የመቅደላዉ ሰበቦች

0
219

በግዛቷ ፀሀይ አትጠልቅም…የተባለላት የታላቋ  እንግሊዝ መንግሥት ስም በኢትዮጵያ ምክንያት ጠፍቷል፣ ወደ  እየሩሳሌም እና መካ የሚሔዱ ኢትዮጵያውያን በየደረሱበት ሁሉ የሀበሻ ንጉሥ የእንግሊዝን ንግሥት አሽከሮች በሰንሰለት አስሮ ካስቀመጣቸው እነሆ አራት ዓመታት አለፉ፣ እያሉ ማውራታቸው በመላው ዓለም ተዳረሰ። የእንግሊዝ መንግሥት ወሬው እንዳይስፋፋ ቢደብቅም ይባስ እየተስፋፋ እና እየገነነ ሄደ። ያኔ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩት ሕንዶች ይህን ወሬ ሰምተው የእንግሊዝ መንግሥት ‘ደካማ ነው’ እያሉ የእንግሊዝን መንግሥት ከሀገራችው ለማስወጣት ይዶልቱ እና ያስቡ ጀመር። እንግሊዞች በየደረሱበት ሁሉ ይሰደቡ እና ይናቁ ነበር። በያሉበት እና በየደረሱበት ሁሉ በማፈር አንገታቸውን ይደፉ ነበር። ኢትዮጵያ በማትታወቅበት ሀገራት ሁሉ ዝነኛ ሆነች…። ሲል ጳውሎስ ኞኞ፣ በዓፄ ቴዎድሮስ መፅሃፉ ላይ ፅፎታል።

እንግሊዝ በብሔራዊ ክብሯ ላይ የወረደው እንዲህ ያለው የውርደት ናዳ በአፍሪካውያን ላይ ላሳየችው ንቀት የከፈለችው ዋጋ ነበር። የታላቅ ሀገራቸውን የቀደመ ክብር እና ሃያልነት ለመመለስ፣ ለማሰልጠን ፅኑ ምኞት ለነበራቸው ለአርቆ አሳቢው አፍሪካዊው ንጉሥ ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ያሳዩት ቸልታ ንጉሡን ከማበሳጨቱ አልፎ በዘመኑ ታላቅ የተባለለትን የእሮጌን ጦርነት አሰከተለ።

ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ መንግሥት የጀመሩትን የሀገር ግንባታ የሚያግዙ ባለሙያዎችን እንዲልኩላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ በእንግሊዙ ቆንስል ካሜሩን በኩል ይልካሉ። ምላሽ ሳይመጣ ብዙ ወራት አለፉ። ደብዳቤው ለንደን የደረሰው ዘግይቶ ነበርና። የቅርብ ወዳጃቸው የነበረውን ካሜሮንን ንጉሡ በወዳጅነት ስሜት ተቀበሉት። ካሜሩን ከእንግሊዝ ያመጣውን ስጦታ አቀረበ፤ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ግን ዋናውን የደብባቤያቸውን ምላሽ ሲጠይቁት አለማምጣቱን ነገራቸው። ንጉሡም እጅግ ተበሳጩ እና ከጠላቶቼ ከቱርኮች ጋር አብረህ ክደህኛል በሚል ካሜሩንን ከአጠገባቸው ከነበሩት ሌሎች የውጭ ዜጎች ጋር አሰሩት። ታዲያ ይህ የንጉሡ እርምጃ ነበር በመቅደላ አምባ ላይ በታላቋ ብሪታኒያ እና በኢትዮጵያ መካከል ለተደረገው የእሮጌ ጦርነት እንደ ዋና ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ፅፈዋል።

ዳግማዊ ቴዎድሮስ ይህን የእንግሊዝን መንግሥት ዝምታ ለመንግሥታቸው እውቅና የመንፈግ የንቀት ያህል ስለቆጠሩት ባለሙያዎቹ እስካልተላኩልኝ ድረስ እስረኞቹ እንደማይለቀቁ ቆረጡ። ይህ የካፒቴን ካሜሩን እና ሌሎች አውሮፓውያን በኢትዮጵያ የመታሰራቸው ዜና ከእንግሊዝ ባለስልጣናት ጆሮ እንደደረሰ ትዉልደ ኢራቃዊውን የምስራቅ አፍሪቃ ሀገራትን በደንብ ያውቃል ያሉትን ሀርሙዝድ ራሳም የተባለ መልእክተኛ የጨርቃ ጨርቅ ስጦታ አስይዘው እስረኞችን እንዲያስፈታ ወደ ኢትዮጵያ ላኩት። ራሳምን ከዐፄ ቴዎድሮስ በክብር ከተቀበሉት በኋላ የመጣበትን ምክንያት ጠየቁት፣ እርሱም የእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያ እስረኞችን እንዲፈቱ መጠየቃቸውን ገልፆ የተላከላቸውን ስጦታ አበረከተ። ንጉሡም እስረኞቹን ፈትተው አስረከቡት እና ያሰሩበትንም ምክንያት ገልፀው መጀመሪያ ስለፃፉት ደብዳቤ መልስ ባለመሰጠቱ የተላከላቸውን ስጦታ መልሰው ሰጡት። ቀጥሎም ሲያስቡት ከጠላታቸው ከቱርክ ጋር ተማክሮ ጦርነት እንደሚያካሂዱባቸው አውቀው እንደገና ተመልሰው እንዲታሰሩ አደረጉ። ራሳም እንደገና ከንጉሡ ፊት ቀርቦ እስረኞቹን አልፈታም ካሉ የእንግሊዝ መንግስት በጦር ሀይል እንደሚያስፈታቸው በማስረዳ በድጋሚ እንዲፈቱ ጠየቀ። ቴዎድሮስ ግን ተናደው ራሳምን አሰሩት።

ሁኔታው መካረር ቢጀምርም የእንግሊዝ መንግሥት ግን በሌሎች አንገንጋቢ ጉዳዮች በመወጠሩ ትኩረት አለመስጠቱን አለን ሙር “ብሉ ናይል” በተሰኘ መፅሀፉ ላይ አብራርቶታል። በመሆኑም አለን ሙር እንደፃፈው እንግሊዝ በወቅቱ የወግ አጥባቂው ፓርቲ አሸንፎ አዲስ መንግሥት ምስረታ ላይ የነበረች እና በሀገሪቱ የሪፎርም ሰነድ ላይ በተነሱ አመፆች እና ሁከቶች የእያንዳንዱ አእምሮ ተወጥሮ ነበር። በዚያም ላይ በወቅቱ በፕራሽያ እና በኦስትሪያ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ለንደንን በገንዘብ ቀውስ መትቷታል። በተጨማሪም አደገኛ የከብት በሽታ ወረርሽኝ በመላ ኢንግላንድ እየተስፋፋ ነበር። ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያው ጉዳይ ብዙም ክብደት አልተሰጠውም።

ጀርመናዊው ፍላድ ጉዳዩን ለእንግሊዝ መንግሥት አስረድቶ መፍትሔ ለመምከር እንግሊዝ ተጓዘ። ፍላድ ታዲያ ለንደን የደረሰው ሐምሌ ወር 1858 ዓ.ም ነበር። ፍላድ ጉዞ በጀመረበት ወቅት እስረኞቹ በደህና ሁኔታ የተያዙ መሆናቸውን ሪፖርት አደረገ፤ ነገር ግን  እንግሊዝ በደረሰ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሀርሙዝድ ራሳም በደብረታቦር የመታሰሩ ዜና መጣ እና ዐፄ ቴዎድሮስ  ራሳምን በኃይል ወይም በድርድር እንዲለቁ እስካልተደረገ ድረስ እስረኞችን በመያዢያነት አስረዋቸው እንደሚቀጥሉ ግልፅ ሆነ። ለጊዜው  ሀገሪቱ ከገጠማት ቀውስ የተነሳ ኃይል መጠቀም አይታሰብም፣ ስለሆነም አማራጩ ዲፕሎማሲ መሆኑ ታመነበት።

ስለሆነም ቴዎድሮስ የጠየቁት የተመረጡ ሙያተኞች ተዘጋጁ። እናም ፍላድ ባለሙያዎቹን የማባበያ ስጦታዎችን እና የንግሥት ቪክቶሪያን  የቃል መልዕክት ይዞ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ታዘዘ። ይሁን እንጂ ባለሙያዎቹን በቀይባህር ወደብ እንዲቆዩ በማድረግ እስረኞቹ ሲፈቱ ባለሙያዎቹን እንደሚልክ እየተደራደረ ቆየ። ዓፄ ቴዎድሮስ ፍንክች አላሉም። እስረኞቹን  ቢፈቱ እንደሚሻል ካልሆነ የእንግሊዝ መንግሥት በሀይል ለማስፈታት እንደሚገደድ ሲሞግታቸው ቆየ። ዓፄ ቴዎድሮስ ታዲያ “የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ እኛ አንፈራም ጠላቶቼን ድል ማድረግ የለመድኩት ነው” ብለው በቁጣ ከመለሱለት በኋላ ፍላድንም አስረው አስቀሩት። በዚህ መካከል ነው እንግዲህ የታላቋ እንግሊዝ በእስረኞቹ ዙሪያ በመላው ዓለም የተናፈሰው ወሬ ክብሯ እንዲጎድፍ፣ እንዲናቅ የሆኑበት ሀቅ የለንደኑን ምክር ቤት ያወከው። የእስረኞቹ ሁኔታ ሳይሆን የተነካው ክብራቸው ስላንገበገባቸው፣  በኢትዮጵያ ላይ ጦር ማዝመት የሀገር ክብር ጉዳይ ተደርጎ ስለተወሰደ በመጨረሻ እስረኞቹን በኃይል ለማስፈታት በምክር ቤቱ ተወሰነ። እናም የጦርነት ትዕዛዝ ተሰጠ።

ለዚህ ልዩ ኦፕሬሽን የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት አካል በሆነው በሕንድ ያለው ሰራዊት ተመረጠ። ዘመቻውን እንዲመራ ደግሞ በብዙ አለማቀፍ ውጊያዎች የተሻለ ልምድ እና ብቃት ያለው ጄኔራል ናፒየር ተሰየመ። ናፒየርም ወደ ኢትዮጵያ የዘመቻ ግዳጅ የተሰጠውን የቦምባይ ሰራዊትን በመምራት ተንቀሳቀሰ።

የሃምሳ ሰባት ዓመት ጎልማሳው ናፒየር በመጨረሻ 32ሺ ሰዎች የተፈቀደለት ሲሆን ከዚህ ውስጥ  ወታደሮቹ 13ሺ ብቻ ነበሩ፣ ከወታደሮቹም ውስጥ 4ሺህ የሚሆኑት አውሮፓውያን እና 9ሺዎቹ የሕንድ ተወላጆች የተካተቱበት ነበር። 55ሺህ እንስሳት አብረው ዘምተዋል። መድፎችን ለማጓጓዝ አርባ አራት የሰለጠኑ ዝሆኖች ተዘጋጁ። በአይነቱ የተለየ አይነት ግዙፍ ወታደራዊ ዘመቻ ሆኖም ተመዝግቧል።

መሪ ራስ አማን በላይ እንደፃፉት በዚህን ጊዜ የእንግሊዝ ጦር በጄኔራል ናፒየር እየተመራ በ1860 ዓ.ም ምፅዋ አጠገብ በምትገኘው ዙላ ወደብ ላይ ደረሰ። በቱርክ ወታደሮች እና በሃገሬው እየተረዱ በሰንአፌ ሰፈሩ። ከሰናፌም እንዳሉ የትግሬ እና የላስታ መሳፍንት በተስፋ ሲጠባበቁት ለነበረው የእንግሊዝ ጦር ሰንጋ እና ለጭነት የሚሆን አጋሰስ ፈረስ አስረክበው ከጄኔራሉ ጋር ተዋወቁ። ስምምነት ከፈፀሙ በኋላም በሚያውቁት ሰዎች እየተመሩ ዋድላ ደረሱ። የእንግሊዝ ጦር መንገዱ ሁሉ ክፍት መሆኑን አውቆ፤ ከዋድላ ደላንታ ወገልጤና ላይ ሰፍሮ ጄኔራሉ “እስረኞችን ፈትተው ይላኩልን” ሲል ለቴዎድሮስ ደብዳቤ ፃፈላቸው።

“እንግሊዞች መጡ ባህር ተሻገሩ

ዐፄ ቴዎድሮስ ይበልጡናል ብለው

መድፍና መትረየስ ማሰራቱን አውቀው”

ተብሎም የተገጠመው ያኔ ነበር።

የጦርነቱ አይቀሬነት እርግጥ በሆነበት በዚህ ወቅት፤ ዐፄ ቴዎድሮስ ሰራዊታቸውን ሰብስበው ታላቅ ንግግር አድርገው ሲያበቁ ወደ ተዘጋጀላቸው የጦር ግንባር ሄዱ። የእንግሊዝ ጦር ሰራዊት በኢትዮጵያ መሳፍንት እየተመራ ከወገልጤና ተነስቶ የበሽሎን ወንዝ ተሻግሮ ወደ እሮጌ ሲደርስ ፉላ ሥላሴ  መሽጎ የነበረው የዐፄ ቴዎድሮስ የጦር ሰራዊት በፊታውራሪ ገብርዬ መኮንን እየታዘዘ ሄዶ ጦርነት ገጠማቸው። ትንሽ እንደቆየና እንደተዋጋ ድል ሆነና ድሉ ለፊታውራሪ ገብርዬ ሆነ። ከእሮጌ ተነስቶ ወደ በሽሎ ወንዝ ወደሚያወርደው መንገድ እየፎከረ እና እየሸለለ ሲሄድ ወደ ኋላ አፈግፍጎና ጥሩ ስፍራ ይዞ ሲጠብቃቸው የነበረው የእንግሊዝ የጦር ሰራዊት በመትረየስ ደግኖ ከኋላ ከፊት ሆኖ በፊታውራሪ ገብርየ የሚመራውን ሰራዊት ጨረሳቸው። ከዚያም በጉዞ ላይ የነበሩ ወታደሮች  ተመልሰው ዐፄ ቴዎድሮስ ወዳሉበት ምሽግ ሄደው የሆነውን ሁሉ ነገሯቸው። በዚህን ጊዜ በጣም አዘኑ።

ከዚያም ናፒየር እስረኞችን ለቀው ራሳቸው  ዐፄ ቴዎድሮስ እጃቸውን እንዲሰጡ የሀያ አራት ስዓት ጥያቄ አቀረበላቸው።  የቴዎድሮስ ጦር እየተመናመነ ቢሄድም ከንጉሣችን ጋር አንለይም ብለው በጀግንነት ብዙዎች ተሰው። መቅደላ በመድፍ ነደደች።     ንጉሡም ወታደሮቻቸው ማለቃቸውን ካወቁ በኋላ እስረኞችንም ሁሉ ለቅቀው በተወለዱ በሃምሳ ዓመታቸው በንጉሡ በ13ኛው ዓመት ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም በገዛ ሽጉጣቸው  ለሃገራቸው ክብር ሲሉ ራሳቸውን ሰውተው አላማቸውን ተንተርሰው ተገኙ።

“ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው

ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው

ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ ሀገራቸው

ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው” ተብሎ ተገጠመላቸው።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here