ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር )
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል:: ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እና የአፈር ማዳበሪያን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከል ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙ ፈተና የታየበት፣ አንድም ብር ከውጭ ብድር ያልተገኘበት፣ ከወደብ እስከ ግድቡ ድረስ ግብዓትን አጅበን እየወሰድን የሠራነው ነው” ብለዋል::
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላው አፍሪካ ኩራት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህም “ለመላው አፍሪካ መቻልን ያሳየንበት፣ ስህተትን እና በውስጣችን ያለውን ውድቀት ያረምንበት ነው” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቀጣዩ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያን ማምረት አለመቻሏ ለብዙ ችግሮች እንዳጋለጣትም አብራርተዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት ሲደረግ እንደነበርም ተናግረዋል::
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካውን አቋቁሞ ለመሥራት በትንሹ ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠቁመዋል:: የአፈር ማዳበሪያ የኢትዮጵያን ፍላጎት በሚመልስ መልኩ መመረት እንዳለበት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፋብሪካውን የማቋቋም ሂደቱ ምናልባትም በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊጀመር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ይታወቃል፤ በጥቂት ወራት ውስጥም “በታላቁ ግድብ ሪባን እንቆርጣለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር::
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም