መሶብ የአንድ ማዕከል ከብልሹ አሠራር የጸዳ ቀልጣፋ አገልግሎትን በዲጂታል ሥርዓት ለመስጠት የሚያስችል ስለመሆኑ ተስፋ ተጥሎበታል። የባሕር ዳር ከተማ ማዕከልም ከሰሞኑ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጤናው ምሕረቱ ለበኩር ጋዜጣ እንደገለጹት ከዚህ በፊት በከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ነበሩ። ታዲያ መሶብ ይህንን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
በከተማዋ የተቀላጠፈ አሠራርን ለመተግበር የተመረቀው የባሕር ዳር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሁን ላይ በስምንት ተቋማት 48 አገልግሎቶችን ይሰጣል። በቀጣይም ሌሎች ተቋማትም አገልግሎቶቻቸውን ይዘው ወደ ማዕከሉ እንደሚገቡ ነው አቶ ጤናው የገለጹልን።
በተለይም ሙስናን ለመግታት እና አንድ ጉዳይን ለማስፈጸም የሚፈጀውን ጊዜ ይታደጋል። ወደ ማዕከሉ የገቡት ተቋማት በርካታ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው በተለይም ለሙስና ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ አገልግሎቶች ወደ ማዕከሉ ገብተዋል።
በየዕለቱ በርካታ ሕዝብ አገልግሎት ለማግኘት የሚያቀናባቸው እንደ ወሳኝ ኩነት፣ ከተማ እና መሠረተ ልማት፣ የውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ገቢዎች፣ ንግድ እና ገበያ ልማት፣ ፍትሕ፣ ሥራ እና ክህሎት እንዲሁም ትራንስፖርት ጽ/ቤት በማዕከሉ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ክፍሎች ናቸው። የቀበሌ መታወቂያ መስጠትም በማዕኩሉ የሚከናወን ተግባር ነው።
ማዕከሉ ሰፊ የባለጉዳይ መቆያ፣ የመሠብሰቢያ እና የሥልጠና አዳራሾች፣ የሕጻናት ማቆያ፣ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ መስጫ፣ ካፍቴርያ እና የመኪና ማቆያ የተሟሉለት ነው፤ ይህም አገልግሎት ፈላጊዎች ጉዳያቸውን ምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲያስፈጽሙ ያደርጋል።
አቶ ጤናው እንዳሉት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ነባሩን የከተማው አስተዳደር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የተካ አይደለም። ሆኖም ብልሹ አሠራርን በመፍታት ፈጣን አገልግሎት ሕብረተሰቡ እንዲያገኝ ታልሞ የተቋቋመ ነው። በመሆኑም ማሕበረሰቡ ወደ ማዕከሉ ሲመጣ ሙሉ በሙሉ ከወረቀት የጸዳ ሥራ ስለሚሠራ መረጃዎቻቸውን ስካን አድርገው እንዲይዙ አሳስበዋል።
በምረቃ ፕሮግራሙ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የባሕርዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማውን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተው ነበር።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “ጊዜውን ሰውቶ፣ ከቅርብም ከሩቅም አገልግሎት ፈልጎ የሚመጣን ሰው በተገቢው መልኩ ማስተናገድ እንደ ሀገር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው” ብለዋል።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም