የሕዝብም የመንግሥትም ትልቅ ግብ

0
94

በባህላዊ መንገድ በማረስ፣ እንደ በፊቱ ዝናብን ጠብቆ በማምረት እንዲሁም  በመኸር እርሻ ላይ ብቻ በመንጠልጠል በምግብ እህል ራስን መቻል አይቻልም፡፡ እንደተለመደው በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ አምርቶ በምግብ እህል ራስን መቻል የለውጥ መንገድን አዝጋሚ ከማድረጉም በላይ ድህነትን በመለማመድ ስንፍና የተሞላበት የስራ ባህልን እንደ ማበረታታት ይቆጠራል፡፡

እንደ ዜጋ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግብርና መር ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምጣኔ ሐብት ለመገንባት እና ግብርናዉ የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል ለመጨመር ከተለመደው የመኸር እርሻ በተጨማሪ መስኖ ልማት ላይ በመሥራት ምርትን መጨመር ያስፈልጋል፡፡

ምርትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ዓይነቶችን በበቂ መጠን ማሰራጨት እና የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ማሻሻል ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡

እንደ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዘንድሮም ለ2017/18 በጀት ዓመት የምርት ዘመን የሚሆን ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ በምታስገባበት ወቅት ለከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ከመዳረጓ በተጨማሪ በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ መኖርና በወቅቱ አለመድረስ  ሌላኛው ችግር ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያን ማቀነባበር የሚያስችሉ እንደ ፎስፌት፣ ፖታሽ እና የተፈጥሮ ጋዝ ማዕድናት በበቂ መጠን እንዳላት የማዕድን እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቀደሙ ዓመታት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ታዲያ ሰሞኑን የመጣው ብስራት ይህንን ችግር የሚያስቀርና ለሀገር እድገት ትልቁን ሚና ለሚጫወተው ግብርና  ግብ መሳካት ጭምር የሚያግዝ ነው ነው፡፡

ባርባ ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው እና ከናይጄሪያው ባለሐብት አሊኮ ዳንጎቴ ጋር የተደረገው ስምምነት “ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ  ፋብሪካ ልትገነባ ነው” የሚል ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት እንደ መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ከማስቀረት ባለፈ የአፈር ማዳበሪያ እጥረትን በማስቀረት የህዝብን ጥያቄ የሚመልስ የመንግሥትንም  የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ብስራት ነው፡፡ ስለሆነም የሕዝብም የመንግሥትም ትልቅ ግብ የሆነውና ተስፋ የተጣለበት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ  እውን ይሆን ዘንድ ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በኲር የሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here