በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሜሪካ እና ሶቭየት ሕብረት በአንድ ጎራ ተሰልፈው የጋራ ጠላታቸውን ጀርመንን እና አጋሮቿን አንበርክከው ነበር። ነገር ግን ጦርነቱ ወደ መጠናቀቁ ላይ አሜሪካ በጃፓን ላይ የተጠቀመችው አቶሚክ ቦምብ ለሩሲያ ያስተላለፈው መልእክት ጥሩ አልነበረም። አሜሪካ የዚህ አስፈሪ ቦምብ ባለቤት መሆኗ ከሩሲያ ጋር ያለውን ወዳጅነት በመሸርሸር ርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርጓቸዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ይህን ስሜት ይዘው በወዳጅነት መቀጠል አልቻሉም። እናም አንዱ በአንዱ ላይ የቴክኖሎጂ እና ወታደራዊ የበላይነት ለማረጋገጥ በፉክክር ውስጥ የገቡበት የቀዝቃዛው ጦርነት ቀጠለ። በዚህ የቃላት ጦርነት ወቅት የጦር መሳሪያ የበላይነት ይዞ መገኘት የወደፊቱ ኃያል ሀገር እንደሚያደርግ በማመን በሁለቱም ወገን እጅግ አውዳሚ የኑክሊየር ቦምቦችን እና ሮኬቶችን በመስራት ላይ ተጠመዱ። ይህ የጦር መሳሪያ ፉክክር ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይሎችን እስከመገንባትም ደረሰ።
ነገር ግን የአውዳሚ ቦምቦች፣ ወይም አህጉር አቋራጭ የኒኩሌር አረር እና ሮኬቶች ተሸካሚ ባልስቲክ ሚሳየሎች ባለቤት መሆን ብቻውን አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ እንደማያደርግ ተረጋገጠ። በሁለቱም መካከል የሚደረግ የኒኩሌር ልውውጥ ሁለቱንም ወገን አውዳሚ በመሆኑ እየተፈራሩ ከመቀጠል ሌላ አማራጭ እንዳይኖር አድርጎታል። ይሁን እንጂ በዚህ ሳይገደቡ ፉክክሩን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ የሁሉም ጎራዎች እምነት ነበር። በመሆኑም ሳይንቲስቶቻቸው ሰው ሰራሽ ሳተላይቶችን ወደ ሕዋ መላክ እንደሚቻል ያቀረቡት ምክረ ሀሳብ በፖለቲከኞች ቅቡል እንዲሆን የማሳመን ጥረት አድርገዋል። በተለይ አሜሪካውያን ይህን ለማድረግ በማሰብ ተቀዳሚ ነበሩ።
በዚህ የተነሣ ሁለቱም ኃያላን ሀገራት የኑክሊየር ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ስጋት ቢኖርባቸውም ሳይንሱን በማሻሻልና ሌሎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር ተግባራቸውን አጠናክረው ከመቀጠል አልታቀቡም፡፡ የምድር ወሰናቸውን በማስፋት የሚያደርጉት ፉክክር በሕዋ ምርምር ላይም የበላይ የመሆን ሌላ ፍላጎት አስነሳ።
