የመምራት እና የመደገፍ ዕድሜ ክልል

0
52

ባለፈው ሳምንት ጽሑፋችን ልጆች ከአንድ እስከ ዘጠኝ ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ምን ድጋፍ ይሻሉ? የሚለውን በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የስነ ልቦና አማካሪ አቶ እሱባለው ነጋ ሐሳባቸውን አካፍለውልን ነበር፡፡

በዚህ ክፍል ደግሞ በቀጣዩ የዕድሜ ክልል (የታዳጊነት ወይም ከ10 እስከ 18 ዓመት) የልጅ ባህርይ እና አስተዳደግ ምን መሆን እንደሚገባው ሙያዊ ሐሳባቸውን አካተናል፡፡

ይህ የዕድሜ ክልል ሳይንሱም ኃይማኖቱም የሚጋሩት የእሳትነት  (ፋየር ኤጅ)  የሚባለው ነው፤ ይህም ከአካላዊ ቅጣት ያደገ ድጋፍ የሚያስፈልግበት የዕድሜ ክልል ነው፡፡

 

ባለሙያው እንዳስገነዘቡት በመጀመሪያው የዕድሜ (ከአንድ እስከ ዘጠኝ ዓመት) ክልል በብዛት የቤተሰብ ሥራ የሚበዛበት፣ በቤተሰብ ሃሳብ የሚመሩበት ነበር፡፡ በዚህ ዕድሜ ክልል (ከ10 እስከ 18 ዓመት) ግን ልጆች የመረዳት አቅማቸው ስለሚጨምር የሚያዩትን ነገር ለምን? ብለው መጠየቅ የሚጀምሩበት ስለሆነ መደገፍ እና መምራት ይገባል፡፡

ምክንያታዊነት፣ በመነጋገር መግባባት እና የራሳቸው ሃሳብ አለኝ ብለው የሚያምኑበት  የዕድሜ ክልል ነው፡፡ በመሆኑም ቤተሰብ ለዕድሜ ለውጣቸው ዝግጁ መሆን ይገባዋል፡፡

ከ10 ዓመት በኋላ ባለው የዕድሜ ክልል ልጆች ሲያጠፉ እንኳን ቅጣቱ በመግረፍ፣ በመቆንጠጥ፣ …. በልጆቹ ባህርይ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ስለማይኖር እነዚህን ቅጣቶች መፈጸም አይመከርም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ ጥፋቱን የሚያጠፋው አስተሳሰባቸው (ሀሳባቸው) እንደሆነ መገንዘብ ስለሚገባ ነው፡፡

 

በዚህ ዕድሜ ክልል በተለይ ከ10 እስከ 15 ዓመት ሴት ልጆች ቀድመው ስለሚበስሉ የተለዬ ትኩረትን ይሻሉ ሲሉ ነው ያብራሩት፡፡ ይሁን እንጂ ሴት ልጆች ነገሮችን ቀድመው ቢረዱም ስሜታቸው ቶሎ ቶሎ ከፍ ዝቅ የሚልበት ወቅት ስለሆነም ይህንንም መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ወደ 16 ዓመት ገደማ ሴቶች የወር አበባ የሚያዩበት ዕድሜ (ከዚህ ዕድሜ ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ሊጀምር እንደሚችልም ልብ ይሏል) በመሆኑ የሚያመጣውን የስሜት ለውጥ በደንብ ቀርቦ ማስረዳት እና መምከር ያስፈልጋል፤ የስሜት ለውጡም እስከ 17 ዓመት ድረስ ፈጣን ስለሆነ መነጫነጭ ሲያሳዩ ያጣችው ነገር ይኖራል ብሎ በመገንዘብ ቀርቦ መነጋገር ይገባዋል፡፡

 

ተቃራኒ ጾታን (በተቀራራቢ የዕድሜ ክልል የሚገኝ) አይተው በአይን ቢወዱ እና እሱ ባያያቸው ‘ቆንጆ አይደለሁም’ በሚል ወደ ድብርት የሚገቡበት ስሜትም ሊፈጠር ስለሚችል ቤተሰብ በየተራ እየቀረበ ስሜቷ በዕድሜ የመጣ እንደሆነ የማስረዳት ኃላፊነት እንዳለበት ነው ሐሳባቸውን በማሳያ ያጠናከሩት፡፡ ከእሷ የጎደለ ነገር እንደሌለ ማስረዳት የሚገባበት እንጂ “ከወንድ ጋር እንዳላይሽ” ማለት አይገባም በማለትም ይመክራሉ፡፡

እንደ አቶ እሱባለው ማብራሪያ ልጆች በዚህ ዕድሜ ቤት ውስጥ እንደፈለጉ እንዲጠይቁ እና የሚሰማቸውን ሳይሰስቱ እንዲያጋሩ ቤት ውስጥ በግልፅነት የሚወራበትን መድረክ መፍጠር ይገባል፤ ይህን ማድረግ ከተቻለ ደግሞ ልጆቹ ሲያድጉ በየትኛውም ቦታ ሃሳባቸውን ለመግለፅ አይቸገሩም፡፡

ቤተሰብ ደግሞ በነሱ ወሬ ውስጥ መንገዳቸው ወዴት እንደሆነ መገንዘብ ያስችላቸዋል፤ ይህም የሳቱት ነገር ካለ በመነጋገር ወደ ትክክለኛው መንገድ የመመለስ ዕድልን ያመጣል፡፡

 

አቶ እሱባለው እንደሚሉት ልጅን ድርቅ ብሎ ከመከራከር ይልቅ “ሀሳብህ (ዕይታህ) ልክ ነው፤ ነገር ግን በዚህኛው ጎን ብታየው” ብሎ የነሱን ሃሳብ ሳያጣጥሉ መረዳዳት መቻል ልጆችን ወደ ትክክለኛ ሃሳብ እንዲቀርቡ ይረዳል፡፡

ነገሮች ገብተዋቸው በራሳቸው እንዲወስኑ መርዳት እንጂ “እንዲህ ካላደረክ/ካላደረግሽ” እያልን እልህ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግም አያስፈልግም፤ ወላጅ ነገሮችን ተከራክሮ፣ ሃሳብን በሃሳብ አሸንፎ፣ አምነው እና አውቀው እንዲከተሉት ማድረግ እንጂ መጎተት አይገባም፤ ለዚህ ነው ይህ የዕድሜ ክልል ከመንገድ እንዳይወጡ የመደገፍ ደረጃ የሚባለው፡፡

 

ባለሙያው አክለው እንዳሉት የተሳሳተ ነገር ካለ አዕምሯቸው ውስጥ ያለውን ስህተት መጥረግ እና ትክክለኛውን መንገድ ማሳየት ይገባል፡፡ የሃይማኖትን ዋጋ እንዲያውቁ ማድረግም  በማንኛውም መሰናክል እንዳይወድቁ ያደርጋቸዋል፡፡

ቤተሰብን ሲያዩ መደንገጥ እና መፍራት በልጆቹ ባህርይ ውስጥ የሚለውጠው ነገር የለም፤ ስለዚህ ወላጅ ከልጁ በደንብ መቀራረብ እና ጊዜ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ጊዜ መሥጠት ሲባል ልጆቻችን በማይናወጥ ማንነት መገንባት /መስጠት/ መቻል ነው፡፡

የቤተሰብ የመመካከር ጊዜ የቤተሰብን ፍቅር ያመጣል፡፡ ልጆችን አስሮ ቁጭ ማድረግ አፍራሽ ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ አለው፤ ከክፉ ነገሮችም አያርቅም፡፡ ከእኩያ ጋር እንዲጫወቱ በማድረግ የመምራት (ሊደርሺፕ) አቅም የሚዳብርበትም  መንገድ ነው፡፡

 

ስህተት ሠርተውም ቢሆን እንኳ ወደ ከፋው ስህተት እንዳይገቡ ልጆችን አለማራቅ እና ደጋግሞ መምከር እንዲሁም መምራት ይፈልጋል፡፡

ለልጅ የሚደረገው ነገር የሚያስፈልገው፣ የሚጠቅመው  ከአስፈላጊ ነገሮችን ብቻ “ይጠቅማል ወይ?” ብለን ራሳችንን ጠይቀን እንጂ በማልቀሳቸው፣ በማኩረፋቸው፣ በመፈለጋቸው እና ስለቻልን ብቻ የሚሉትን ሁሉ ማድረግ አይገባም፤ የሚፈልጉት ሁሉ ከተደረገላቸው ግን አኩራፊ እና በቀለኛ ባህርይን ያዳብራሉ፡፡ ስለዚህ ወላጅ የሚጠቅማቸውን ብቻ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ልጅን በቤት ውስጥ ነገሮችን በጥሩ መልኩ መመልከት የሚችሉ አድርጎ መገንባት ይቻላል የሚሉት አቶ እሱባለው፤ አንዱን ልጅ ከሌላው ልጅ ወይም ጓደኛ ማበላለጥ እና ማወዳደር ግን ጥሩ ውጤት አይኖረውም ባይ ናቸው፡፡ የውድድር መንፈሱ ይጋባባቸውና ሲያድጉም ባላቸው የማይደሰቱ እንዲሁም ሁልጊዜ በሌላው ሰው መውደቅ የሚደሰቱ ይሆናሉ፡፡

 

በመሆኑም ጎበዝ ልጅ ቢኖርም ሌላኛውን ጎበዝ ለማድረግ እሱ የተለዬ ነገር የለውም፣ ብትሠራ እንደሱ መሆን /መብለጥም ትችላለህ ብሎ በጥሩ መንገድ እንዲከተለው፣ እርዳታም እንዲጠይቀው ማድረግ ይገባል፡፡ በመሆኑም ወላጆች በጣም መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡

ብዙ ልጆች በጥላቻ ስሜት ውስጥ ሆነው የሚያድጉት ወላጅ ጤናማ ያልሆነ የውድድር መንፈስ እየፈጠረ ስለሚያሳድጋቸው መሆኑን ያነሱት አቶ እሱባለው ወላጆች ልጆቻቸውን ካወዳደሩ ራሳቸውን ከትናንት እና ዛሬ ማንነት ብቻ እንዲለኩ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ስለ ሀገራቸው የሚያስቡ እንዲሆኑ በንባብ እንዲተጉ ማገዝ፣ ወላጅ ከአቅሙ በላይ ሲሆን ደግሞ በሃይማኖት አባት ማስመከር፣ መልካም ልጆችን ደግሞ ማመስገን እና ማስመስገን ይገባዋል፡፡

 

ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ የወጣትነት ዕድሜ (ከ18 እስከ 29 ዓመት ያለው) ክልል ነው፤ ይህን የዕድሜ ክልል ቴክኖሎጂው እንዳይነጥቀን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት ጊዜ ነው፡፡ አቶ እሱባለው እንዳሉትም በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር እየተፈተንበት ያለው ነገር ይህ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ድንገት የገቡበት ቴክኖሎጂ ረጅሙን ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡ ከሃይማኖትም ያስወጣቸዋልና ነው፡፡

እንደ ወላጅ በዚህ ዕድሜ (ከዚህ ዕድሜም በፊት ቢሆን) ስልክ ከገዛን ከስልካቸው አለመራቅ፣ ቀይ መስመር አስምረን መጠቀም የሚገባቸውን ነገር ብቻ ማሳየት፣ እንዲከታተሉ ማድረግ እና ስልካቸው ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ መመጠን ይገባል፡፡

በልጆች ዕይታ በቴክኖሎጂ አርአያ የሚደረጓቸው ሰዎችም ስላሉ ከእናት እና ከአባት ውጭ ያሉትን ሰዎች ልክ ናቸው ብሎ መከተል ሊጀምሩ ይችላሉ፤ በመሆኑም የሚያዩትን መጠነኛ ዕውቀት ይዘው እንዳይጠፉ ወላጆች ሳይሰለቹ መከታተል ይገባቸዋል፡፡

አውሮፓ፣ አሜሪካ እና በሌሎች አህጉራት ከሀገራችን ጋር ያለውን የባሕል ልዩነት መንገር እና ሁልጊዜም ትክክል እንዳልሆኑ በደንብ አስምሮ ማስረዳት የወላጆች የዘወትር ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ነው የመከሩት፡፡

 

እንደ አቶ እሱባለው ገለጻ ልጆች የማይነኩ የህይወት መስመሮችን (የባሕል መበረዝ፣ የጥላቻ ስሜት የሚያሳድሩ አላስፈላጊ ውድድሮች፣ አለባበስ)  ሲነኩ ልጆችን ማጣት እንጀምራለን፤  በመሆኑም የልጆቻችንን ድክመት ፈልጎ ማግኘት ይገባል፡፡

በዚህ የዕድሜ ክልል ማገናዘብ የሚጀምሩበት በመሆኑ ከታች የተሠራው (ይዘውት የመጡት መልካም ነገር) እንዳይጠፋ ማድረግ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይላሉ አቶ እሱባለው በዚህ ዕድሜ ለልጆች ኃላፊነቶችን መስጠት ይገባል፤  “ይህን ታደርጋለህ፣ እንደምትፈጽመውም አውቃለሁ” እያሉ ኃላፊነት በመስጠት ማትጋት ይቻላል ነው ያሉት፡፡ ኃላፊነት ሲሰጡ ደግሞ ሰጥቶ መተው ብቻ ሳይሆን ልጆች ኃላፊነቱን እየተወጡ ነው ወይ ብሎ መከታተል፣ ደካማ አፈፃፀም ቢኖራቸውም ጎበዝ በማለት ማበረታታት የተሻለ ለመሥራት ይተጋሉ፤ የብስለት ደረጃቸውም እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ከግላዊ ህይወት ያለፈ ነገር እንዲያስቡ ማገዝ፣ ድህነትን በመጸየፍ ባለፀግነትን አብዝተው የሚሹ እንዲሆኑ ካደረግን በአካባቢያቸው ያለውን ፀጋ እንዴት ነው የምጠቀመው? ብለው ማሰብ ይጀምራሉ፡፡

 

በዕድሜያቸው ምክንያት እየተፈጠረ ያለውን አካላዊ ለውጥ መገንዘብ እንዲችሉ ወላጅ ከስር ከስር ማናገር፣ መምከር፣ “አፈቀርኩ” ቢሉ እንኳ ከወላጅ ጋር በግልጽ እንዲያወሩ ማድረግ ይገባል፡፡ ስለ ፍቅር ምንነት፣ ጊዜው መቼ እንደሆነ፣  ትክክለኛው ስሜት ከፍ ዝቅ  እንደሚል ማስገንዘብ፣ በተለይ ለወንድ ልጆች ስለሴት ልጅ ክብር መንገር፣ ሴቶችም ሴትነታቸው ትልቅ ዋጋ እና ክብር እንደሆነ ማስገንዘብ ከተቻለ ችግር ቢገጥማቸውም በቀላሉ አይፈተኑም፡፡

ገጠር አካባቢ ወንዶች ገበያ ሲሄዱ ሴቶች ወፍጮ ሲፈጩ ነገሮችን እናትም ለሴት ልጇ አባትም ለወንድ ልጁ ይነግራሉ፤ ለወደፊቱ ህይወት እንዲዘጋጁ ያደርጋሉ ፡፡ በከተማ አካባቢ ግን ወላጆች ልጆችን በግልፅነት ማነጋገር እና ለመጭው ህይወት ማዘጋጀቱ ስለሌለ የወጣትነት እሳት ስሜቱ ሲመጣ መሳሳት ይጀምራሉ፡፡

 

ወላጅ ሴት ልጄ  ወጥታ ተደፍራ ስሜን ታስነሳለች ብሎ መጨነቅ ብቻ ሳይሆን ቤት ውስጥ ያሳደግነው ወንድ ልጅ ሄዶ የሌላ ሰው ሴት ልጅ እንዳያበላሽ  እኩል የራሳቸውን ዋጋ ከፍ አድርገው መንገር እና መምራት ይገባል፡፡ በህይወታቸው ሊመጣ የሚችለውን ነገር ቀድሞ ከመከልከል ይልቅ እውነታውን መንገር ከተቻለ በቤት ውስጥ ወንድንም ሴትንም ልጅ በእኩል መጠን ማስረዳት እና ማሳወቅ፣ ማስተማር መቻል ይገባል፡፡

በቤተሰብ ደረጃ ልጆቻችንን እናት ሴት ልጆቻቸውን፣ አባቶች ወንድ ልጆቻቸውን በሥርዓቱ ነገ ስለሚመሩት ሥርዓት ያለው ትዳር ማድረግ ስለሚገባቸው ነገር መንገር፣ ማስረዳትን መልመድም ይገባል፡፡

ባጠቃላይ ግን መንፈሳዊነት ማለትም /ባመኑበት ነገር መኖርን/፣ መሰጠትን በደንብ እንዲያዳብሩ ማድረግ ከቤተሰብ ይጠበቃል፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here