የባሕር ዳር ከነማው ተጫዋች አለልኝ አዘነ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
በብዙዎቹ ዘንድ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል በሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረው አለልኝ አዘነ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የመሐል ሜዳው ኮከብ ባለፉት ሦስት ዓመታት በባሕር ዳር ከነማ ቤት ማሳለፉ አይዘነጋም። ጥር ሁለት ቀን 1990 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ልማት ሰፈር የተወለደው አለልኝ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው በአርባ ምንጭ ታዳጊ ቡድን ነበር።
በኋላም አቅሙን እና ክህሎቱን አጎልብቶ ለዋናው ቡድን ተሰልፎ መጫወት እንደቻለ የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል። በአዞዎቹ ቤት ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴም በ2011ዓ.ም ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሏል። በሀይቆቹ ቤትም ሁለት ዓመታትን አሳልፏል። አይደክሜው አማካኝ በ2013 ዓ.ም ሀዋሳ ከነማን በመልቀቅ የጣናው ሞገድን መቀላቀል ችሏል። በጣናው ሞገድ ያሳየው ድንቅ አቋምም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲመረጥ ምክንያት ሆኖታል።
አለልኝ አዘነ ለባሕር ዳር ከነማ ሲጫወት በገጠመው የጉልበት ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ለመራቅ የተገደደ ሲሆን ክለቡ በሰጠው እረፍትም ወደ ትውልድ ቦታው አርባ ምንጭ አቅንቶ ከቤተሰቦቹ ጋር ጊዜውን እያሳለፈ ባለበት ወቅት ነው ህልፈተ ህይወቱ የተሰማው።
አለልኝ በቴክኒክ እና በታክቲክ ክህሎቱ የላቀ፣ተክለ ሰውነትን እና የአዕምሮ ዝግጁነትን ያዋሀደ ተጫዋች እንደነበር ይነገራል።በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ በኮሜንታተርነት እያገለገለ የሚገኘው ጊልበርት ሴሌብዋል፣ አለልኝ በጣም የሚገርም ተሰጥኦ ፣ በአውሮፓ ምድር መጫወት የሚያስችል ክህሎት እና አቋምም እንደነበረው ምስክርነቱን ሰጥቷል።
በእርግጥም ተጫዋቹ ሩቅ ያልም እንደነበር የቅርብ የቡድን ጓደኞቹ ተናግረዋል። አዲሱ ሙሽራ ግን ህልሙን ሳይኖር ይህቺን ምድር በ26 ዓመቱ ተሰናበታት። የአሟሟቱን ምክንያት የአርባ ምንጭ ከተማ ፓሊስ እያጣራ መሆኑንም የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብም አለልኝ ይለብሰው የነበረው 23 ቁጥር መለያ ከዚህ በኋላ እንዳይለበስ በክብር ማስቀመጡን አሳውቃል::
የመሐል ሜዳው ኮከብ የቀብር ስነ ሥርዓት መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም በተወለደበት እና ባደገበት አርባ ምንጭ ከተማ ተፈጽሟል። አሚኮ በኩር ስፖርት ዝግጅትም በአለልኝ አዘነ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለወዳጅ ቤተሰቦቹም መጽናናትን ተመኝቷል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም