“አንዳንድ የዐይን በሽታዎች ከበድ ያለ ራስ ምታት ፣ ማቅለሽለሽ አንዲሁም ማስታዎክ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ይሄም ብዙ ጊዜ የዐይን ችግር ነው ተብሎ ስለማይገመት ዐይናቸውን የታመሙ ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ ችግራቸው ሳይታዎቅ በሕመም እና በስቃይ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡” ያሉን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በዐይን ሕክምና ማዕከል የሕጻናት ዐይን ሕክምና ፤ የዐይን መንሸዋረር አንዲሁም የዐይን ነርቭ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር ዳግማዊ አበበ ናቸው፡፡
ዶ/ር ዳግማዊ አበበ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት የዐይን ህመም አንደ ህመሙ አይነት እና መጠን በታካሚዎች ዘንድ በብዙ መልኩ ይገለጻል፡፡ ብዙ አይነት የዐይን ህመም ምልክቶች መኖራቸውንም ጠቅሰውልናል፡፡ ለአብነት ዐይን ከመጠን ያለፈ መቅላት፣ መቆርቆር ወይም የማቃጠል ስሜት፣ ማሳከክ ፣የእይታ መቀነስ፣ ብዥታ፣ ነገሮችን በጣም አቅርቦ ወይም አርቆ ማየት፣ አንድ ነገር ሁለት ሆኖ መታየት፣ የዐይን መወጠር ፣ በታደጋጋሚ መጋጨት ወይም መውደቅ፣ ሰዎችን ለይቶ አለማወቅ፣ ቆየት ላለ ጊዜ ዐይን ለዐይን መተያየት አለመቻል፣ እባጭ መታየት፣ ከመጠን ያለፈ ፈሳሽ መውጣት፣ መንሸዋረር፣ ነጭ ጠባሳ መሰል ነገር መከሰት፣ ቆቡ መውረድ እና እንደልብ አለመዘጋት እና ማንቀሳቀስ አለመቻል፣ በእይታ ላይ እንደ ጥላ ወይም ሸረሪት መሳይ ነገሮችን ማየት፣ ማታ ላይ በደንብ አለማየት፣ ከልክ በላይ እምባ ማውጣት እና ብርሃን መፍራት እንዲሁም በተደጋጋሚ ዐይናችንን በጣታችን መጠንቆል ካለ ዐይን ታመመ ወይም ከዚህ በፊት ህመም ተከስቶበት ነበር ሊባል እንደሚችል ዶ/ር ዳግማዊ በዝርዝር ነግረውናል፡፡
መግቢያችን ላይ እንደጠቆምነው አንዳንድ ጊዜ የዐይን በሽታ ምልክቶች ከዐይን ውጪ በሌሎች የሰውነታችን ክፍሎች ይከሰታሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን በታካሚው ላይ ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ ለዐይነ ስውርነት የመዳረግ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ሕጻን እንዲሁም እድሜዉ ከ 40 ዓመት በላይ የሆነ ሰው የዐይን ህመም ኖረውም አልኖረውም ከተቻለ በዓመት አንድ ግዜ የዐይን ምርመራ ሊያደርግ እንደሚገባ ዶ/ር ዳግማዊ መክረዋል፡፡
የዘርፉ ባለሙያ እንዳሉት ሕጻናት ዐይናቸው በሚታመምበት ጊዜ ከምልክቶቹ አንዱን ወይም ከአንድ በላይ ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ ልክ እንደ አዋቂዎቹ ሁሉ ሕጻናትም በተለያዩ የዐይን በሽታዎች ይጠቃሉ የሚሉት ባለሙያው፤ ከነዚህም መካከል አሳሳቢ አና በተደጋጋሚ በሕጻናት የሚስተዋሉ የዐይን ህመሞች የዐይን ካንሰር እና የተለያዪ የዐይን እባጮች፣ የዐይን ሞራ ግርዶሽ፣ በመነፅር ሚስተካከል የእይታ ችግር፣ የዐይን መንሸዋረር፣ የዐይን ኢንፌክሽን እና የዐይን አለርጅን ጠቅሰውልናል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በዋነኝነት ሕጻናት ላይ የተለያዩ የዐይን በሽታዎች የሚከሰቱት በዘረመል ችግር፣ ከቤተሰብ በመውረስ፣ በርግዝና ጊዜ በነበረ ያልታከመ ኢንፌክሽን፣ ፀሀይ እና አቧራ በበዛበት ቦታ ላይ አብዝቶ በመዋል፣ ስልክ ወይም ኮምፒዩተር ላይ ብዙ ጊዜ በማሳለፍ፣ ዐይን ላይ በሚከሰቱ ሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ በተለያዩ መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት እና እንደ ስኳር ያሉ የተለያዩ የውስጥ ደዌ በሽታዎች አማካኝነት ሊከሰቱ እንደሚችሉ ነው ባለሙያው የነገሩን፡፡
