አርሶ አደር ይማም አሊ የደቡብ ወሎ ዞን የለጋምቦ ወረዳ ቀበሌ 023 ነዋሪ ናቸው። የእርሻ ሥራቸውን በወቅቱ በማረስ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ያስረዳሉ። የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) እና ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያን በመጠቀም የመስኖ ልማትን እንደሚያከናውኑ በስልክ ነግረውናል። በትንሽ መሬት ላይ የተሻለ ምርት እንደሚያገኙም ገልፀዋል።
አርሶ አደር ይማም በተለይ አትክልት እና ፍራፍሬ አምርተው ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ለሽያጭ ያቀርባሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የመስኖ ልማትን ለማከናወን ማሳቸውን አርሰው፣ አለስልሰው ለዘር አዘጋጅተዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመስኖ ልማት ላይ በልዩ ትኩረት በመሥራቴ የተሻለ ምርት እያገኘሁ ነው ብለዋል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ ባለፈው ዓመት (በ2016 ዓ.ም) ከመስኖ ልማት ከ94 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ነው የነገሩን።
እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ እና ካሮት በብዛት ያመርታሉ። በዚህ ወቅትም ቀይ ሽንኩርት እየተከሉ መሆኑን ነው በስልክ ለበኩር ጋዜጣ የተናገሩት። ወቅቱ ለመስኖ ሥራ ጥሩ እና እርጥበታማ መሆኑን በማንሳት ድንገት የውኃ እጥረት ቢከሰት ከስጋት ነጻ ለመሆን በሴፍቲ ታንከር ውኃ በማጠራቀም ላይ መሆናቸውን ነው የነገሩን።
አርሶ አደሩ እንደነገሩን ማሳን ማረስ፣ ማለስለስ እና መዝራት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የተሻለ ምርት ለማግኘት ማሳን ከተባይ መከላከል እና አረምንም ማረም ይገባል። እርሳቸውም በሰብል የተሸፈነ ማሳቸውን ዘወትር ከተባይ እና ከአረም እንደሚከላከሉ ተናግረዋል። በመስኖ ልማት የተሻለ ተጠቃሚ መሆናቸውን በማስታወስ ሌሎች አርሶ አደሮችም የመስኖ ልማት በማልማት ራሳቸውን ብሎም ሀገራቸውን መጥቀም ቢችሉ መልካም መሆኑን የእርሳቸውን ተሞክሮ ዋቢ አድርገው ምክር ለግሰዋል።
ሌላው ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሚገኙ የነገሩን የደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ 020 ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አራጋው ሀሰን ናቸው። በግብርና ሥራ የሚተዳደሩት አርሶ አደር አራጋው ግብርና የኑሮ መሠረታቸው ነው። ልጆቻቸውን ያሳድጉበታል፤ ያስተምሩበታል። በመኸር ወራት ባቄላ በስፋት እንዳመረቱም ነው የተናገሩት። የግብርና ባለሙያ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅትም ለመስኖ የሚሆን የእርሻ ማሳቸውን እያረሱ እና የውኃ ማፋሰሻ ቦይ እያዘጋጁ መሆኑን በስልክ ነግረውናል።
ሁለት ሔክታር መሬታቸውን በመስኖ በማልማት ከራሳቸው አልፎ ምርቱን ለገበያ እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል። በቀጣይ ስንዴ እና ገብስ በብዛት እንደሚያመርቱ አክለዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀማቸው የሚያገኙት ምርት መጨመሩን ተናግረዋል።
ወደፊት መንግሥት ከዚህ በተሻለ የተሻሻለ ምርጥ ዘር፣ በቂ የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ቢያቀርብላቸው ከዚህ የበለጠ ምርት አምርተን ለገበያ ማቅረብ እንችላለን ብለዋል።
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን የ2017 ዓ.ም የበጋ መስኖ ልማት የንቅናቄ መድረክ መካሄዱን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ለበኲር ጋዜጣ ተናግረዋል።
በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት 31 ሺህ ሔክታር መሬት (27 ሺህ ሔክታር በነባር እና ከ4 ሺህ ሔክታር በላይ ደግሞ በአዲስ) በመስኖ ለማልማት መታቀዱን ነው መምሪያ ኃላፊው በስልክ በሰጡን መረጃ ያስታወቁት። የተሻለ ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በበልግ እና በበጋው የሚለሙ የፍራፍሬ፣ የአትክልት እና ጥራጥሬ ሰብሎችን ጨምሮ ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል። እንደ አቶ አህመድ ማብራሪያ በቆላማ አካባቢዎች የተሻለ ምርት እየሰጡ ያሉትን ቋሚ የፍራፍሬ ተክሎች (አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ቡና እና ሙዝ)፣ በደጋማ አካባቢዎች ደግሞ የአፕል ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመትም በዞኑ 36 ሺህ 500 ሔክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል:: ከዚህም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በዞኑ በትኩረት እየተሠራበት የሚገኘው ሌላው ዘርፍ የአትክልት ልማት (ጎምን፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ) መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።
