የሕጻናት ቀን

0
31

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ስለ ሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ምን ታውቃላችሁ? ስለ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን እንገራችሁ፡፡

ልጆች፣ ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀንበዓለም አቀፍ ደረጃ 36 ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 20 ጊዜየሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናትበሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙ ሕጻናት በመጫወቻ ቦታ ተጫውተዋል። በመድረኩ የቀዳማይ ልጅነት ዘመን እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሑፍ ቀርቧል። የተማሪዎች የጥያቄ እና መልስ ውድድርም ተካሂዷል።

የበዓሉ ተሳታፊ ሕጻን ሐብታሙ መልኬ በዓሉን በተለያዩ ጨዋታዎች እና በጥያቄ እና መልስ ውድድር መሳተፉን እና ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።  የአማራ ክልል የሕጻናት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሕጻን ተምኪን ይሃ ሕጻናት የመጫወት እና ጥበቃ የማግኘት መብት አላቸው ብላለች። ጨዋታ ልጆች ከሰዎች ጋር ያላቸውን ተግባቦት እና የስሜት ልህቀት የሚያሳድጉበት በመሆኑ የተሟላ ዕድገት እና ደኅንነት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስታለች። ስለዚህ ልጆች የልጅነት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲያሳልፉ የመጫወቻ ቦታዎች ሰላማዊ እና ከአደጋ የራቁ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ በዓሉ በየደረጃው በተለያዩ ዝግጅቶች በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳዎች እና በዞኖች ሲከበር ቆይቷል ብለዋል።  በክልሉ በርካታ ሕጻናት በችግር ውስጥ ሆነው የሚማሩ፣ ትምህርት የማያገኙ እና ጥቃት የሚደርስባቸው አሉ ብለዋል። ስለዚህ ይህ በዓል በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሠሩ ሥራዎችን በማጠናከር ሕጻናት ደኅንነታቸው፣ ጤንነታቸው እና አካላዊ ብቃታቸው የተጠበቀ ሆነው እንዲያድጉ ብዙ ሥራዎች እየተሠራበት መሆኑን ተናግረዋል።

ሕጻናት የዴሞክራሲ ሥርዓት መብታቸውን እንዲለማመዱ በሕጻናት ፓርላማ እየተሠራ ነው ብለዋል። ለሕጻናት ጤናማ እና ለኑሮ ምቹ፣ ተስማሚ አካባቢ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ መሠራት ስላለበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይሕጻናት የአንድ ሀገር የወደፊት ተስፋ እና ሀብት ናቸው ብለዋል። ሀገር ተረካቢ ሕጻናት ላይ መሥራት በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በማኅበራዊ ኑሮ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡

ተረት

ድመት እና ቀበሮ

ከዕለታት አንድ ቀን ድመት አንድ ጫካ ውስጥ ቀበሮ ታያለች:: ከዚያም ለራሷ እንዲህ ትላለች፡- “ቀበሮ በጣም ቀልጣፋ ነው:: ብዙ ልምድ ያለው ነው:: በሰፊውም የተከበረ ነው:: ስለዚህ መልካም ሰላምታ ላቅርብለትና ልቀርበው ይገባል”:: ቀጥላም፣ “እንደምን አደርክ አያ ቀበሮ! እንዴትስ ከርመሀል? ለመሆኑ ሁሉ ነገር በጣም በተወደደበት በዚህ በአሁኑ ጊዜ ኑሮን እንዴት ተቋቋምከው?”

ይሄኔ ቀበሮ በጣም እየተኩራራ ተጎማለለ:: ድመቷንም ሽቅብ ቁልቁል እያየ ገረመማት:: ከኩራትና ከእብሪቱ የተነሳም ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ መስጠት ብዙ ጊዜ ፈጀበት:: በመጨረሻም እዲህ አላት፡- “አንቺ ምስኪን ጢም-ላሽ ፍጥረት! አንቺ የቤት አሽከር! ደካማ፣ የአይጥ-አባራሪ! ማነሽና ነው እኔን የተከበርኩትን ቀበሮ ኑሮ ከበደህ ወይ የምትይኝ? ማነሽናስ ነው የኑሮ ውድነቱን ተቋቋምከው ወይ? ብለሹ የምትጠይቂኝ? ለመሆኑ እስከዛሬ ድረስ አንቺ ምን ተምረሻል? በምንስ ጥበብ ሰልጥነሻል? ምን ችሎታ አለሽ?”