በመሆኑም ከ1940ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ ሕዋ ሌላው የቀዝቃዛው ጦርነት ምትሃታዊ የፉክክር መድረክ ሆነ። በዚህ ፉክክር ሁለቱ ኃያላን የቴክኖሎጂ፣ ወታደራዊ አቅም እና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስርዓታቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ በሰፊው ተንቀሳቅሰዋል። ስለሆነም ቀደም ሲል በጦር መሳሪያ እሽቅድድም ወቅት አንዱ በአንዱ ላይ የመረጃ ስለላ እና የጦፈ የሚዲያ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያካሄድ የነበረ ሲሆን በሕዋ ፉክክሩም ይህን አላማ የበለጠ ማስፈፀም እንደሚቻል በማሰብ በአዲስ ጉልበት ወደ ፉክክር ገብተዋል።
በአሜሪካ እና በሶቭየት መካከል በሚደረገው ፉክክር በሕዋ ምርምሩ ማን ቀድሞ የተሻለ ርቀት ሊሄድ እንደሚችል ለማየት የሚደረግ ሩጫ ተጠናከረ። በሕዋ ፉክክሩ ዋና ዋና ተግባራት በሰው ሰራሽ ሳተላይቶች አማካኝነት ሕዋን መመርመር፣ የሰው ልጅን ወደ ሕዋ መላክ፣ እንዲሁም ሰዎችን ጨረቃ ላይ ማሳረፍ የመሳሰሉ ተግባራትን ለማሳካት ያለመ ነበር።
የሕዋ ፉክክሩ ውጤታማ በሆነ መልኩ የተጀመረው ሶቭየቶች በ1949 ዓ.ም “ስፑትኒክ 1” የተባለችውን ሳተላይት ወደ ጠፈር ካመጠቁ በኋላ ነበር። ሶቭየቶች “ስፑትኒክ 1”ን አር 7 በተሰኘው አህጉር አቋራጭ ባልስቲክ ሚሳየል አማካይነት ነበር እንድትወነጨፍ ያደረጉት። በመሆኑም “ስፑትኒክ 1” በዓለም የመጀመሪያዋ ሰው ሰራሽ ሳተላይት እና በመሬት ምህዋር ላይ የተቀመጠች የመጀመሪያዋ ሰው ሰራሽ ሳተላይት ናት። የስፑትኒክ ወደ ሕዋ መምጠቅ ለአሜሪካውያን ዱብዳ ነበር። እነርሱ አልተደሰቱበትም። ምክንያቱም ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ ከሩሲያ በፊት አቅደው እየሰሩ የነበሩት አሜሪካውያን ነበሩ። ይሁን እንጂ ፍፁም አሜሪካውያን ባልጠበቁት ሰዓት ሶቭየቶች ሳተላይት ማምጠቃቸው የማይታመን ከመሆኑም በላይ አስደንጋጭ ነበር። በተጨማሪም ይህ በአሜሪካ የአየር ክልል የኒኩሌር አረር የማስወንጨፍ አቅም ያለው አር 7 የተባለው አህጉር አቋራጭ ባልስቲክ ሚሳየል አስገራሚ አቅም የማሳየት ሙከራ አሜሪካኖችን በአስቸኳይ ስለሶቭየቶች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች መረጃ እንዲያነፈንፉ አደረጋቸው።
ስፑትኒክን በተሳካ ሁኔታ ወደ ሕዋ የማምጠቁ ስኬት የአሜሪካ ኤክስፐርቶችን እና ዜጎችን አስደንግጧል። ምክንያቱም በዚህ የቴክኖሎጂ እድገት አሜሪካ ቀዳሚነቱን ይዛ እንደምትፈፅም አስቀድሞ የተያዘውን እምነት ክሹፍ አድርጎት ነበርና። በዚህ ምክንያት አሜሪካ ከሶቭየቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ወደ ኋላ ቀርታለች በሚል ስለታሰበ ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና አስከትሎ ነበር። የሶቭየቶች ውጤታማ መሆን የአሜሪካ ወታደራዊ ዘርፍ በአጠቃላይ አዲስ ቴክኖሎጅን በመፍጠር ረገድ ወደ ኋላ ቀርቷል የሚል ፍርሀትን ማንገሱ አልቀረም። በዚህ የተነሳም የስፑትኒክ ወደ ሕዋ መምጠቅ የጦር መሳሪያ ፉክክሩን የማክረር እና የቀዝቃዛውን ጦርነት ውጥረት የመጨመር ሚና ነበረው።
