የሕግ የበላይነት ማለት በሕግ መሠረት መገዛት እና መተዳደር ማለት ነው:: በዚህ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ:: በሕግ መሠረት መገዛት ሲባል በምን ዓይነት ሕግ? የሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ ነው::
ሕግ ማለት በአንድ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች መብትና ጥቅማቸው የሚረጋገጥበት እና በሁሉም ሊከበር እና ሊፈፀም የሚገባ ስርዓት ነው:: ከሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕገ መንግሥት ጀምሮ አዋጆችን፣ ደንቦች እና መመሪያዎችን ያጠቃልላል::
የሕግ የበላይነት ትርጉም
በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን…..በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አንድ ፓለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት ነው” በሚል የሕግ የበላይነት ለሀገር ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ገልጿል :: ሆኖም ግን የሕግ የበላይነት የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ሰነዶች ቢጠቀስም ስምምነት ላይ የተደረሰበት አንዳች ትርጉም ሲሰጠው አይስተዋልም::
ዊሊያም ጋርድነር የተባለ የሕግ ምሁር የሕግ የበላይነት ታሪክ እና አላባዊያን (THE HISTORY AND ELEMENTS OF THE RULE OF LAW) በተሰኘው መጽሐፍ ላይ “የሕግ የበላይነት ማለት የመንግሥት አካላት፣ ባለሥልጣናት (ሠራተኛውን ጭምሮ) እና ዜጎች በሕግ ጥላ ስር ሲወሰኑና ሲያከብሩ ነው” ይላል::
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2014 እ.ኤ.አ ለፀጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፓርት፤ “የሕግ የበላይነት የአስተዳደር መርህ ሲሆን ሁሉም ሰው፣ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በግልፅ በፀደቀ፣ ያለአድሎ በእኩል በሚፈፀም፣ በገለልተኛ ፍርድ ቤት በሚተረጎም እና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነዶች ጋር በተጣጣመ ሕግ ተጠያቂ መሆንን የሚያመለክት መሆን አለበት:: ይህ ሲሆን ደግሞ ተጠያቂነትን፣ ርትዕን፣ ተገማችነትን፣ የሥልጣን ክፍፍልን፣ ውሳኔ ሰጪነት ተሳታፊነትን፣ የዘፈቀደ አሠራርን ለማስወገድ እና የሕግ እና የሥነ ስርዓት ግልፀኝነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሂደት እና ጥረት ይጨምራል” በማለት ተንትኗል::
ጽንሰ ሀሳቡን የሚያጠኑ የሕግ ልሂቃን ከላይ ከተጠቀሱት ትርጉሞች አንፃር እይታቸውን ሕጋዊነትን መሰረት ያደረገ ዝቅተኛው እይታ እና መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን ያካተተ የሕግ የበላይነት በሚል በሁለት ከፍለውታል::
ሕጋዊነትን መሰረት ያደረገው ዝቅተኛው የሕግ የበላይነት እይታ ዊሊያም ከሰጠው ትርጉም ጋር ተመሳሳይ ነው:: ሕግ መሠረታዊ የአሥተዳደር መሣሪያ ሲሆን ግልፅ ፣ ተደራሽ፣ ተገማች ፣ የማይለዋወጥ እና ወደ ፊት የሚፈፀም መሆን እንደሚገባው ይገልጻል:: መሠረታዊ ፍሬ ነገሮችን መሠረት ያደረገው የሕግ የበላይነት እይታ አንድ ሕግ ተቀባይ ለመሆን ከሥነ ሥርዓታዊ መስፈርቶች በተጨማሪ የሞራል ቅቡልነት ያለው ፣ ሰብዓዊ መብቶችን እና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ያከበረ መሆን ይገባዋል የሚል ነው::
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አንድ ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም የባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሌለው በመደንገግ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ገደብ አስቀምጧል:: ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው መንግሥት ምንም እንኳ ሕጋዊ መስፈርቶችን ያሟላ ሕግ ቢያወጣም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ካላከበረ ሕጉ ተፈፃሚነት የለውም::
ይህም ሲባል መንግሥት አላማውን ለማስፈፀም ወይም ለአገዛዝ እንዲመቸው መሠረታዊ ፍሬ ነገሮችን ያላከበረ እና መደበኛ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትን ያልተከተለ ሕግ ሊያወጣ እንደሚችል ashamlaws.wordpress.com ዘገባ ጠቁሟል:: ለአብነት የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ስርዓት በሕግ የተደገፈ ነበር:: ሕጎቹ መሰረታዊ የሕግ መርሆችን እና ሀገሪቷ የተቀበለቻቸውን ዓለማቀፍ አስገዳጅ ለሰው ልጆች የሚገቡ ሰብአዊ መብቶችን በተከተለ መንገድ እንዲሆን ይጠበቃል:: እነዚህ ሕጎች የሕዝቡን እና በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን የሚመለከቱ አጠቃላይ ጉዳዮችን የሚገዙ ናቸው:: ከነዚህም ውስጥ ሥርዓተ መንግሥትን፣ የመንግሥት አሥተዳደር ሁኔታን፣ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እና በተወካዮቹ አማካኝነት እንዴት እንደሚገዛ፣ እንደሚተዳደር፣ የምርጫ ሥርዓቱን፣ መብቶቹን፣ መብቶቹ የሚጥሱ ሰዎችም እንዴት በወንጀል እንደሚጠየቁ፣ ውሎች በምን መልኩ እንደሚፈፀሙ እና እንደሚከበሩ፣ የንግድ ሥርዓቱ እንዴት እንደሚመራ፣ የቤተሰብና ጋብቻ ሥርዓት እንዴት እንደሚጠበቅ…የሚጠቀሱ ናቸው::
የሕግ የበላይነት የመንግሥትን የዘፈቀደ የሥልጣን አጠቃቀምን ለመገደብ፣ የዜጎችን የንብረት፣ የነፃነት እና የሕይወት መብት በሌሎች እንዳይጣስ ጥበቃ ለማድረግ ይረዳል::
በአንድ ሀገር ውስጥ የሕግ የበላይነት ስለመኖሩ ማረጋገጥ የመሆኑ መገለጫ አላባውያን የተለያዩ ቢሆንም በዓለማቀፍ ደረጃ የሕግ የበላይነትን የሚያከብሩ ሀገራትን ደረጃ (rule of law index) የሚያወጣው ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፕሮጀክት የሚጠቀምባቸውን አምስት መለኪያዎች እንዳሉ መረጃው ጠቁሟል::
በሕግ የተገደበ የመንግሥት ሥልጣን
የመንግሥት፣ የባለሥልጣናቱ እና እንደራሴዎቹ ሥልጣን መገደብ ወይም መወሰን አለበት የሚለው የሕግ የበላይነት መለኪያ መስፈርት አንዱ ነው:: ዋና አላማውም መንግሥት በዘፈቀደ ያለገደብ ልጓም እንደሌለው ፈረስ የሚፈነጭ ከሆነ የዜጎችን መብት በመጨፍለቅ ጨቋኝና አምባገነን ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው:: መንግሥት መጠቀም ያለበት የሥልጣን መጠን የሀገርን እና የዜጎችን ሰላም፣ ደህንነት እና መብት አክብሮ ለማስከበር በሚያስችል መልኩ መሆን ይገባዋል ::
መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባራት በሚፈፅምበት ወቅት በሕግ በተቀመጡ አሠራሮች አግባብ መሆን ይገባዋል:: ይህን ከተቃረነ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል:: በተጨማሪም ሕጉን ለመቀየር ወይም ለማሻሻል ፍላጎት ቢያድርባቸው ሕግ የማውጣት ሥልጣንን የሚገድቡ ወሰኖችን በመጣስ ሊሆን አይገባም::
የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ ዘጠኝ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም:: ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ሕግ አውጪው የሚያወጣው ሕግ ወይም ሕግ አስፈፃሚው የሚወስነው ውሳኔ ወይም ሕግ ተርጓሚው አካል ሕግ ሲተረጉም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ማክበር እንዳለበት በሥልጣናቸው ላይ ገደብ አስቀምጧል:: ይህን ገደብ የጣሰ ሕግ፣ ውሳኔ እና የሕግ ትርጉም ተፈፃሚነት የለውም:: የመንግሥት አካላት በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን ብቻ እየሠሩ ስለመሆኑ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሚያሰፍን የቁጥጥር ማድረጊያ መንገድ ሊኖር ይገባል::
የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 12 ማንኛውም ኃላፊ እና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን ይደነግጋል:: ተጠያቂ ከሚደረግባቸው መንገዶች መካከል የሦስቱ የመንግሥት አካላት የእርስ በርስ ቁጥጥር መኖር ለምሳሌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 (17 እስከ 18) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈፃሚውን አካል የሚቆጣጠሩበትን አግባብ ደንግጓል:: ለሲቨል ማህበራትና ለሚዲያ ተጠያቂ በመሆን፣ የመንግሥት ስልጣን በሕግ አግባብ ብቻ እንዲተላለፍ በማድረግ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ ቁጥር ሦስት ሰፍሯል::
ሕጋዊነት
የሕግ የበላይነት ማረጋገጫ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል ሌላው የሕጋዊነት መርህ መኖር ነው:: አንድ ሕግ ከረቂቅ ጀምሮ ፀድቆ ተግባር ላይ በሚውልበት ወቅት ተደራሽ መሆኑ፣ ሕጉ ግልፅና በቀላሉ የሚረዱት መሆኑ፣ ለውጥን የሚያስተናግድ፣ ተገማች የሆነ፣ ሊፈፀም የሚችል፣ በሁሉም ላይ በእኩል ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ እና ማስፈፀሚ ሥርዓትና ተቋም ሊኖር ይገባል የሚል ነው:: አንድ የሕግ ሥርዓት እነዚህን መስፈርቶች የማያሟላ ከሆነ መንግሥት እና ዜጎች ለሕጉ ይገዛሉ ተብሎ አይጠበቅም::
ይህ መርህ መከበሩ ዜጎች ባልወጣ ሕግ እንዳይቀጡና የወጡትንም ሕጎች አክብረው የእለት ተዕለት ሕይወታቸውን እንዲመሩ ይደረጋል:: ሕጉም ተገማች በመሆኑ ግብይት እንዲሳለጥ ያደርጋል:: ምክንያቱም ትርፍና ኪሳራቸውን አስልተው እንዲገበያዩ ያስችላቸዋል:: ለምሳሌ የውል ሕግ በመኖሩ ዜጎች ያለ ስጋት በነፃነት እንዲገበያዩ ዋስትና ይሰጣቸዋል:: ውሉን ያላከበረ ተገዶ እንዲፈፅም ወይም ካሳ እንዲከፍል ስለሚደርግ ለሌላኛው ወገን ዋስትና ይሆናል::
የንብረት ሕግ ዜጎች ገንዘባቸውን ፣ እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን አውጥተው ያፈሩትን ንብረት በነፃነት እንዲጠቀሙ ጥበቃ ያደርጋል:: የዚህ መርህ መስፈርቶች ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ተደንግገው ይገኛሉ:: ስለመንግሥት አሠራር ግልፅነት እና ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆንን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ንዑስ ቁጥር አንድ እና 25 እንደቅደም ተከተላቸው ተደንግገዋል::
ገለልተኛ እና ነፃ የዳኝነት አካል
ነጻ የሆነ ፍ/ቤት የሕግ በላይነት መሠረታዊ ገፅታና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መኖር ቅድመ ሁኔታ ነው:: የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛው ባሕሪ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች መከበር እና መረጋገጥ ነው:: መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች በሕገ-መንግሥት ወይም በሌላ ሕግ መደንገጋቸው ብቻ በራሱ ለመብቶች መረጋገጥ ዋስትና ሊሆን አይችልም:: እነዚህ መብቶች እውን ይሆኑ ዘንድ ነፃ ፍ/ቤት መኖር አለበት:: ነፃነት የሌለው ፍ/ቤት የሰዎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲረጋገጥ ሊያደርግ አይችልም::
በዜጎች እና በመንግሥት እንዲሁም በሰዎች መካከል ባሉ ግንኙነቶች ሳቢያ የሚነሱ የፍትሐብሔር ወይም የወንጀል ክርክሮችን ገለልተኛ እና ነፃ ሆኖ እልባት ሊሰጥ የሚችል ፍ/ቤት በሌለበት የሕግ በላይነት ሊረጋገጥ አይችልም:: የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና መልካም አስተዳደር እውን ሊሆኑ አይችሉም:: ሰላምና ዘለቄታ ያለው ልማትም ዋስትና አይኖረውም::
የዳኝነት ነፃነት ለኢንቨስትመንት እና ለኢኮኖሚ እድገት መሠረት ነው:: ባለሃብቱ በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት እንዲኖረው በአንድ ሀገር ውሰጥ የዳኝነት ነፃነት መስፈንና መረጋገጥ ወሳኝ ነው:: ስለዚህ ስለዳኝነት ነፃነት አስፈላጊነት ላይ ምንም ክርክር የለውም:: የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 78 እና 79 ነፃ የዳኝነት አካል እንደተቋቋመ እና በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣንም ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተፅእኖ ነፃ መሆናቸው እና ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት በሕግ በመመራት እንደሚያከናውኑ ተደንግጓል:: ጥያቄው ያለው የዳኝነት ነፃነት ስፋትና እና ተግባራዊ አፈፃፀሙ ላይ ነው::
ሰላም፣ ሥርዓት እና ደኅንነት
የአንድ ሀገር መንግሥት ፣ ሕዝብ እና ነዋሪዎች ሰላም ፣ ደኅንነት፣ ሥርዓት መብት እና ጥቅም መከበር እና መረጋገጥ የሕግ የበላይነት ዋነኛ ገፅታ ነው:: ዘላቂ ዋስትና ያለው ሰላም ለማረጋገጥ የሚቻለው በሀገራዊ ደኅንነት፣ በመንግሥት እና በሕዝብ ጥቅም፣ በግለሰቦች ደህንነትና መብት ላይ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች፣ ዝግጅቶችን እና ሴራዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ሲቻልና ወንጀሎቹ ከተፈፀሙ አጥፊዎችን በሕግ ሥርዓት ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረብና ማስቀጣት ሲቻል ነው::
የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እና ማንኛውም ሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን በሕገ መንግሥቱና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችና ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ የማከናውን ባህል ሲዳብር የምርጫ ውድድሮችን ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ሕግና ሥርዓትን መሠረት በማድረግ የሚከናወኑ መሆን ይገባቸዋል::
መንግሥት ሰላም እና ደህንነትን ለማስጠበቅ መብት አለው:: መንግሥት ሀገረ መንግሥቱ የቆመበትን ሥርዓት እና ደህንነት ማስከበር አለበት ሲባል ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት የመከላከል ሥራ መሥራት፣ ፓለቲካዊ ግጭቶችን (ሽብርተኝነት፣ አለመረጋጋትን፣ በታጠቁ ኀይሎች መካከል የሚደረግ ግጭትን) ውጤታማ በሆነ መልኩ መቀነስ እና የግል ችግርን ወይም በደልን ለመወጣት መደበኛውን የሕግ ማስከበር ሥርዓት ከመከተል ይልቅ ኀይልን መጠቀም ማህበራዊ ተቀባይነት ያለው አድርጎ አለመፈፀም ለምሳሌ የደቦ ፍትሕ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው::
ሰብዓዊ መብት እና ነፃነት መከበር
ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው:: የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የዜጎች ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩ ስለመሆኑ በመሠረታዊ መርህነት የተደነገገ ከመሆኑም በላይ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል ሕግ አውጭ፣ አስፈፃሚና የዳኝነት አካል በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት በተካተቱ የሰብዓዊ መብትና መሠረታዊ ነፃነቶች ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው ስለመሆኑ በአንቀጽ 13 ንኡስ ቁጥር አንድ ተደንግጓል::
መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታ የሚወጣው አስፈላጊውን የሕግ ፣ የአስተዳደርና ሌሎች እርምጃዎች በመውሰድ ነው:: መንግሥት ከዜጎቹ ጋር ባለው የቀጥታ ግንኙነት እንዲሁም ዜጎች ባላቸው የእርስ በርስ ግንኙነት አንዱ የሌላውን መብት የማክበር ግዴታ አለበት:: በመሆኑም የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን አላግባብና ከሕግ ውጭ በመጠቀም የሚፈፀሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድርጊቶችን እንዲሁም ሰዎች ባላቸው የጎንዮሽ ግንኙነት አንዱ የሌላውን መብትና ነፃነት የሚጥሱ ድርጊቶች የወንጀል ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚያስከትሉ ድርጊቶች መሆናቸው ተደንግጓል:: በመከላከል እና ጥሰቱ ተፈፅሞ ሲገኝ በተሟላ ሁኔታ በወንጀል ፍትሕ ስርዓቱ እንዲፈፀም በማድረግ መንግሥት ሰብዓዊ መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታውን በመወጣት የሕግ የባለይነትን ማረጋገጥ እንዳለበት መረጃዎች አረጋግጠዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም