የክረምቱ ወቅት ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ አንስቶ የዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ጋራና ሸንተረሩ አረንጓዴ ይለብሳል:: የተለዬ ሕብር የሚፈጥረው አደይ አበባ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት አብሳሪ ነው።
በበርካታ ኢትዮጵያውን ዘንድ አደይ አበባ የአዲስ ዓመት አብሳሪ፣ የመስከረም ወር መለያ ተደርጎ ይወሰዳል። የመስከረም ወር፣ የመስቀል ደመራ እና አዲስ ዓመት ከአደይ አበባ ውበትና መዓዛ ጋር የተቆራኙ ናቸው።
መስከረም ወር የክረምቱ ጨለማ ተገፎ ብርሐን ከመሆኑ፣ ሜዳና ሸንተረሩ በአበባ ከመልበሱ በተጨማሪ ማሕበራዊ መስተጋብር የሚፈፀምበትም ነው:: ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው የመስቀል በዓል አጀማመር መሰረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል መገኘት ጋር የተያያዘ ሲሆን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከንግሥት እሌኒ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እንደሚከበር የቱሪዝም ኢትዮጵያ መረጃ ያስረዳል::
እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በጠፋበት ወቅት ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ለመፈለግ በተነሳችበት ወቅት አንድ ባህታዊ “በራዕይ ተገልፆልኛል፤ መስቀሉን ለማግኘት ደመራ አስደምረሽ /እንጨት አስከምረሽ/ በእሳት ሲቀጣጠል ጭሱ መስቀሉ ወዳለበት ቦታ ይመራሻል፤ ከዚያም በኋላ አስቆፍረሽ ታወጪዋለሽ” አላት:: በተባለው መሠረት ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ፍለጋ መስከረም 17 ቀን ቁፋሮ አስጀምራ ከስድስት እስከ ሰባት ወራት ፈጅቶ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ ተገኘ:: በዚህ መሰረት መስቀሉ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን የደመራ ሥነ ሥርዓት በማካሄድ ይዘከራል::
ይህ ታላቅ በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባሕል፣ አኗኗር እና ወግ የሚከበር ቢሆንም የበዓሉ አከባበር ደረጃ እና የሚሰጠው ትኩረት ከቦታ ቦታ ይለያያል::
በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት /በዩኔስኮ/ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው እና በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በልዩ ድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ማሕበራዊ ፋይዳው የጎላ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ ሽንብጥ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ፈንታው ወንዴ የመስቀል በዓል አዲስ ዓመትን ተከትሎ በመሆኑ የሚመጣው ዘመኑን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በጨዋታ እና በመጠያየቅ እንዲሁም ከጎረቤት ጋር የተለያዩ ማሕበራዊ መስተጋብሮቸን በማከናወን (ቅርጫ፣ አብሮ በመመገብ …) እንደሚያሳልፉና እንደሚደሰቱ ነው የተናገሩት።
አቶ ፉንታሁን የበዓሉ አከባበር ከመስቀል ዓደባባይ ይጀምራል ይላሉ፤ ዋናው ደመራ ከተለኮሰ በኋላም ለሀገር መልካም ጊዜ እንዲመጣ ተመኝተው ወደ ሰፈር ይመለሳሉ:: በሰፈር ደግሞ አማካይ ቦታ ላይ ሌሊት ለሚለኮሰው ደመራ በዓሉን በጋራ የሚያከብሩ ሰፈርተኞች እንጨት በማዋጣት (ከየቤቱ ተሰብስቦ) ይሠራሉ (ደምራሉ)።
አቶ ፈንታው ባለፉት ጊዜያት የነበረውን የበዓሉን አከባር እንደሚከተለው ያስታውሱታል፤ ሙሉ የሰፈሩ ሰዎች ይሰባሰባሉ፤ በዕድሩ የተገዛው ድንኳን፣ ወንበር፣ የመመገቢያ ዕቃዎች ወደ ደመራው ቦታ በማምጣት ይዘጋጃል:: በመዋጮው በሬ ይገዛል፤ ባ ስለቱ ደግሞ በጉን፣ የሚጠጣው፣ የሚበላውን ሁሉ ያቀርባል:: ከዚያም ዕለቱ ከምግቡ እና ከመጠጡ ባሻገር በውብ ባሕላዊ በጨዋታዎች ታጅቦ እየተደሰቱ በጋራ ያከብራሉ። በመጨረሻም ለቀጣይ ዓት መልካም ምኞትን በመመኜት፣ ሁሉም የሚፈልገው እንዲደረግት አምላኩን ለምኖ ስለቱን ተስሎ ይለያያሉ::
የመስቀል በዓል ሲከበር ወቅቱ የትምህርት መጀመሪያ በመሆኑ ደግሞ በዕለቱ የሰፈሩ ጎበዝ ተማሪዎ እንዲበረታቱ ደብተር ይሸለማሉ፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ይበረታታሉ:: የዕምነቱ ተከታይ ያልሆኑ ሰፈርተኞች በዓሉን ባያከብሩም ለልጆች ስጦታ በማበርከት በጋራ ያመሰግናሉ።
መስቀል በጋራ ስለሚከበር ለሰፈሩ አዲስ የሆነ ሰው እንኳን ማሕበራዊ ግንኙነት የሚመሠረተው በዚህ ቀን ስለሆነ በጉጉት ይጠበቅ እንደ ነበር አቶ ፈንታሁን አስታውሰዋል።
አቶ ፈንታሁን እንደታዘቡት በአዲስ ሰፈሮች በሚገኙ ሰዎችም እንደ ቀድሞው በደመቀ እና በተባበረ መንፈስ ያከብራሉ:: ይህ ማሕበራዊ መስተጋብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ምኞታቸውን ገልፀዋል::
በጣና ቀበሌ ነዋሪው አቶ እያሱ ሳህሉ በበኩላቸው በዓላትን (መስቀልን ጨምሮ) በዓደባባይ ወይም በቤት ውስጥ እንደሚያከብሩ ነው የነገሩን፤ የመስቀል በዓል ደግሞ ከአካባቢው ነዋሪ ጋር መስተጋብር ተፈጥሮ የሚከበር መሆኑ ነው ልዩ ያደርገዋል ይላሉ። ሰዎች ተስለው፣ ስለታቸው ሰምሮ የተሳሉትን በማቅረብ እና በማዘጋጀት በጋራ ይደሰታሉ፣ አሁን ደግሞ በሬ ታርዶ ቅርጫ በመግባት አንድ ወይም ሁለት መደብ ቅርጫ ለድግሱ በመስጠት በጋራ ደስታቸውን ይጋራሉ፤ ይህም ለቤተሰብም ሆነ ልጆች ልዩ ትዝታ አለው።
ልጆች የሚተዋወቁበት፣ “ለቀጣይ ዓመት በሰላም ከደረስኩ …” ብለው ተስለው፣ ፍላጎት ካልተሳካም ዓመትን መድረስ በራሱ ትልቅ ነገር መሆኑን ልጆች የሚያውቁበት፣ ከቤታቸው ውጭ ቤተሰባዊ መስተጋብርን የሚፈጥሩበት ውብ ማሕበራዊ ትውስታን የሚፈጥር በዓል ነው፤ በመሆኑም ልጆቻችንም ይህ ውብ ባሕል ገብቷቸው ወደ ፊት የሚያስቀጥሉት እንደሚሆን እምነቴ ነው ብለዋል።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም