“የሕዳሴው ግድብ የሞራል ልዕልናን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያቅፍ ነው” የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

0
141

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከ60 ሚሊዮን በላይ የሀገራችን ነዋሪ የኤሌክትሪክ መብራት ተጠቃሚ አይደለም። ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነት ክር ያስተሳሰረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደግሞ ይህን ችግር ያስቀራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው። በተከታታይ ዓመታት የውኃ ሙሌቱ በስኬት ተካሂዶም የተወሰኑት ተርባይኖች ብርሃን መስጠት ጀምረዋል። የዓባይ ወንዝ ባይተዋርነትንና “ኦባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” ተረትን የቀየረና መላውን ኢትዮጵያዊ ያስተሳሰረ ገመድም ሆኗል::

ታላቁን ግድብ በተመለከተ ፕሬዘዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የጋራ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ96 ነጥብ 7 በመቶ በላይ ተጠናቅቋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም 5 ሺህ 259 ሜጋ ዋት መድረሱንም ተናግረዋል::

የኢነርጂ መሠረት ልማትን ለማስፋፋት አያሌ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ፕሬዘዳንቱ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እና ሽፋን ጭማሪ ማሳየቱንም አክለዋል::

ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መከናወኑ ይታወሳል። ግንባታውም ከ96 ነጥብ 7 በመቶ በላይ መጠናቀቁን አስታውቀዋል:: “በ2016 በጀት ዓመት የግድቡ የሲቪል ግንባታ ሥራም ሙሉ በሙሉ አልቋል” ሲሉ አክለዋል። ለዚህም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሚና የጎላ እንደነበር ነው ያመላከቱት። “ለግድቡ እዚህ መድረስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሚና የላቀ ነው:: በታሪክም በወርቅ ቀለም ይጻፋል” ብለዋል::

እንደ ፕሬዘዳንቱ ማብራሪያ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ማሳያ ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻም አይደለም፤ የዘመናት ህልም ወደ ሚጨበጥ ዕውነት የተቀየረበት ነው። “የራሳችንን የዕድገት ህልም በራሳችን አቅም መፍታት እንደምንችል ያሳየንበት ነው” ብለዋል::

ዓመቱ የኢትዮጵያ አሸናፊነት ዓመት እንደነበር በማንሳት የሕዳሴ ግድብ ቱሪዝምን፣ የውኃ ሃብትን፣ የአካባቢ ሚዛን መጠበቅን፣ የሞራል ልዕልናን እና የኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ሁሉ የሚያቅፍ እንደሆነ ነው ያብራሩት።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ጥቅምት 4  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here