ድመቲትም፣ ትህትና በተላበሰ ቃና፤ “አንድ ጥበብ ብቻ ነው ያለኝ” አለችው::

አያ ቀበሮም፣ “ምን ጥበብ ትችያሽ? ተናገሪ እስቲ?” አለና ጠየቃት::

ድመቲትም፣ “ውሾች ድንገት መጥተው ሲያባርሩኝ ፈጥኜ ዛፍ ላይ እወጣለሁ:: ይሄ ነው ጥበቤ”

ቀበሮም በጣም በኩራት ተነፋፍቶ “ይሄ ብቻ ነው እንዴ ችሎታሽ? ጥበብሽ ይሄ ብቻ ሆኖ እንዲህ በአደባባይ ስትፎክሪ መሰማትሽ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው:: ጉረኛ ነሽ! እኔን ስላላየሽ ነው:: እኔ ከመቶ በላይ ጥበብና ችሎታ አለኝ:: ከዛ በተጨማሪም አንድ ከረጢት ሙሉ ዘዴና ስልት አለኝ:: እኔ አንቺን ከልቤ እወድሻለሁ፤ ነይ፤ ነይ አብረን እንሂድና ከውሾች የምታመልጪበትን ዘዴ አስተምርሻለሁ” አላት::

በድንገት ከየት መጣ ሳይባል አንድ አዳኝ ይመጣል:: አራት ትላልቅ አዳኝ – ውሾች ይዟል::

ይሄኔ እመት ድመት በከፍተኛ ፍጥነት ተቀላጥፋ ዛፍ ላይ ትወጣለች:: በቅርንፎቹም ተንጠላጥላ ሙሉ በሙሉ በቅጠሎቹ ተሸፋፍና ተደብቃ ትቀመጣለች:: ቅጠላ -ቅጠሎቹ መካከል ሆና፣ “አያ ቀበሮ፤ ቦርሳህን ክፈተው:: ቶሎ ብለህ ቦርሳህን ክፈትና ከዘዴህ አንዱን አውጥተህ ተጠቀም” እያለች ትጮህ ጀመር:: ግን ምን ያደርጋል አያ ቀበሮ ምንም ማድረግ አልቻለም::

“አሁን የገባህበትን አጣብቂኝ ተመልከት:: አጠራቅሜያለሁ ካልካቸው ከመቶ በላይ ዘዴዎች አንዱን እንኳ ስራ ላይ ሳታውል ፈፅሞ ከማትወጣበት ችግር ውስጥ ገባህ:: እኔ ከልቤ አምኜ የያዝኳትና በረዥም ጊዜ ልምድ የተካንኳትን ሀቀኛና ፈጣን ዘዴ ተጠቀምኩ:: ዛፍ የመውጣት ዘዴ ብታውቅ እንደዚህ ሆነህ አትቀርም ነበር” ብላው የበለጠ ጥቅጥቅ ወዳለ ቅጠላ – ቅጠል ውስጥ ገብታ ስታበቃ በመጨረሻ አዳኙና ውሾቹ ሲሄዱ ወረደች ይባላል::

ሞክሩ

ውኃ ውስጥ እየታየ የማይረጥብ ምንድን ነው?

እናት ቤት ጠባቂ ልጅቱ ዙዋሪ ምንድን ናት?

እየደነሰች ታረግዛለች?

 

መልስ

ነፀብራቅ

የቤት ቁልፍ

እንዝርት

ነገር በምሳሌ

ሐሰት አያድንም፤ መራቆት መልክ አያሳምርም፡፡

ሐሰትመናገር ከችግር አያድንም፡፡

 

መልካም አባት እጁን በልጁ ኪስ ይከታል፡፡

ለልጁ ያስባል፤ ይጨነቃል፤

 

ሥርዓት ያናግራል፤ እርቅ ያፋቅራል፡፡

ሁሉም ነገር በአግባቡ ሲሆን ያስደስታል፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የህዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here