የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይከሰታል?

0
348

የመሬት መንቀጥቀጥ በሰው ልጆች ታሪክ መመዝገብ ከጀመረ አራት ሺህ ዓመታት ተቆጥረዋል። በታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1556 በቻይና የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሁሉም የከፋው እንደሆነ ይነገራል። በዚህ አደጋ ከ830 ሺህ ሰዎች በላይ መሞታቸውም ይነገራል። ከዚህ ክስተት በኋላ በታሪክ በሚገባ የተመዘገበው አደገኛው እና ገዳዩ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው እ.አ.አ. በ2004 ነው። ይህ ሱናሚን የቀላቀለው አደገኛ የመሬት መንቀጥቀት በኢንዶኔዢያ፣ ታይላንድ፣ ሲሪላንካ እና ህንድ የ230 ሺህ ሰዎችን ህይወት በልቷል።

ሬክተር ስኬል (Richter scale) የተሰኘው የመሬት መንቀጥቀጥ መጠን መለኪያ አኃዝ በ1930ዎቹ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የቻይናው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል ከስምንት እስከ ስምንት ነጥብ ሦስት ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል። ይሁንና በሬክተር ስኬል ልኬት መሠረት ከፍተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው እ.አ.አ በ1960 በቺሊ ነው። ይህ ቺሊ ውስጥ ቫልዲቪያ በተባለው አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል ዘጠኝ ነጥብ አምስት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ለአምስት ሺህ 700 ሰዎች ሞትም ምክንያት ሆኗል።

መሬት የተዋቀረችው በሦስት ንጣፎች ነው። የመሬት ማዕከላዊው ክፍል ‘ኮር’ ይባላል። መሃል ላይ የሚገኘው የመሬት ክፍል ‘ማንትል’ ነው። ሦስተኛው ውጫዊው ክፍል ‘ክረስት’ ይባላል። ይህ በዓይናችን የምናየው የመሬት ክፍል ነው።

የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ እንደሚያብራራው የመሬት መንቀጥቀጥ በከርሰ ምድር ውስጥ የተከማቸው ኃይል በድንገት ሲለቀቅ የሚፈጠር ክስተት ነው። የተከማቸው ኃይል ሲለቀቅ የመሬት ንብርብሮች (layers) ይፈጠራሉ።

መሬትን የፈጠሩ ንብርብሮች አራት ናቸው። ሊቶስፌር (lithosphere)፣ በእንግሊዘኛው መጠሪያቸው…ከነዚህ ንብርብሮች መካከል crust እና የmantle የላይኛው ንብር የመሬትን የላይኛውን ንጣፍ ይፈጥራሉ። ይህ ንጣፍ lithosphere ይባላል። ይህ ከሁለት የተለያዩ ንብርብሮች የተፈጠረው lithosphere ሁል ጊዜም በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው። ይህ ማቆሚያ የሌለው እንቅስቃሴ ጫናው እየበረታ ሲሄድ በድንገት የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል።

የመሬት መንቀጥቀጥ የሚነሳበት ማዕከል ኤፒሴንተር (epicenter) የሚባል ሲሆን ትልቁ የመንቀጥቀጥ መጠን የሚከሰተውም በዚሁ ዙሪያ ነው።

ሳይንስ ኒውስ ኤክስፕሎርስ (Science News Explores) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚተነትነው ክረስት እና የማንትል የላይኛው አካል ‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ ከተባለ ድንጋይ የተሠሩ ናቸው። እነዚህ ፕሌቶች ሁሌም በዝግታ እንቅስቃሴ ውስጥ ናቸው። በዚህ ጊዜ ግጭት እና መተፋፈግ ይፈጠራል። ይህ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ ሆኖ በመሬት ገጽ ላይ ያሉ አካላትን የሚያፈራርሰው። በቀላል አገላለጽ በዓይናችን ከምናየው መሬት በታች ያሉት ንብርብር አለቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ እርስ በርስ ሲተፋፈጉ አሊያም ሲፋጩ መሬት ትንቀጠቀጣለች ማለት ነው።

መሬት የተዋቀረችባቸው እነዚህ ‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ በየዓመቱ ጥቂት ሴንቲ ሜትሮችን ይንቀሳቀሳሉ። እንቅስቃሴያቸው ደግሞ በተለያየ አቅጣጫ ነው። ፍጥነታቸውም የተለያየ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ አለቶች እርስ በርስ ተፋፍገው ሊያልፉ ይችላሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ክፍል ከሌላኛው እየራቀ ሊሄድ ይችላል። እርስ በርስም የሚጋጩ አሉ። በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ድንጋዮች ሲተፋፈጉ ርዕደ መሬት ያስከትላሉ። በመተፋፈጉ መካከል የሚከሰተው ኃይል ከፍተኛ ስለሆነ የመሬት ማዕበል ይፈጥራል።

የመሬት መንቀጥቀጥ የባሕር ጠለል ላይ ሲከሰት ደግሞ ከፍተኛ ማዕበል ይፈጠራል። ሱናሚ የሚባለውም ይህ ነው። በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት ነውጦች ይመዘገባሉ። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ የሚባሉ እና በተለዬ ቴክኖሎጂ የሚለዩ ናቸው። በጣም ከፍተኛ የሚባሉት ደግሞ ከተሞችን የማፈራረስ አቅም አላቸው።

ይህ የመሬት ውስጥ ንቅናቄ እና መንቀጥቀጥ ጥንካሬ የሚለካበት መሳሪያ ሬክተር ስኬል ይባላል። ይህ መለኪያ ርዕደ መሬቱ የፈጠረውን የመንቀጥቀጥ መጠን (ማግኒቲዩድ) ይመዝናል።

በዓለማችን ብዙ ጊዜ ተደጋጋሚ ርዕደ መሬቶች የሚከሰቱበት ሥፍራ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ነው። በዚህም ምክንያት በፓሲፊክ ውቅያኖስ አቅራቢያ የሚገኙ እንደ ጃፓን ያሉ ሀገራት ርዕደ መሬትን ተላምደውታል።

ጃፓን ውስጥ ሕንፃዎች ርዕደ መሬትን እንዲቋቋሙ ተደርገው ነው የሚገነቡት። ይህ መሆኑ ደግሞ በሀገሪቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት አብዛኞቹ መዋቅሮች ይናጣሉ እንጂ የመፍረስ እድላቸው ጠባብ እንዲሆን ያደርገዋል።

 

የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይለካል?

የመሬት መንቀጥቀጥ በሚከሰት ጊዜ የሚፈጠር የኃይል ማዕበል አለ። ይህ የኃይል ማዕበል ሴይስሚክ ዌቭ (seismic wave) በመባል ይታወቃል። ሳይንቲስቶች የመሬት መንቀጥቀጥ መጠንን የሚናገሩት ይህንን የኃይል ማዕበል በመለካት ነው። ይህ ማዕበል የሚለካበት መሣሪያ ሴይስሞ ሜትር (seismo meter) የሚባል ሲሆን መለኪያው ደግሞ ሬክተር ስኬል በመባል ይታወቃል።

ይህ የመሬጥ መንቀጥቀጥን ተከትሎ የሚመጣው የሴይስሚክ ማዕበል በምድር ላይ ብቻ የሚከሰት ክስተት አለመሆኑን ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። እንደ ዘርፉ ተመራማሪዎች ገላጻ ይህ የሴስሚክ ማዕበል ጨረቃ፣ ማርስ እና ጁፒተርን በመሳሰሉ ፕላኔቶች ላይም ጭምር ተስተውሏል።

የናሳ ተመራማሪዎች የማርስን የመሬት መንቀጥቀጥ (mars quake) እያጠኑ ነው፣ ይህንን ጥናት በመጠቀም ከርሰ ምድር ውስጥ ምን ዓይነት ንብሮች እንዳሉ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ነው።

 

የመሬት መንቀጥቀጥ በኢትዮጵያስ?

ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ እስከ 40 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟት ነበር:: በርዕደ መሬት ምህንድስና ሙያ ዘርፍ ጥናቶችን በማድረግ የሚታወቁት ዶክተር መሰለ ኃይሌ ከአል አይን ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ሁኔታ የስምጥ ሸለቆ በሚባሉ አካባቢዎች ያሉ ቦታዎች ለመሬት መንቀጥቀጥ የበለጠ ተጋለጭ ናቸው ብለዋል። የስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚባለውም ከቀይ ባሕር ተነስቶ መቀሌ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ አንኮበር፣ ደብረብርሃን፣ አዋሽ፣ አዳማ፣ መተሃራ፣ ፈንታሌ፣ መቂ፣ ዝዋይ፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፣ አዲስ አበባ (አቃቂ ቃሊቲ እና አካባቢው) የሚያካልላቸው ናቸው::

የተመዘገቡ ጥናቶችን መነሻ በማድረግ እንዳስረዱት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ 1898 ዓ.ም ላይ ነበር የተከሰተው:: አደጋው ያጋጠመው ላንጋኖ ላይ ነበር:: አደጋው ስድስት ነጥብ ስምንት ሬክተር ስኬል የተመዘገበ ሲሆን በወቅቱ በአዲስ አበባ የነበሩ ቤተ ክርስቲያናትን አፈራርሶ ነበር::

ሁለተኛው የመሬት መንቀጥቀጥ ያጋጠመው በ1953 ዓ.ም ሲሆን ከአዲስ አበባ እስከ ደሴ ባለው ዋና መስመር ላይ ልዩ ስሙ ካራቆሬ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ አጋጥሞ ነበር:: ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ሦስት ነጥብ 75 ሬክተር ስኬል ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በአካባቢው የነበሩ ቦታዎችን በተለይም ማጀቴ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ እና በሌሎች ውስን አካባቢዎች ላይ የነበሩ መኖሪያ ቤቶችን አፈራርሷል::

ሦስተኛው አደጋ ደግሞ በ1960 ዓ.ም ሰርዶ ተብሎ በሚጠራው የአፋር ማህበረሰብ በሚኖርበት ቦታ ስድስት ነጥብ አራት ሬክተር ስኬል የተመዘገበ አደጋ አጋጥሞ ቤቶችን አውድሞ አልፏል:: በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ እስከ ስድስት ነጥብ ስምንት ሬክተር ስኬል የተመዘገቡ ከ30 እስከ 40 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ያጋጠማት ሲሆን ብዙዎቹ የከፋ አደጋ ያላደረሱት የመሬት መንቀጥቀጥ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ህንጻዎች ስላልተገነቡ ነው::

ታዲያ ይህ ችግር ሲያጋጥም እንዴት ራሱን መከላከል ይችላል? የሚለውን ባለሙያው ያብራራሉ። የመሬት መንቀጥቀጥ እስከ 10 ሰከንድ ነው ሊቆይ የሚችለው፤ ይህም ማለት   አደጋ ሲያጋጥም ቤት ወዲያው አይፈርስም:: ስለዚህ ሰዉ ማድረግ ያለበት ካለበት ቦታ ለመሮጥ አለመሞከር ነው:: ከወንበሮች ስር መሆን፣ ለምሳሌ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከሆንን ጠንከር ያሉ ነገሮችን መጠለል ለምሳሌ አልጋ፣ ጠረጴዛ፣ በር ስር መሸሸግ፣ መንቀጥቀጡ እስከሚያልቅ ባለንበት መቆየት ይገባል::

ትክክለኛው ነገር ለመረጋጋት መሞከር እና ህንጻ ባንድ ጊዜ ስለማይፈርስ በየት በኩል እየፈረሰ እንደሆነ በማየት የተሻለ ደህንነት የሚገኝበትን ቦታ መፈለግ ይገባል::

ብዙ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ በዙር ሊከናወን ይችላል። የመጀመሪያው ዙር ካለቀ በኋላ በመውጣት ወደ ባዶ ቦታ ከህንጻ እና ከሚወድቁ ነገሮች መራቅ፣ እሳት አደጋዎች እንዳይነሱ የምግብ ማብሰያ እና ሌሎች የተያያዙ እሳቶች ካሉ ማጥፋት ያስፈልጋል::

ተጨማሪ የመረጃ ምንጮቻችን አል አይን፣ ቢቢሲ እና ሰዋሰው ድረገፆች ናቸው::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here