የመስቀሉ ታሪክ

0
75

ከክርስቶስ ልደት በፊት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ እና የመግደያ መሣሪያ ነበር:: በግሪካውያን እና በሮማውያን ዘመን ወንጀለኞች በመስቀል ላይ ተሰቅለው ተገድለዋል:: ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ልማድ መሠረት እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ በአይሁዳዊያን ተሰቅሏል:: ይህን የስቅለት ዕለት ለመዘከርም የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ መከበር ከጀመረ ከ1 ሺህ 600 ዓመታት በላይ ሆኖታል::

የአከባበሩ መነሻ ለብዙ ዘመናት ጠፍቶ የቆየው የክርስቶስ መስቀል መገኘት እና ከንግሥት እሌኒ ጋር ይቆራኛል:: ንግሥት ሄሌና (እሌኒ) በኋላም ቅድስት ሄሌና በላቲን ቋንቋ ደግሞ ፍላቪያ ኢዮሊያ ሄሌና አውጉስታ በመባል የምትጠራ ሲሆን የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ናት:: በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም የትውልድ ቦታዋን የተመለከተው አፈታሪክ “እንግሊዝ፣ ሄሌኖፖሊስ ቢታንያ ሆኖ የዘር ግንዷ ከእስያ ይመዘዛል” የሚል ነው:: “ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ነው” የሚሉም አልጠፉም:: የትውልድ ዘመኗንም እንዲሁ በተጠጋጋ ግምት ከ246 – 250 ዓ.ም መካከል እንደሆነ እና ህልፈተ ህይወቷ በ330 ዓ.ም በአሁኗ የቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል እንደሆነ የሚናገሩ አሉ:: ቅድስናዋም በሮማ ካቶሊክ፣ በምስራቅ ኦርቶዶክስ፣ በኦሬንታል ኦርቶዶክስ፣ በአንጀሊካን እና ሉተራን ቤተ ክርስቲያኖች ዕውቅና ተሰጥቶታል::

ንግሥት እሌኒ (ሄሌና)፣ የሮማ ጄኔራል የነበረውን እና በኋላ ንጉሥ የሆነውን ክሎረንስን አግብታ፣ በ274 ዓ.ም ቆስጠንጢኖስ የተባለ ወንድ ልጅ ወልዳለች:: በ292 ዓ.ም ከባሏ ጋር ተለያይታ በ306 ዓ.ም ንጉሥ ክሎረንስ ሲሞት፣ ሰራዊቱ የእሌኒን ልጅ ቆስጠንጢኖስን ቀብቶ አነገሠው:: ይህ አጋጣሚም ንግሥት ሄሌናን ወደቀድሞ ክብር እና ማዕረጓ እንድትመለስ አስቻላት:: ንግሥት እሌኒ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ለመፈለግ ያነሳሳት በልጇ ቆስጠንጢኖስ ላይ ትንቢት በመኖሩ እንደሆነ በትውፊት ይነሳል:: “ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እንደነገሠ ከሦስት አቅጣጫ ከሦስት የተለያዩ ባላንጣዎች ጋር ጦርነቶች ሊያደርግ ተነሳ:: ውጊያውን ከማድረጉ በፊት ግን ስለማሸነፉ ልቡን ጥርጣሬ ገባው:: እንዲህ የልቡ ጥርጣሬ ከፍ ባለበት በሙሉ የቀትር ሰዓት ግን አንድ በብርሃን የተሞላ መስቀል ከሰማይ ወደ ንጉሡ ቀረበ:: በዚህ በከዋክብት ብርሃን በተሞላ መስቀል ላይም “በዚህ ምልክት ተዋጋ” የሚል ጽሑፍ ተመለከተ:: በዚህ ጊዜ ንጉሡ ፈጥኖ በሰማይ ላይ የተመለከተውን መስቀል የሚመስል እና የሚያክል እንዲሠራ ለወታደሮቹ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ከሠራዊቱ ቀድሞ እንዲመራ አደረገ:: በመስቀሉ ኃይልም በቁጥር ከሱ ሠራዊት የሚበልጥ ጦር የነበራቸውን ጠላቶቹን አሸነፈ::” ይላል ታሪኩ::

በሌላ በኩል ንጉሡ በስጋ ደዌ በሽታ ይሰቃይ ስለነበር ወደ አቡነ ሲልቨስተር ቀርቦ ሲያማክራቸው፣ በክርስቲያን ወግ መሠረት አጥምቀውት ተፈወሰ ተብሎም ይነሳል:: ንግሥት እሌኒ ቀደም ሲልም ክርስቲያን ብትሆንም በልጇ ላይ አምላኳ ያደረገውን ተዓምር ስታይ የበለጠ ተሳበች፤ ኢየሩሳሌምንም ለመጎብኘት ወደሥፍራው አመራች:: በዚያም ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አስቆፍራ በማውጣት (በጎልጎታ) ዕውነተኛውን መስቀል በመለየት የክርስትና ምልክት የሆነውን መስቀል ለዓለም ክርስቲያኖች አበረከተች::

በሀገራችንም በመካከለኛው ዘመን በዚህ ስም የምትጠራ ኢትዮጵያዊት ንግሥት እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል:: በታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እና በኢትዮጵያዊቷ ንግሥት እሌኒ መካከል ያለው የዘመን ልዩነት እጅግ የተራራቀ ነው:: ምክንያቱም ኢትዮጵያዊቷ በ16ኛው ክፍለ ዘመን፣ ቅድስት ሄሌና ደግሞ በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በአራተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የኖሩ ናቸውና:: ኢትዮጵያዊቷ እሌኒ የሃድያ ንጉሥ የነበረው የንጉሥ መሐመድ ልጅ ስትሆን በኋላ ክርስትናን ተቀብላ ከዐፄ ልብነ ድንግል ጋር ተጋብታ የኖረች ጠንካራ ሴት ነበረች:: በሕይወት ዘመኗ በመንግሥት አስተዳደር ላይ ተጨባጭ ሚና የነበራት፣ ለብዙ ነገሥታትም አማካሪ ሆና ያገለገለች ታላቅ ፖለቲከኛ ነበረች:: የተወለደችበት ጊዜ በትክክል ባይታወቅም በ1522 ዓ.ም ነበር ያረፈችው::

ስለመስቀል በዓል አከባበር መነሻ በጽሑፍና በቃል የተላለፉ መረጃዎች እንደሚነግሩን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በተዓምራዊነቱ በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅናት ተነሣሥተው ከ300 ዓመታት በላይ በቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ጥለውት ተቀብሮ ነበር።

ይሁንና በ326 ዓ.ም የቄሳር ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ፣ ኪራቆስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ ተረዳች። ከዚያም በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት ባቀጣጠለችው ጊዜ፣ ጢሱ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ በመጠቆሙ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች። ንግሥተ እሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣቸው ይነገራል። ዛሬ በኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ታሪክ ተከትሎ እንደሆነ የሊቃውንቱ ምስክርነት አለ።

ስለመስቀል በዓል በአንዳንድ ሊቃውንት የተለያየ አስተያየት ሲሰነዘር ቆይቷል። ከዚህ ውስጥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መስቀሉን ለማግኘት ሰባት ወራት ያህል እንደፈጀ ቢነገርም በአንዳንድ ሊቃውንት እሳቤ ደግሞ መስቀሉ የተገኘው መስከረም 17 ነው ሲሉ በአጽንዖት ይናገራሉ። ይሁንና አብዛኛው የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት ግን “መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን ነው፣ ይህ ወር ግን የዐቢይ ጾም ወር በመሆኑ በዓሉ በመስከረም 17 እንዲሆን ሊቃውንቱ ተስማምተው አቆይተውልናል” ሲሉ የላይኛውን ሃሳብ ያፈርሳሉ።

ስለመስቀሉ ጉዳይ ስናነሳ አንድ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አለ፤ ይኸውም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ ኢየሱስ የተሰቀለበት የቀኙ ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል የሚባለው ጉዳይ ነው። ስለዚህ መስቀል መምጣት የቤተክርስቲያኗ ጸሐፍት በተለያዩ ሠነዶቻቸው የተረኩ ሲሆን፣ ንጉሡ ዐፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን አስመጥተው በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር፣ ሊያሳርፉበት ያልሞከሩበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸገረ። በመጨረሻ ግን “መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አስቀምጠው” የሚል መለኮታዊ ምሪት ስለደረሳቸው፣ አሁን ግሸን አምባ በተባለ ሥፍራ አስቀምጠውታል:: ይህም ሥፍራ የመስቀል ቅርጽ ያለው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳለው ይነገራል።

