጊኒ፣ ሊቢያ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ማሊ፣ አልጄሪያን ያካተተ ሲሆን በሴኔጋላዊው መሪ ሴንጎር የሚመራው የሞኖሮቪያው ቡድን ደግሞ  በሥሩ ሃያ አራት ሀገራትን (ሴኔጋል፣ ቶጎ፣ አይቮሪኮስት፣ ናይጄሪያ፣ ላይቤሪያ ካሜሮንን ጨምሮ  ሌሎች በርካታ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ  ሀገራትን) ያቀፈ ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ከፍፍል ወደ ጎን በመተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እ.አ.አ ግንቦት 25 ቀን 1963 ለመመሥረት ችለዋል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት የኢትዮጵያው መሪ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ እና የጋናው መሪ ኩዋሜ ንኩርማህ ለምሥረታው የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ ሲመሠረትም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያው የድርጅቱ ሊቀ መንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት በዋነኝነት በቅኝ ግዛት ሥር ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ነጻ በማውጣት፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ውህደት በመፍጠር የአፍሪካዊያንን ሕይዎት ማሻሻልን ዓላማ በማድረግ ነበር። ቅኝ ግዛትን ከማስወገድ ባለፈ አፍሪካዊያን ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ፖለቲካዊ  ነፃነት እንዲኖራቸው ማስቻልም ሌላኛው ዓላማው ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚል ስያሜውንም በ2002 በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ላይ በነበረው የአንድነቱ ጉባኤ ላይ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተሸጋግሯል፡፡ አባል ሀገራቱም 55 ደርሰዋል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ /ANC/ የአፓርታይድን አገዛዝ እንዲዋጋና ዛኑ  እና ዛፑ የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ዚምባብዌን ነጻ እንዲያወጡ መሳሪያና ወታደራዊ ስልጠናን አበርክቷል።

ሕብረት ከሆነ በኋላ (የአፍሪካ ሕብረት) አሳካቸው ከሚባሉ ጥቂት ጉዳዮች መካከል ደግሞ በሀገራት መካከል እና በአንድ ሀገር የውስጥ ግጭቶች ላይ እየገባ ለማሸማገል የሚያደርገው ጥረት ነው፡፡ ለአብነትም በሶማሊያ የላካቸው ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ በኢትዮጵያ በተከሰተው የሰሜኑ ጦርነት የኢትዮጵያን መንግሥትና የሕወሓት መሪዎችን እንዲደራደሩ በማድረግ የመዘዙትን ሰይፍ ወደ ሰገባው በመመለስ ጦርነቱ በውይይት እንዲቋጭ አድርጓል። ከድርጅቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በሶማሊያ ሌሎች ድርጅቶች መሥራት ያልቻሉትን የሰላም ማስከበር ዘመቻ በውጤታማነት ሠርቷል። አል ሸባብን ከሞቃዲሾና ከኪስማዩ በማስወጣት በሶማሊያ በሕዝብ ተቀባይነት ያለው መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመሥርቷል፡፡   ቀደም ብሎም የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ቡሩንዲ፣   ዳርፉር  (ሱዳን) እና ወደ ኮሞሮስ ደሴቶች ልኳል። ይህ ሁኔታ አፍሪካዊያን የሚፈጠሩባቸውን ችግሮች በራሳቸው ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ አንድ አቋም መያዙ ከሕብረቱ ታሪክ ተጠቃሽ ስኬት አንዱ ነው፡፡

ስታቲስታ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በአህጉሪቱ 429 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከድህነት ወለል በታች የሆነ ሕይወትን ይመራሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አፍሪካ ቀጥተኛውን የቅኝ ግዛት ዘመን እንደተጠናቀቀ ብታወጅም አሁንም የእጅ አዙሩ ቅኝ ግዛት እንደቀጠለ ነው። አውሮፓዊያን የአፍሪካ ሕዝቦች ሀብታቸውን በነፃነት ተጠቅመው ምቹ ሕይዎት እንዳይኖሩ በዘሩት ዘረኝነት በእርስ በርስ ጦርነት አዙሪት ውስጥ ይገኛሉ። በአሁኑ ጊዜ ሌላው ዓለም በቴክኖሎጂ ፈጠራ  የዕለት ተዕለት ኑሮውን እያዘመነ ሕይዎቱን ቀላል እያደረገ ይገኛል፡፡ በተቃራኒው አፍሪካዊያን ኋላ ቀር በሆነ አመለካከት ተሸብበው ሁሌም ለማኝ እና ተረጂ በመሆን ድህነትን ለልጅ ልጅ እያወረሱ መኖርን የሙጢኝ ብለዋል፡፡

ከጥገኝነት የተላቀቀች፣ የኢኮኖሚ ነጻነቷ የተረጋገጠ አህጉር መፍጠር የሚለው ዓለማ የመሥራቾቹ ሕልም ነበር፡፡ ይሁንና   በርካታ የፖለቲካ ሙህራን የአፍሪካ ሕብረት የተመሠረተበትን ዓላማ አሳክቷል ብለው አያስቡም፡፡ የተመሠረተበትን ዓለማ በለማሳካቱም አንዳንዶች “ጥርስ አልባ አንበሳ” እያሉ ይጠሩታል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ  አህጉሪቱ ከቅኝ ግዛት ብትላቀቅም አፍሪካ በየጊዜው ከጦርነትና ግጭቶች እስከ መፈንቅለ መንግሥት የደረሱ የሰላምና የደኅንነት እጦቶችን እያስተናገደች ነው፡፡  የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት መውጣት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የተሞከሩ መፈንቅለ መንግሥቶች  ከ200 በላይ ደርሰዋል፡፡ የዚህ መበራከት ዋና ምክንያት ደግሞ ሀገራቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባለመዘርጋታቸው እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

አንዳንድ ምሁራን የአፍሪካ ሕብረት የሥራ ቋንቋ በፊት ቅኝ ሲገዙ በነበሩት ሀገራት ቋንቋ ማድረጉ በራሱ ከቅኝ ግዛት እንዳልወጣ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ እንደሚታወቀው ሕብረቱ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ፣ ፖርቹጋልኛ እና ስፓኒሽን በሥራ ቋንቋነት ይጠቀማቸዋል፡፡ አፍሪካዊ የሆነ ራሱን የቻለ የትምህርት ፖሊሲ ስላልተቀረጸም አፍሪካ ልቿን በምዕራባዊያን የትምህርት ፖሊሲ እንድታስተምር ተገዳለች።  ይህም ሕብረቱ የተቋቋመበትን ዓላማ አለማሳካቱን አንዱ ማሳያ አድርገው ያቀርባሉ።

የአፍሪካ ሕብረት ለውጭ ርዕዮተ ዓለም ከፍተኛ ተፅዕኖ ተጋላጭ በመሆኑ በሀገራቱ መካከል አንድነት  እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡ የአፍሪካ ሀገራት ላይ የምዕራቡ ዓለም፣ የቻይና እና የሩሲያ ርዕዮተ ዓለም ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ሁሉም  ለርዕዮተ ዓለም ተከታዮቻቸው የጦር መሣሪያ ድጋፍ በማድረግ አፍሪካዊ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ አድርገዋል የሚሉም አሉ።

ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት መርህ ምክንያት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአምባገነናዊ መንግሥታት ግፍና ጭፍጨፋ ሲካሄድ ድርጅቱ በዝምታ ማለፉ በርካታ አምባገነን መሪዎች እንዲፈጠሩ በር ከፍቷል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን መርህ በመሰረዝ ጣልቃ ቢገባም በቁርጠኝነት ሲንቀሳቀስ አይስተዋልም፡፡ ለዚህም ነው ግጭቶች እና ጦርነቶች የተበራከቱት የሚሉም አሉ።

ሕብረቱ አጀንዳ 2063ን በመቅረጽ ለተግባራዊነቱ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል፡፡ አጀንዳ 2063 ሕብረቱ  ለ50 ዓመት  የሚመራበትን ዕቅድ የያዘ ማዕቀፍ ነው። ማዕቀፉ እ.አ.አ በ2013 የጸደቀ ሲሆን እስከ 2063 የሚከወን ይሆናል፡፡  ሰባት የትኩረት አቅታጫዎችን በማስቀመጥም አጀንዳውን ለመተግበር እየተሞከረ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አጀንዳ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ዕውን ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ሕብረቱ በርካታ ችግሮች አሉበትና ነው፤ ለአብነትም 38 በመቶ ብቻ ነው ከጠቅላላ በጀቱ በአባል ሀገሮች የሚሸፈነው፡፡ 61 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከአጋሮች ይገኛል ተብሎ በታሰቢ የተያዘ  ነው። ከዚህ ባለፈም ሁሉም አባላት  የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በአግባቡ አያዋጡም። ይህ ደግሞ ለምዕራባዊያን ተጽዕኖ ተጋላጭ ያደርገዋል። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ታዲያ የአጀንዳ 2063 ዕውን የመሆን ነገር ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን የሚኖሩበት አሕጉርን የሚወክለው  ተቋም በዓለም አቀፍ መድረክ ያለው ተደማጭነትም አነስተኛ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የአፍሪካ ሕብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት በአፍሪካ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች አህጉሪቱን በዓመት 18 ቢሊዮን ዶላር (ሁለት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር ገደማ) እያስወጣ ነው፡፡ በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ጦርነቶች ኢኮኖሚውን ከማዳካም ባለፈ ዜጎች እንደቅጠል እንዲረግፉ አድርጓል፡፡ በተለይ እልባት ያልተገኘለት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እና የሰሞኑ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚታየው ግጭት አሁንም አህጉሪቷን  አንድም ጥይት የማይሰማባት ሰላማዊ አሕጉር አደርጋታለው የሚለውን የሕብረቱ እቅድን እንዳልተሳካ ማሳያ ነው።

እንዲህ እንዲያ እያለ የአፍሪካ ሕብረት ሀሳቦችን እንዳነገበ ከዓመት ዓመት ጉባኤዎችን እያካሄደ ዕቀዶቹንም እያሳወቀ መጓዙን ቀጥሏል፡፡ ዘንድሮም 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካዊያንና ዘርዓ-አፍሪካዊያን”በሚል መሪ ሀሳብ   የካቲት 8 እና 9/ 2017 ዓ.ም  የመሪዎች ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን   በስብሰባውም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣለች፡፡ በዚህ ስብሰባ የአፍሪካ ድምጽ በዓለም መድረኮች እንዲሰማ እና ሕብረቱ እንዲጠናከር በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸው ነው የተገለጸው፡፡ የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት 15 አባል ሀገራት አሉት። ኢትዮጵያም ለሦስት ዓመታት የምክር ቤቱ አባል ሆና ታገለግላለች።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here