በመኸር ተዘርተው ምርቱ የተሰበሰበባቸው ቆላማ አካባቢዎች ቀድመው ወደ እርሻ (የበጋ መስኖ ልማት) እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ቀበሌ ድረስ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት መካሔዱንም ተናግረዋል። ለበጋ መስኖ ልማት ሥራ ከ52 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውልም አስረድተዋል። ምርጥ ዘር (በዋናነት የስንዴ እና የአትክልት ዘር) በግብርና ማዕከላት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ዓመቱ በዝናብ ስርጭቱ ጥሩ በመሆኑ ከወንዞቹ የሚጠለፍ በቂ ውኃ እንዳለ ተናግረዋል። ለዚህም ሁለት ሺህ 500 የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን አስታውቀዋል። በቅርብም ለግብርና ልማት ሥራው የሚያገለግሉ 300 የግብርና ሥራ ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። 85 በፀሐይ ብርሐን የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት በሂደት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ምርታማነትን ለማሳደግ የማጠራቀሚያ ኩሬ፣ የፕላስቲክ ሸራ ንጣፍ፣ የውኃ መሳቢያ ሞተር እና ሌሎች ለበጋ ሥራ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆልቲካልቸር ዳይሬክተሩ አቶ ይበልጣል ወንድምነው ለበኲር ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በ2017 በጀት ዓመት 342 ሺህ 480 ሔክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ47 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው። ከዚህ ውስጥ 250 ሺህ ሔክታር መሬት በስንዴ እንደሚሸፈን ተናግረዋል። ለዚህም በቅድመ ዝግጅት ወቅት በመስኖ የሚለማውን መሬት የመለየት፣ ለተሳታፊ አርሶ አደሮች ግንዛቤ የመፍጠር፣ የግብዓት አቅርቦት የማሳለጥ እና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። እስካሁን በተሠራው ቅድመ ዝግጅት ሥራም ከ127 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከ15 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ ታርሶ በመስኖ ተሸፍኗል። 212 ኪሎ ሜትር የካናል ጠረጋ እና ጥገና ሥራ ተከናውኗል። 38 ሺህ ሔክታር የአትክልት ዘር መደብም ተዘጋጅቷል።
በአማራ ክልል በመስኖ የሚለማ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ቢኖርም እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው ግን ከ20 በመቶ እንደማይበልጥ አክለዋል። ለዚህም የመስኖ መሠረተ ልማቶች አለመስፋፋት፣ የበጀት እጥረት እና ሌሎች ችግሮችን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የዘንድሮውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነት ለማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ገልጸዋል። የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ የተሻለ የምርት ጭማሪ ለማግኘት ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።
ለበጋ መስኖ ሥራው ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የአፈር ማዳበሪያው ከተከማቸበት ቦታ ወደ አርሶ አደሩ የማዘዋወር ሥራም እየተሠራ ነው። የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች ከሰኔ ወር ጀምሮ ለአርሶ አደሩ እንደተሠራጩ እና በቀጣይም ተጨማሪ ለማሰራጨት ታቅዷል ብለዋል።
ይህም ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ከመላቀቅ ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ለማምረት የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል። ባለፈው ዓመት (2016 ዓ.ም) 300 ሺህ ሔክታር የሚጠጋ ማሳ በመስኖ ተሸፍኖ 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደተገኘ አስታውሰዋል። አርሶ አደሩ የእርጥበት ጊዜው ሳያልፍ እና የውኃ መጠኑ ሳይቀንስ ፈጥኖ መዝራት እንዳለበት አሳስበዋል። የግብይት፣ የነዳጅ አቅርቦት፣ የሰብል ጥበቃ እና የተባይ ቁጥጥር ሥራዎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በመሆናቸው በትኩረት መሥራት እንደሚገባ በማንሳት በአጠቃላይ የግብርና ሥራ የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም