የመርታት ጅማሮ

0
142
Blood sampling by an older man

“አልዛሂመር” ማስታወስ አለመቻል ወይም መርሳት የሚያስከትለውን በሽታ ምልክቶቹ ከመታየታቸው አስቀድሞ ከቆዳ ስር የሚገኝ ፈሳሽ ናሙናን በመመርመር ለመከላከል፣ እየተባባሰ እንዳይሄድ ሂደቱን ለማዘግየት እና መድሃኒት ለማግኘት ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መዳረሱን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

በአሜሪካ የሰሜን አሪዞና ዩኒቨርሲቲ በረዳት ኘሮፌሰር ትራቪስ ጊቦንስ የተመራ የተመራማሪዎች ቡድን አንጐል ኃይል በሚያገኝበት የግሉኮስ አጠቃቀም ላይ ትኩረት አድርጐ መስራቱን አስታውቋል፡፡ በዚህም የኃይል ምንጭ የሆነውን በደም ውስጥ የሚገኝ ግሉኮስ ጤናማ አንጐል ፈጥኖ እንደሚጠቀም ወይም እንደሚያቃጥል፤ በተቃራኒው በአልዛሂመር የተጠቃ ሰው አንጐል ኃይል ሰጪ  ግሉኮስን የመጠቀም ፍጥነቱ   አዝጋሚ እንደሚሆን አስፍረዋል- ከግኝታቸው፡፡

የቡድን መሪው በአንጐል ውስጥ የሚገኝ ግሉኮስን ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን አልሸሸጉም፤ እናም የሚመሩት ቡድን በቀላል ናሙና መሰብሰቢያ መሣሪያ ወደ አንጐል ግሉኮስ ከሚያጓጉዙ የደም ስሮች ናሙና በመውሰድ ውጤቱን የማወቅ ሙከራ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

በአዲሱ ምርመራ በየደረጃው በተገቢው መንገድ እየተመራ ለውጦች፣ መሻሻል እና ወደ ዋናው  ግኝት የሚያደርሱ ጠቋሚ ውጤቶች መታየታቸውን አብስረዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡

በቀጣይ በ “ጉልኮስ” ማለትም በአንጎል የኃይል ምንጭ አጠቃቀም ላይ የማገናዘብ (ኮግኒቲቭ) እክል ያለባቸው እና በ “አልዛሂመር” በሽታ የተያዙ ሰዎችን ለማነፃፀር ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአንጐል ሂደት እና ሂደቱን ለመለካት አስቸጋሪ መሆኑን የጠቀሱት ተመራማሪዎቹ በ“ባዮማርከርስ” ስነህይወታዊ ሂደት እና ይዘቱን በመመርመር የሚፈለገው ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ነው ያሰመሩበት – ቡድን መሪው፡፡

በመጨረሻም ወደ አንጐል ከሚያደርሱ የደም ስሮች በሚጓጓዘው ኃይል ሰጪ  “ግሉኮስ” ላይ አተኩሮ የተጀመሩትን ጥረቶች ለፍፃሜ በማብቃት  የአልዛሂመር በሽታን መከላከል የሚያስችል ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል ነው ያሰመሩበት- ተመራማሪዎቹ፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታህሳስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here