ደመራ የሚለው ቃል -ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም ስለሆነም ደመራ እንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ የመስቀል በዓል ነው፡፡ መስቀል የሰላምና የድኅንነት የመቀደስ ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር ነው ይላል አምደ ተዋህዶ በድረ ገጹ።

ተጨማሪ ምንጮች፡- አስተምህሮ እና ብሪታኒካ ድረ ገጾች።

ሳምንቱ በታሪክ

የዐፄ ሠርፀ ድንግል ሕልፈት

በዙፋን ስማቸው “መለክ ሰገድ” ኢትዮጵያን ከ1555-1590 ዓ.ም የመሩ ንጉሥ ነበሩ። አባታቸው ዐፄ ሚናስ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ እቴጌ አድማስ ሞገስ ነበሩ። ከኢብን መሐመድ ( አህመድግራኝ) ወረራ ጀምሮ እስከ ዐፄ ሚናስ ዘመን የቀጠለው አለመረጋጋት በኒህ ንጉሥ ዘመን አንጻራዊ እልባት አግኝቷል። ለዚህ ተጠያቂ የሚሆኑ ጉልህ ክስተቶች በሰሜን የቱርኮች ወረራ በንጉሡ ወታደራዊ ብቃት በመክሸፉ፣ በደቡብ የባሬንቱ ሕዝቦች ሐረርን በመውረራቸው የአዳል ግዛት ኃይል በመዳከሙ እና ስለዚህ ምክንያት ከአዳል ጦርነት በማብቃቱ፣ የሀገሪቱን ዋና ከተማ ከመካከለኛው ክፍል ወደ ዓባይ ምዕራብ በማሻገሩ እና በሌሎች ምክንያቶች ነበር። በአጠቃላይ መልኩ ይህ ንጉሥ ከዐፄ ሚናስ የተረከቡትን ግዛት አስፍተውና አጠናክረው ለቀጣዩ መሪ ትተው አልፈዋል። የንግሡ ባለቤት እቴጌ ማርያም ሰናም ለተከታዮቹ ነገሥታት መነሳትም ሆነ መውደቅ ባበረክተችው አስተዋጽኦ በታሪክ ትታወሳለች።

ዐፄ ሠርፀ ድንግል የንግሥና ዘመናቸውን (ከ1557-1590 ዓ.ም) ሙሉ በቀይ ባሕር በኩል የቱርኮችን (ኦቶማን) ጥቃት በመከላከል ያሳለፉ ናቸው። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ሠርፀ ድንግል በተወለዱ በ47 ዓመታቸው መስከረም 23 ቀን 1590 ዓ.ም አረፉ።

ምንጭ፡- ጆርጅ ዋይን- The Historical Geography of Ethiopia: from the first century AD to 1704”

 

የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት

መስከረም 23 ቀን 1973 ዓ.ም ምስራቃዊ የጀርመን ሀገር የነበረችው የጀርመን ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ከምዕራባዊው የጀርመን ሀገር ጋር ተቀላቅላ ክልሏ የጀርመን ፈዴራላዊ ሪፑብሊክ አካል ሆኖ ሕዝቦቿም የአውሮፓ ሕብረት ዜጎች ሆኑ።

ከውህደቱ አስቀድሞ በምሥራቅ ጀርመን እየበረታ በሄደው ተቃውሞ ጫና ሰበብ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 9፣1989 ጀርመንን ለሁለት የከፈለው የበርሊን ግንብ ፈረሰ፣ድንበሩም ተከፈተ።ግንቡ ከፈረሰ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ሲቀር የዛሬ 30 ዓመት የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት እውን ሆነ። ከውህደቱ በኋላ ብዙ እድገቶች ተመዝግበዋል። ሆኖም አሁንም በምሥራቅ እና ምዕራብ ጀርመን መካከል የኤኮኖሚን ጨምሮ ሌሎችም ልዩነቶች አለመስተካከላቸው ውህደቱ በተከበረና በታሰበ ቁጥር ተደጋግሞ የሚነሳ ጉዳይ ነው ። ከውህደቱ በኋላ ብዙዎች ምሥራቅ ጀርመንን እየለቀቁ ወደ ምዕራቡ ክፍል መሰደዳቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዘለቀ አንዱ ችግር ነው ሲል የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here