በ1950 ዓ.ም ሁለቱም ሀገራት አዳዲስ ቴክኖሎጂ ለመፍጠር በስራ ተጠምደው ታይተዋል። እናም አሜሪካ ኤክስፕሎረር 1 የተሰኘች መንኮራኩሯን አመጠቀች። የተነደፈችው በሮኬት ሳይንቲስቱ ዋርነር ብራውን አመራር ሰጪነት በዩ ኤስ ሰራዊት ነው። በዚሁ ዓመት የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበሩት ደዌት ዲ አይዘናወር ናሳ የተሰኘውን የምርምር ጣቢያ የመሰረተውን ይፋዊ ትዕዛዝ ፈረሙ። ናሳ ጠፈርን ለማሰስ አላማ ያደረገ የፌዴራል ኤጀንሲ መሆኑ ይታወቃል።
አይዘናወር በተጨማሪም ከናሳ መርሀ ግብር ጋር ተባብረው የሚተገበሩ ሁለት ከብሔራዊ ደህንነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሕዋ መርሀ ግብሮችን ዘርግተዋል። የመጀመሪያው በአሜሪካ አየር ኃይል የሚመራ በሕዋ ወታደራዊ አቅም ላይ ምርምር የሚያደርግ ነው። ሁለተኛው በሲ አይ ኤ፣ በአየር ሀይሉ እና ኮሮና የሚል አዲስ የሚስጢር ስም በተሰጠው አዲስ ድርጅት የሚመራ፣ የሶቭየትን መረጃ ለማሰባሰብ በሳተላይቶቿ ዙሪያ ቅኝት ማድረግን ያለመ ነበር።
የሕዋ ፉክክሩ ተጧጧፈ። በ1951 ዓ.ም የሶቭየት የሕዋ ምርምር መርሀ ግብር “ሉና 2” የተሰኘች ሳተላይትን በማምጠቅ ሌላ እመርታ አስመዘገበ፣ ጨረቃን በመርገጥ የመጀመሪያዋ የሕዋ አሳሽ ናት። በ1953 ዓ.ም የሶቭየት ጠፈርተኛ ዩሪ ጋጋሪን “ቮስቶክ 1” በተሰኘች መንኮራኩር በመጠቀም የምድርን ምህዋር የዞረ የመጀመሪያው ሰው ሆነ። አሜሪካ በበኩሏ ሰው ወደ ጠፈር ለመላክ ባደረገችው ጥረት የናሳ ኢንጂነሮች በክብደት ከቮስቶክ የቀለለች መንኮራኩር በመገንባት ችምፓዚ ይዛ ወደ ጠፈር በማምጠቅ ሙከራ አደረጉ እና ዩሪ ጋጋሪ ከመሄዱ በፊት የመጨረሻውን በረራ መጋቢት ወር 1953 ዓ.ም አድርገው ነበር። በመሆኑም በግንቦት ወር 1953 ዓ.ም ላይ አሜሪካዊው አለን ሸፈርድ ወደ ህዋ በመምጠቅ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ሆኗል። ነገር ግን የመሬትን ምህዋር አልዞረም።
በዚያው ግንቦት ወር ከጥቂት ቀናት በኋላ ጆን ኤፍ ኬኔዲ አስር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጨረቃ ላይ ሰዎችን እንደሚያሳርፉ ጠንከር ያለ ይፋዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። የካቲት ውስጥ 1954 ዓ.ም ላይ ጆን ኤፍ ግሊን የመሬትን ምህዋር በመዞር የመጀመሪያው አሜሪካዊ ሆነ። እንዲሁም በዚሁ ዓመት መጨረሻ የናሳ የጨረቃ ፕሮጀክት የሆነው አፖሎ የሙከራ ዝግጅቱን መጨረሱ ታወቀ።
ከ1953 እስከ 1956 ዓ.ም ድረስ የናሳ በጀት ወደ 500 በመቶ ጨምሮ የነበረና ጨረቃ የማረፍ መርሀ ግብሩንም ለማሳካት የሰው ሀይሉን በመቶ ሽዎቹ ማሳደጉ ተዘግቧል። በጥር ወር 1959 ዓ.ም አፖሎ አንድ ችግር ገጠማት፣ በዚህ ወቅት መንኮራኩሯ የመነሳት ሙከራ በማድረግ ላይ ሳለች ካሳፈረቻቸው ሦስት ጠፈርተኞች ጋር በእሳት ጋየች።
ታህሳስ 1968 ዓ.ም ላይ አፖሎ 8 የተሰኘችው ሰዎችን ያሳፈረችው መንኮራኩር የጨረቃን ምህዋር የመዞር የህዋ ተልእኮ ይዛ ፍሎሪዳ ከሚገኘው፣ ሜሪት ደሴት ካለው የናሳ ማእከል መጠቀች። በሐምሌ ወር 1961 ዓ.ም ላይም ኒል አርምስትሮንግ፣ ኤድዊን አልድሪን እና ማይክል ኮሊንስ በአፖሎ 11 መንኮራኩር ወደ ጨረቃ የመጠቁበት ስኬታማ በረራ ተደረገ። ከአራት ቀን በረራ በኋላ ኒል አርምስትሮንግ በጨረቃ አካል ላይ በመራመድ የመጀመሪያው ሰው ሆኖ ታየ። ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ላይ የማርፍበት ክስተቱን ሲገልፀውም “ ለአንድ ግለሰብ አንድ ትንሽ እርምጃ፣ ለሰው ዘሮች ደግሞ አንድ ግዙፍ እመርታ ነው” በማለት ነበር።
በስፑትኒክ የተጀመረውን የሕዋ እሽቅድምድም ጨረቃ ላይ በማረፍ አሜሪካ በተሳካ ሁኔታ አሸንፋለች። በሶቭየቶች በኩል ከ1961 እስከ 1964 ዓ.ም መካከል ባሉት ዓመታት ጨረቃ ላይ ለማረፍ ያደረጉት ሙከራ በ1961 ዓ.ም ከመነሻው ላይ የተከሰተውን አስደንጋጭ ፍንዳታ ጨምሮ ሦስት ያልተሳኩ ሙከራዎችን አድርገዋል። ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው የአሜሪካ ሕዝብ በሕዋ ፉክክሩ ተማርኮ የነበረ እና በሶቭየት እና በአሜሪካ የሕዋ መርሀ ግብሮች አዳዲስ ለውጦች ላይ በብሔራዊ ሚዲያው ከፍተኛ ሽፋን ያገኙ ነበር። ጠፈርተኞች እንደ ብሔራዊ ጀግና ይታዩም ነበር። የሶቭየት ጠፈርተኞች ግን ሁልጊዜ አሜሪካን ለመብለጥ እና የኮሚኒስት አስተሳሰብን የበላይነት ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ ጥረት የሚያደርጉ ተንኮለኛች ተደርገው ይታዩ ነበር።
የሕዋ እሽቅድድሙ በአጭሩ የአሜሪካ መንግሥት የጨረቃ ጉዞ ፍላጎት ከ1960ዎቹ በኋላ ተዳከመ። ነገር ግን በ1967 ዓ.ም አፖሎ-ሶይዝ የተባለ ጥምር የመንኮራኩር የሕዋ ላይ ጉዞ በተደረገበት ጊዜ ሦስት የአሜሪካ ጠፈርተኞች ወደ ሕዋ ተጉዘው የነበረ ሲሆን ያረፉትም በራሺያ ሚር በተባለው የሕዋ ማእከል ነበር። እናም ሶየዝ የተባለችው ሶቭየት ሰራሽ መንኮራኩር ከአሜሪካ አፖሎ ተጓዦች ጋር ሕዋ ላይ ተገናኙ። በዚህ እጃቸውን ሲጨባበጡ የታዩት የሁለቱም በረራዎች ቡድን መሪዎች የሁለቱን ኃያላን መንግሥታት ግንኙነት ወደ በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ አካባቢ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ እንደ ማሳያ ተወስዶ ነበር። ምንም እንኳ ሁለቱ ያደረጉት ፉክክር የኃይል የበላይነት ለማግኘት ቢሆንም በመሀል ግን ቴክኖሎጅው የማደግ እድል አግኝቷል። ዛሬ የሕዋ ሳይንስ ለዓለማችን ሳይንስ መመንደግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ልብ ይሏል።
ምንጭ-history.co
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም