የሕይወት ግብ መዳረሻ መንገድ

0
145

ምዕራፍ ጎጃም ትባላለች፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ትምህርት ቤቱ የጀመረው የተማሪ ምገባ ፕሮግራም ብዙ አበርክቶ እንዳለው ስታስረዳ፤ “አርፋጅ ተማሪ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቤቱ ለጥዋት ፈረቃ ከአንድ ሰዓት፣ ለከሰዓት ፈረቃ ደግሞ ከአምስት ሰዓት  ጀምሮ ምግብ የሚያቀርብ በመሆኑ ሁሉም ተማሪዎች በሰዓቱ እንድንገኝ አስችሏል፡፡ ምግባችንን ተመግበን እንዳጠናቀቅን ቀጥታ ወደ መማሪያ ክፍላችን ያለምንም መንጠባጠብ በመግባት ትምህርታችንን ያለአንዳች ኮሽታ እንድንከታተል  አስችሎናል” በማለት ነው፡፡

የተማሪ ምገባው ከዚህ በፊት ያቋርጡ እና ከትምህርት ይርቁ የነበሩ ተማሪዎችን ሕይወት መታደጉንም አስታውሳለች፡፡ በተለይ ሕጻናት ከትምህርት በሚርቁበት ወቅት መዋያቸውን አልባሌ ቦታ ላይ ያደርጋሉ፡፡ ይህም ለሱስ እና ተያያዥ ችግሮች እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ከመኖሪያ ቀያቸው እንዲወጡ በማድረግም ደኅንነታቸው አስተማማኝ እንዳይሆን፣  ላለ ዕድሜ ጋብቻ  እና ለጉልበት ብዝበዛ እንዲጋለጡ የመሆን አጋጣሚያቸውም ሰፊ ነው፡፡ የተማሪ ምገባ የጀመሩ ትምህርት ቤቶች የትውልድን የነገ መዳረሻ ያስቀጥላሉ ማለት ነው፡፡

ምዕራፍ እንደምትለው የተማሪ ምገባው እርሷን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ወደ አልባሌ ቦታ እንዳይሄዱ ብቻ ሳይሆን የጊዜ አጠቃቀም በማሻሻል፣ የትምህርት አቀባበልን በማሳደግ በየዓመቱ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አስችሏል፡፡ ምገባው ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱን የምትናገረው ምዕራፍ ሩዝ፣ እንቁላል፣ ሻይ እና ዳቦ እየቀረበላቸው መሆኑን አስታውሳለች፡፡

ምዕራፍ በዚህ ዓመት የክልላዊ ፈተና ተፈታኝ መሆኗን ገልጻለች፡፡ የተሻለ ውጤት አስመዝግባ ወደ ቀጣዩ የትምህርት ደረጃ ለመሸጋገር ትምህርት ቤቱ አዘጋጅቶ ለሁሉም ተማሪዎች በሰጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እየተጠቀመች ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ እየተከናወነ የሚገኘው ምገባ ደግሞ ጊዜዋን በአግባቡ እንድትጠቀም እንደሚያግዛት ታምናለች፡፡ ምክንያቷ ደግሞ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ውጪ በሚሆኑበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ጥናት ላይ እንዳያውሉ ያደርጋቸዋል የሚል ነው፡፡ እሷም ቀሪ ጊዜያትን በአግባቡ ለመጠቀም ከትምህርት ቤት እንደማትርቅ አረጋግጣለች፡፡

ተማሪ ምዕራፍ የትምህርት ቤት የተማሪ ምገባው በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ቤተሰብ ልጆች እና በጸጥታ ችግሩ ምክንያት በመሸኛ መጥተው መኖሪያ  ተከራይተው  ለሚማሩ ተማሪዎች ትልቅ እፎይታ መሆኑን ታምናለች፡፡ በተለይ ምግብ አብስለው የማያውቁ ተማሪዎችን እንደታደጋቸው፣ ወጪም እንዲቀንስላቸው እንዳደረጋቸው ከክፍል ጓደኞቿ ተረድታለች፡፡ እነዚህ ተማሪዎች አብስሎ የመመገቢያ ጊዜያቸውን ለጥናት በማዋል የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አግዟቸዋል የሚል እምነት አላት፡፡

አዲሡ ተስፋ ክልሉ ባጋጠመው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ከሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን አቸፈር ወረዳ ሊበን ከተማ ወደ ባሕር ዳር ከተማ መጥቶ በቁልቋል ሜዳ ትምህርት ቤት ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ የሚያስችል የምገባ ፕሮግራም ማስጀመሩ ለእርሱ እና ለሌሎች ትልቅ እገዛ ነው፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ እንደወጣ የሚናገረው ተማሪው፣ ትምህርቱን ወደ ባሕር ዳር ከተማ መጥቶ ለማስቀጠል ሲያስብ የቤት ኪራይ፣ የምግብ እና ሌሎች ከትምህርት ግብዓት ማሟላት ጋር የተያያዙ ወጪዎች አሳስቦት እንደነበር አስታውሷል፡፡ ይሁን እንጂ የቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጀመረው የተማሪ ምገባ ቢያንስ ለቀለብ የሚያወጣውን ወጪ ቀንሶለታል፡፡ በዚህም ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡

አዲሱ  የተጀመረው ምገባ ከወጪ ቅነሳ በተጨማሪ የትምህርት ጊዜን በአግባቡ ተከታትሎ ዓመቱን በድል ለማጠናቀቅ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጭምር ጠቁሟል፡፡ ጥዋት እና ምሳ ሰዓት ምግብ ስለመሥራት ይታሰብ የነበረውን ሐሳብ እና የጊዜ ብክነት በእጅጉ ይታደጋል፤ እነዚህን ጊዜያት ለጥናት እንዲያውላቸው አስችሎታል፡፡ በዚህም በዓመቱ በክልሉ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቦ ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ ለመሸጋገር ያለመውን ራዕይ ለማሳካት እንደሚያግዘው ጠቁሟል፡፡

“ምንም ሳይኖራቸው ለትምህርት ያለኝን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ተረድተው እያስተማሩኝ ያሉ ቤተሰቦቼ እና ምገባው ከመማር ማስተማር ውጪ የሆኑ ጊዜያትን ከትምህርት ቤት ሳልርቅ እንድጠቀም የሚያደርገኝ በመሆኑ የነገ መዳረሻዬ ጉልበት ናቸው” በማለት ተናግሯል፡፡

የተማሪ ምገባው በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሊሰፋ እንደሚገባ አዲሡ ጠይቋል፡፡ አቋራጭ ተማሪዎች እንዳይኖሩ፣ ተማሪዎች የትምህርት ክፍለ ጊዜን ባለማቆራረጥ ሁሉንም የትምህርት አይነት ይዘቶች በሚገባ መከታተል እንዲችሉ ለማድረግ ከፍተኛ አበርክቶ ያለው በመሆኑ ሁሉም አቅም ያላቸው ወገኖች የተማሪ ምገባን ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የቁልቋል ሜዳ አንደኛ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት ከዚህ ቀደም የወተት ላም በማርባት ለተማሪዎች ለተማሪዎች የወተት ምገባ ያከናውን ነበር፡፡ የወተት ላሞቹ ከዓመታት በፊት መሸጣቸውን ከትምህርት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ከወተት ውጪ የሩዝ፣ እንቁላል እና ሻይ በዳቦ የምገባ ፕሮግራም እያከናወነ ይገኛል፡፡

የተማሪ ምገባው ባለፈው ዓመት ተቋርጦ እንደ ነበርና እንደ ገና በዚህ ዓመት መጀመሩን የነገሩን በትምህርት ቤቱ የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህር መምህሩ አበባው ሽፈራው ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት መቋረጡን ተከትሎ ቁጥራቸው ውስን የማይባሉ ተማሪዎች በወርሀ መስከረም የጀመሩትን ትምህርት ሳያስቀጥሉ መክረማቸውን አስታውሰዋል፡፡ ማሳያ ያደረጉትም ከግማሽ በታች ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኙ እንደ ነበር ነው፡፡

በዚህ ዓመት በካርተር ሴንተር ኢትዮጵያ አማካኝነት እንደ ገና መጀመሩን አቶ አበባው አስታውቀዋል፡፡ በምገባውም 1 ሺህ 736 ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተነስቷል፡፡

አቶ አበባው የተጀመረው የተማሪ ምገባ ፋይዳው ከቃል በላይ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህን ተከትሎም  የተማሪ መጠነ ማቋረጥ በእጅጉ እንዲቀንስ፣ አርፋጅ ተማሪ እንዳይኖር፣ ተማሪዎች በየክፍላቸው በንቃት እንዲከታተሉ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡ ምገባ የተማሪዎች የትምህርት አቀባበል እና ውጤት እንዲሻሻል ማድረጉን በክትትል ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቱ የቆይታ ጊዜውን አጠናቆ መውጣቱን መምህሩ ገልጸዋል፡፡፣ በአሁኑ ወቅት ምገባውን እያስቀጠለ ያለው ትምህርት ቤቱ በራሱ አቅም 100 ሺህ ብር በጅቶ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በፊት ለወተት ላሞች ማደሪያ የነበሩ ቤቶችን በማከራየት ለምገባው እንደተጨማሪ ገቢ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡ የተማሪ ምገባው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በዘላቂነት ይቀጥል ዘንድ ባለሐብቶች፣ ረጂ ድርጅቶች እና ግለሰቦች እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡

በአጠቃላይ  የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ የተማሪ ምገባ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አካሂዶት በነበረው 6ኛ ዙር አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ አስታውቀዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግም በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህም በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ ያሉ ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይርቁ የሚያደርግ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡

ምክር ቤቱ ጉባኤውን እስከ አካሄደበት ወቅት ድረስ 61 ትምህርት ቤቶች እና 145 ሺህ 45 ተማሪዎች በምገባ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ከዕቅዱ አንጻር ሲታይ 14 ነጥብ 5 በመቶ ነው፡፡ ይህም እጅግ ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት ሆኖ ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here