የሕፃናት መብቶች

0
170

በሀገራችን ስለሕፃናት መብት መከበር ብዙ ቢባልም በተግባር ግን መብታቸውን አክብሮ እና አስከብሮ ተግባራዊ በማድረግ በኩል በርካታ ጉድለቶች እንደሚስተዋሉ  በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ  ባለሙያ ወ/ሮ ሙሉነሽ ሞገስ ገልፀውልናል::

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ሕፃናት እንደ ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ሰው መብት አላቸው::  በሥነ-አዕምሮአዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ  እንዲሁም አካላዊ ሁኔታ ተጨማሪ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸውም  በዓለም አቀፍና ብሔራዊ ሕግ ማዕቀፎች ተደንግጓል::

ሕፃን ማነው? ለሚለው የሕግ ትርጓሜ መልስ መስጠት አስፈላጊ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የመብት እና ግዴታ ወሰንን  ለማወቅ ስለሚያስችል ነው:: እንዲሁም ሕፃናት ለአደጋ ተጋላጭ ከመሆናቸው አኳያ ልዩ ጥበቃ ስለሚያስፈልጋቸው  ለይቶ ጥበቃ ለማድረግ ያስችላል::

“ሕፃን ማነው?” ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ሀገራት  የተለያየ ትርጓሜ ሰጥተዋል:: ምንም እንኳ አንድ ወጥ የሆነ የሕፃን ትርጓሜ ባይኖርም ሕፃን የሚለው ቃል ብዙ ሀገራት ዕድሜን ግምት ውስጥ ያስገባ ትርጉም ይጠቀማሉ::

በዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን አንቀፅ አንድ የተመለከተው ዕድሜን መሠረት ያደረገ ትርጉም ሲሆን “ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው ነው” በማለት ደንግጓል::

በተመሳሳይ መልኩ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶች እና ደህንነት ቻርተር በአንቀፅ ሁለት ሕፃን ለሚለው ትርጓሜ ሲሰጥ “ሕፃን ማለት ማንኛውም ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ የተፈጥሮ ሰው ነው” በማለት አስፍሯል::

ሕፃናት በአዕምሯቸው፣ በአካላቸው እና በሥነ – ልቦናቸው ያልበሰሉ፣ የማመዛዘን እና ተገቢና ጠቃሚ ውሳኔ የማስተላለፍ አቅም የሌላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሆኑ እንዲሁም ለተለያዩ ችግሮች በቀላሉ ተጋላጭ የመሆን አጋጣሚያቸው የሰፋ እንደሆነ ነው ባለሙያዋ የገለፁት። ይህንን ተጋላጭነታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ሌሎች ሰዎች ከተሰጧቸው ጥበቃ ባሻገር ለሕጻናት ተጨማሪ ጥበቃዎች እና ከለላዎች  መስጠት በማስፈለጉ ሕጎች እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ሀገራት መፈረማቸውን ወ/ሮ ሙሉነሽ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 36 ንኡስ ቁጥር አንድ  “ሁሉም ሕፃናት በሕይወት የመኖር፣ ወላጆቻችውን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅ እና የእርነሱንም እንክብካቤ የማግኘት ፣ ጉልበታቸውን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ ትምህርታቸውን የመከታተል፣ በጤናቸውና በደኅንነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠሩ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ፣ በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ በአካላቸው ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ቅጣት ነጻ የመሆን መብቶች አሏቸው።

 

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች መብት እና ግዴታዎች፦

አንድ ሰው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ የተሰጠው የመጀመሪያው  የሕይወት መብት መሆኑን  ልብ ማለት እንደሚገባው ባለሙያዋ ጠቁመዋል::   ምክንያት ያሉት ደግሞ አንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ በጤንነቱ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ በሕግ ያስቀጣል:: ሥም የማግኘት የሁሉም ሰው መብት ሲሆን  ይህም እንደ ቤተሰብ እና ማህበራዊ ጥበቃ ሕጻናት  የማግኘት መብት አላቸው::

ከሕፃንነት ጀምሮ ሁሉም ሰው በነፃነቱ እና በግሉ ላይ የሚደርስ ጥቃትን ያለመቀበል መብት አለው::   ቅጣቱም ከባድ እና ማሰቃየት ከሆነ “በቃኝ!” ማለት እንደሚችሉም ባለሙያዋ አስገንዝበዋል::

የልዩ ባለሙያ እርዳታ በሚያስፈልግባቸው በርካታ ሁኔታዎች ውስጥ /ሐኪሞች፣ ሳይኮሎጂስቶች/ ልጆች ከአዋቂዎች የተሻለ ድጋፍ እንዲያገኙ ሕጉ ደንግጓል:: የንብረት መብት እና ኃላፊነቶች ልጆች ገና ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ የሚያገኙዋቸው መብቶች ናቸው:: ምክንያቱም በልጅነት እድሜያቸው ውርስ ወይም ትልቅ ስጦታ ሊቀበሉ ይችላሉ ፤ ነገር ግን የማስተዳደር አቅም ስለሌላቸው በልጁ/ጅቱ ስም  ተወካዮች (ሞግዚቶች) በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ በፍርድ ቤት  የሚወሰዱትን የሞግዚትነት ኃላፊነት በመግለጽ ሊያስተዳድሩ ይችላሉ:: ይህ በሚሆንበት ጊዜ ግን ሞግዚቶች የአንዳንድ ልጆችን መብት በመንፈግ ለችግር ሲዳርጉ መመልከት በሀገራችን የተለመደ ድርጊት እንደሆነ ባለሙያዋ ጠቁመዋል::

 

በቤት ውስጥ ያሉ ልጆች መብቶች እና ግዴታዎች፦

ባለሙያዋ እንደሚሉት ሕጉ ለሕጻናት የሰጠው መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው:: ልጆች ወላጆችን ማክበር እና አስተያየታቸውን የማዳመጥ፣ እንደ አቅማቸው ቤት ማጽዳት፣  ምግብ ማብሰል፣ የበሉበትን ማጠብ፣ ቆሻሻውን ወደ ውጭ ማውጣት… የመሳሰሉ  ተግባራትን  ያከናውናሉ:: ወላጆች ደግሞ  ልጆቻቸው ለወደፊቱ ትልቅ ቦታ እንዲደርሱ እና ለዕድገታው ምቹ ሁኔታዎችን በቤት ውስጥ ማመቻቸትን ይጠይቃል:: ከትምህርት ጋር የተገናኘ ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆችን የትምህርት  አስፈላጊነት መገንዘብ ጠቃሚ ነው፤  እያንዳንዱ ተማሪ ተግሣፅን መቀበል እና የትምህርት ተቋሙን ንብረት ማበላሸት የለበትም፣ በትምህርት ቤት ልጆች በሌሎች ተማሪዎች መብቶቻቸውን ላለማጣት ሲሉ የሚጠበቅባቸውን ግዴታም ማክበር አለባቸው::

ባለሙያዋ እንደሚሉት ወላጆች አስፈላጊውን የወላጅነት ግዴታ ካልተወጡ፣ የልጆቻቸውን ደህንነት ካልጠበቅ እና ካላስተማሩ  የወላጅነት መብት እስከመነጠቅ የሚደርስ ቅጣት እንደሚኖረው በቤተሰብ ሕጉ ላይ ተቀምጧል:: በተጨማሪም በሀገሪቱ የሕፃናትን መብት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎችን ተቀብሎ በማጽደቅ የሀገሪቱ የሕግ አካል ቢደረግም ተግባራዊነቱ ግን ክፍተት ይታይበታል።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 36 ንኡስ ቁጥር አንድ (ሠ) ላይ ደግሞ ሕፃናት በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካላቸው ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢ – ሰብዓዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን መብት ያላቸው መሆኑን ደንግጓል። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ለውትድርና መመልመልና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለጦርነት ማሰለፍም ወንጀል ነው::

በአጠቃላይ  የተጠቀሱትን መሠረታዊ የሕጻናት መብቶች በሀገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ሰነዶች የተቀመጡ ቢሆንም በተግባር እየተሠራበት አይደለም። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ለሥራ ያልደረሱ ልጆች ትምህርት ትተው በሰው ቤት መቀጠራቸው እንደ ትክክለኛ ነገር ተቆጥሮ በየቤቱ መመልከት፣ በየመንገዱ ሕፃናት በሥራ ላይ ተሰማርተው መመልከት…ናቸው::  ጉዳዩ ከድህነት ጋር ተያይዞ  ትክክለኛ  ቢመስልም  ለመወሰን በማይችሉበት ዕድሜ ላይ ሆነው ትልልቆች ጉልበታቸውን ያላግባብ እንዲበዘብዙ እያደረገ በመሆኑ የሕጻናትን ሁለንተናዊ መብቶች በዘላቂነት ለማስጠበቅ በጋራ መትጋት ፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ሲታይ  ለሕግ አካላት መጠቆም እና ርምጃ ማስወሰድ እንደሚገባ ባለሙያዋ አስገንዝበዋል::

( ማራኪ ሰውነት)

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here