ሕጻናት የዐይን ህመም ምልክቶች ሲታዩባቸው በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መውሰድ እንደሚገባም ዶ/ር ዳግማዊ መክረዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለከፋ የዕይታ ችግር ወይም ለዐይነ ስውርነት፤ ባስ ካለም አስከ ሞት ሊያደርሳቸው እንደሚችል ነው ያስገነዘቡት፡፡
ጨቅላ ሕጻናትም ልክ አንደሌሎቹ ሕጻናት ወይም አዋቂዎች በተለያዩ የዐይን ችግሮች ሲጠቁ የተለያዩ ምልክቶችን ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕጻናት ላይ ብዙውን ጊዜ ምልክቶቹን በቀላሉ ማየት እንደማይቻል ነው የተናገሩት፡፡ ስለሆነም አንድ ጨቅላ ሕጻን ዐይኑ ጤናማ ቢመስልም ያለ ጊዜ ከተወለደ፣ ክብደቱ ከሚጠበቀው በታች ከሆነ፣ ትኩሳት ካለው፣ ጡት በአግባቡ ማይጠባ ከሆነ፣ ክብደት ባግባቡ ማይጨምር ከሆነ፣ አልጋ ይዞ እየታከመ ከሆነ፣ የሆድ ህመም ካለበት፣ የዐይን ህመም የታመመ ወንድም ወይም እህት ካለው፣ እይታው ከተንሸዋረረ፣ ዐይኑ እንደ ድመት ዐይን ነጭ ሆኖ ሚያንጸባርቅ ከሆነ፣ ዐይኑ ላይ ነጭ ነገር ከጣለበት፣ ዐይኑ በመጠኑ አነስ ወይም ተለቅ ካለ እና ሚንቀጠቀጥ ከሆነ በአፋጣኝ ወደ ዐይን ሕክምና ቦታ መሄድ ይኖርበታል፡፡ ቢቻል ጨቅላ ሕጻናት በተወለዱ በሁለት ሳምንት ውስጥ አንድ ጊዜ ዐይናቸው በሀኪም ቢታይ ችግር እንኳን ቢገኝ በቶሎ ማከም ችንደሚቻል ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
እናቶች በእርግዝና ወቅት የጤና ችግር ካጋጠማቸው በሚወለደው ሕጻን የዐይን ጤና ላይ እክል ሊፈጥር ይችል ይሆን? በማለት ለዶ/ር ዳግማዊ አበበ ላነሳንላቸው ጥያቄም እርግዝና ላይ የነበሩ የጤና ችግሮች በሚወለደው ሕጻን የዐይን ጤና ላይ እክል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ነው የነገሩን፡፡ በተለይ በእርግዝና ጊዜ የነበሩ የተለያዩ የሰውነት እንዲሁም የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖች በአግባቡና በሰዓቱ ካልታከሙ በማህፀን ውስጥ በማደግ ላይ ያሉትን የተለያዩ የሕጻኑን የሰውነት ክፍሎች ይጎዳሉ፡፡
ስለሆነም አንዲት እናት በእርግዝና ጊዜ አስፈላጊውን በባለሙያ የታገዘ የእርግዝና ክትትል እንድታደርግ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡ ይህ በንዲህ እንዳለ ሌሎች ከእርግዝና ጋር ሚያያዙ ችግሮች ማለትም ስኳር፣ ግፊት፣ ደም ማነስ እና ሌሎች የውስጥ ደዌ ችግሮች በሚወለደው ሕጻን የዐይን እድገት ላይ አሉታዊ ትፅእኖ ስለሚያመጡ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ነው አክለው የገለጹት፡፡
ዶ/ር ዳግማዊ የቅርብ ጊዜ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ በሰጡን መረጃ በዓለማችን ከ90 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት በጣም ከባድ የእይታ ችግር አለባቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት እንደ አፍሪካ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያም ምንም እንኳን የተደረጉት ሀገር አቀፍ ጥናቶች የቆዩ ቢሆኑም ከአጠቃላይ ሕዝቧ መካከል የሕጻናት ዐይነ ስውርነት ዜሮ ነጥብ አንድ በመቶ ደርሷል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ሆስፒታሎች የተሠሩ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ቁጥሩ ከዚህ በጣም ሊጨምር እንደሚችል የሚያሳዩ ናቸው፡፡
በሀገራችን ሕጻናትን ለዐዓይነ ስውርነት ከሚዳርጉ የተለያዩ የዐይን ችግሮች ውስጥ በመነፅር ሚስተካከል የእይታ ችግር አንዲሁም በትራኮማ እና በቫይታሚን ኤ እጥረት የሚመጣ የዐይን ብሌን ጠባሳ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች በበቂ ትምህርት እና ጊዜውን በጠበቀ በባለሙያ በሚሰጥ የዐይን ሕክምና በቀላሉ መዳን እንደሚችሉም ነው ዶ/ር ዳግማዊ የጠቆሙት፡፡ ይሁንና ከግንዛቤ ማነስና በቂ የሕጻናት ዐይን ሕክምና ባለሙያ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ችግሮቹ እንደተባባሱ ቀጥለዋል፡፡ ስለሆነም ከግንዛቤ ማስጨበጡ ጎን ለጎን በቂ የሆኑ የሕጻናት የዐይን ሕክምና ማዕከላት እና አብሮም በበቂ ሁኔታ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲኖሩ እና ቀጣይነት ያለው ሥራ መሠራት እንደሚገባ ነው የመከሩት፡፡
ለዶ/ር ዳግማዊ ሕጻናት ዐይናቸው እንዳይታመም ሌላ መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ ምንድን ነው? በማለት ላነሳንላቸው ጥያቄም ሕጻናት ጤናማ ዐይን እንዲኖራቸው እንዲሁም ዐይናቸው በተለያዩ አይነት በሽታዎች እንዳይጠቁ ጥሩ የሆነ የእርግዝና ክትትል ማድረግን፣ የግል እንዲሁም የአካባቢን ንፅህና በደንብ መጠበቅ፣ ሁል ጊዜ እጅን በሳሙና እና በንፁህ ውኃ መታጠብ፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ስልክን አና ስክሪኖችን አብዝቶ አለመጠቀም፣ አቧራ ቦታ ላይ አብዝቶ አለመጫዎት፣ ዐይን ላይ አደጋ ሊያደርሱ ከሚችሉ እቃዎች እና ጨዋታዎች እንዲቆጠቡ ማድረግ ከወላጆች ይጠበቃል፡፡
በተቻለ አቅምም ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት አንድ ጊዜ ዐይናቸውን እንዲታዩ ማድረግ፣ ለየት ያሉ የዐይን ምልክቶች ሲኖሩ በቶሎ ወደ ሆስፒታል መሄድ፣ ጊዜያቸው ሳይደርስ የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናትን በተወለዱ በሁለት ሳምንታቸው በዐይን ሀኪም እንዲታዩ ማድረግ ቢቻል ሕጻናትን ከዐይነ ስውርነት መታድግ እንደሚቻል ነው የገለጹት፡፡
ከላይ የጠቀስናችው የዐይን ህመሞች በሚከሰቱበት ጊዜም በአቅራቢያ በሚገኙ የዓይን ሕክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ ተመርምሮ ተገቢው ህክምናን ማግኘት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡ ባለሙያው እንዳሉት ያለበቂ ህክምና በተለምዶ በራስ ተነሳሽነት ሳይመረመሩ መድሃኒቶችን መጠቀም ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል፡፡
በሀኪም ትዛዝ መሰረት የሚሰጡ የዐይን ጠብታዎች (መድሃኒቶችን ) በአግባቡ መጠቀም በተለይም የዐይን ቀዶ ጥገና ከተደረገ ደግሞ በቂ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡ ሌላው ማድረግ የሌለብን ነገር ብለው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ዐይን በሚታመም ጊዜ የተለያዩ ቅጠሎችንና ሥራ ስሮችን ዐይን ላይ ማድረግ እንዲሁም በጥናት ባልተደገፉ የባህል ሕክምናዎች የሚታዘዙ ባህላዊ መድሃኒቶችን ከመጠቀም መቆጠብ ይገባል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም