“የብዙኀን ሳይኮሎጂ” ግለሰቦች በትላልቅ ቡድኖች ወይም ህዝቦች ውስጥ እንዴት እንደሚሆኑ፣ አስተሳሰቦቻቸውና ድርጊቶቻቸው በጋራ ተጽዕኖ እንዴት እንደሚቀኀጹ የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ ነው።
ስኪፒዮ ሲግሄሌ እና ጉስታቭ ሌቦን የብዙኀን ሳይኮሎጂን በመቅረጽ ኀገድ ወሳኝ ነበሩ ሲል ሳይኮሎጂ ታውን ገጽ ይጠቅሳል። ትልልቅ ቡድኖች ብቻቸውን ከሚሰሩ ግለሰቦች ፈጽሞ የተለየ ባህሪና ስሜት እንዴት እንደሚያሳዩ ግንዛቤዎችን አቅርበዋል።
ከአንድ ሁለት ይሻላል እንደሚለው የሀገራችን ብሂል፤ እነዚህ ባህሪዎች ብዙውን ጊዜ በቡድኖች ውስጥ የሚጠነክሩ የስነ-ልቦና ሂደቶች ውጤቶች ናቸው። የብዙኀን ሳይኮሎጂ ጽንሰ-ሐሳብ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ፣ አውሮፓ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን በምታደርግበት ወቅት የተነሳ መሆኑ ይነገራል። የኢንዱስትሪ ልማት፣ የከተሞች መስፋፋት እና የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች መምጣት ትላልቅ ቡድኖች እንዲፈጠሩና እንዲገናኙ አዳዲስ መንገዶችን ፈጥሯል።
በዚህ ወቅት፣ ምሁራንና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የቡድን ባህሪ ከግለሰብ ባህሪ በእጅጉ የሚለይ መሆኑን ማስተዋል ጀመሩ። ጉስታቭ ሌቦን ከብዙኀን ሳይኮሎጂ ጋር በተያያዘ ምናልባትም በጣም ታዋቂው ሰው ነው። “ዘ ክራውድ: ኤ ስተዲ ኦፍ ዘ ፖፑላር ማይንድ” በሚል እ.አ.አ በ1895 ታዋቂ ሥራው ውስጥ፤ ሌቦን የህዝቦችን የስነ-ልቦና ባህሪያት አጥንቷል። በህዝብ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች የስነ-ልቦና ለውጥ እንደሚያደርጉ፣ የግለሰባዊ ማንነታቸውን እና ኃላፊነታቸውን እንደሚያጡ ተከራክሯል። እንደ ሌቦን ገለጻ፣ ሰዎች በህዝብ ውስጥ ሲሰባሰቡ፣ የግለሰብ አስተሳሰባቸው በቡድኑ የጋራ አስተሳሰብ ሰላባ እንደሚሆን ጽፏል።
ሌቦን ህዝቦችን “በስሜት የሚመሩ” እንጂ በምክንያት የሚመሩ አይደሉም በማለት ገልጿል። በህዝብ ውስጥ የግለሰቦች አስተሳሰብና ድርጊት በቡድኑ በሚያሸንፉ እንደ ፍርሃት፣ ቁጣ ወይም ደስታ በመሳሰሉት ስሜቶች ይታፈናሉ። ይወሰዳሉ። ይህም ግለሰብ ማንነቱን የሚያጣበትን ውጤት ያስከትላል።
ከዚህ በመነሳት የግል ኃላፊነት እየቀነሰ ይሄዳል። ግለሰቦች ለድርጊታቸው ያላቸው ተጠያቂነት አነስተኛ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚህ ምክንያት፣ ህዝቦች የብዙኀንን ስሜት በሚነኩ አብዮተኞች እና መሪዎች በቀላሉ ሊመሩ እንደሚችሉ ተከራክሯል። በመንጋው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከምክንያት ይልቅ ስሜት ስለሚጫናቸው፤ በስሜት የሚመራቸውን ሰው የመከተል ዝንባሌ ያሳድራሉ።
የሌቦን ንድፈ ሐሳብ በህዝብ ውስጥ ስለሚኖሩ ግለሰቦች ባህሪ በርካታ ወሳኝ ሀሳቦችን አስተዋውቋል። አራት የብዙኀን ሳይኮሎጂ ዋና መርሆዎችን አስቀምጧል።
የመጀመሪያው የግለሰብ ማንነት ማጣት ነው። ከብዙኀን ሳይኮሎጂ ቁልፍ ገጽታዎች አንዱ የግለሰብ ማንነት ማጣት ነው። በሕዝብ ውስጥ፣ ሰዎች የራሳቸውን ባህሪያት የመተው ዝንባሌ አላቸው። እናም ድርጊታቸው በቡድኑ የጋራ ስሜታዊ ሁኔታ ይወሰናል። ይህ ደግሞ ብቻቸውን ከሚሆኑበት ጊዜ በበለጠ ከቡድኑ ጋር ሲሆኑ ስሜታዊ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ባህሪያትን እንዲያሳዩ ያደርጋቸዋል።
ሁለተኛው የስሜት ተላላፊነት ነው። በሕዝብ ውስጥ ስሜቶች ተላላፊ ናቸው። አንድ ሰው ከተቆጣ፣ ከፈራ ወይም ከተደሰተ እነዚህ ስሜቶች በቡድኑ ውስጥ በፍጥነት ሊሰራጩና መላውን ህዝብ ሊነኩ ይችላሉ። ይህ የስሜት ተላላፊነት ብዙውን ጊዜ ምክንያታዊ አስተሳሰብን በስሜት የበላይነት እንዲያዝ ያደርጋል።
ሦስተኛው የቡድን አስተሳሰብ እና ተገዥነት ይባላል። የቡድን አስተሳሰብ የሚከሰተው በቡድን ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ሁኔታውን በእውነታ ላይ ተመስርቶ ከመገምገም ይልቅ ከቡድኑ ጋር የመስማማት ወይም የመዋሃድ ፍላጎት ላይ ተመስርተው ውሳኔ ሲወስኑ ነው። ከቡድኑ ጋር ለመስማማት የሚደረገው ግፊት ወደ ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ እና ምክንያታዊ ያልሆኑ ውጤቶች ሊያመራ ይችላል።
አራተኛው የግለሰብ ኃላፊነት ማጣት ነው። በትላልቅ ቡድኖች ውስጥ ግለሰቦች የግል ተጠያቂነት ስሜታቸው እንደሚቀንስ ይሰማቸዋል። ይህ ደግሞ ሰዎች ብቻቸውን ሲሆኑ ፈጽሞ ሊያደርጉት በማይችሏቸው ድርጊቶች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል። ለምሳሌ ሁከት፣ ዘረፋ ወይም ሌሎች አጥፊ ባህሪዎችን ሊያሳዩ ይችላሉ።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የታየው የብዙኀን ባህሪ በዘመናዊ ሁኔታዎች፣ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን፣ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እና በትላልቅ ተቃውሞዎች ውስጥ መገለጡን ቀጥሏል።
ማህበራዊ ሚዲያ እና የህዝብ አስተሳሰብ
ዛሬ ማህበራዊ ሚዲያ የቡድን ባህሪን በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንደ ትዊተር፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ ያሉ መድረኮች ግለሰቦች በትላልቅ ምናባዊ ቡድኖች ውስጥ እንዲሰባሰቡ ያስችላሉ። በዚህም የብዙኀን ሳይኮሎጂ ስሜታዊ ተለዋዋጭነት ሙሉ በሙሉ ይታያል። ልክ እንደ አካላዊ ህዝብ የኢንተርኔት ላይ ቡድኖች ብዙውን ጊዜ የስሜት ማስተጋባትን ያሳያሉ። የጋራ ስሜቶች እና አመለካከቶች በአውታረ መረቡ ላይ በፍጥነት ይሰራጫሉ። አንድ ነጠላ የቫይራል ልጥፍ የብዙኀን ቁጣን፣ ደስታን ወይም ፍርሃትን ሊያነሳሳ ይችላል። የሰዎችን አስተሳሰብ እና ባህሪ ይነካል። ሰዎች በቡድን ሁኔታ ውስጥ የመረጃን ምንጮች የማጥራት ዝንባሌ የላቸውም። ብዙውን ጊዜ የቡድኑ እና መሪዎች ሐሳብ ሰለባ ይሆናሉ።
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪዎች እና የፖለቲካ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የብዙኀን ሳይኮሎጂ ስልቶችን ተጠቅመው ህዝቦችን በማነሳሳት፣ ምክንያትን ሳይሆን ስሜትን በመጠቀም አስተያየቶችን እና ባህሪዎችን ይቀርጻሉ። የብዙኀን ሳይኮሎጂ በትላልቅ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እና ተቃውሞዎች ውስጥም ወሳኝ ሚና አለው። የህዝበኝነት መሪዎች መነሳትም ይሁን የማህበራዊ ፍትህ እንቅስቃሴዎች፣ የብዙኀን ስሜቶች እና የጋራ አስተሳሰቦች የፖለቲካ ግቦችን ለማሳካት ብዙውን ጊዜ ጥቅም ላይ ይውላሉ። መሪዎች እንደ ፍርሃት፣ ቁጣ ወይም ተስፋ ያሉ የህዝቡን ስሜቶች በመጠቀም ድጋፍ ለመሰብሰብ እና የጋራ ማንነት ስሜት ለመፍጠር ተጠቅመውባቸዋል።
በዓለም ዙሪያ በህንድ፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በአውሮፓ ክፍሎች የታየው የህዝበኝነት እንቅስቃሴዎች ማዕበል የብዙኀን ሳይኮሎጂ የህዝብ አስተያየትን ለመፍጠር እና ማህበራዊ ለውጥን ለማምጣት እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል ያሳየ ሆኗል።
በብዙኀን እንቅስቃሴዎች ውስጥ የግለሰብ ማንነት ማጣት እና የግል ሃላፊነት መቀነስ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖዎች ሊኖራቸው ይችላል። በአንድ በኩል ሰዎችን በጋራ ዓላማ ዙሪያ በማሰባሰብ አንድነትንና የጋራ ዓላማ ስሜትን ያዳብራል። በሌላ በኩል፣ ግለሰቦች ሳያስቡ እና የድርጊቶቻቸውን የረጅም ጊዜ ውጤት ሳያስቡ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ወደ አደገኛ የቡድን አስተሳሰብ ሊያመራ ይችላል።
ሳይኮሎጂ ታውን ገጽ “የብዙኀን ሳይኮሎጂ አዎንታዊ ለውጥ የማምጣት አቅም ቢኖረውም፣ አሉታዊ ጎንም ሊኖረው ይችላል” በማለት ጽፏል። የግለሰብ ኃላፊነት ማጣት እና በህዝብ ውስጥ ያለው ስሜታዊ የበላይነት ወደ አደገኛ ባህሪዎች ሊመራ ይችላል። በናዚ ጀርመን በመሳሰሉ ታሪካዊ ክስተቶች ላይ እንደታየው ታዋቂው የብዙኀን አስተሳሰብ በኃይል፣ በዘረፋ እና በዘር ማጥፋት ድርጊቶች ሊጠናቀቅ ይችላል።
የብዙኀን ሳይኮሎጂን ተጠቅመው ህዝቦችን ለራሳቸው ጥቅም የሚቆጣጠሩ እና የሚያዛቡ ማራኪ መሪዎች ተጽዕኖ የዚህ ክስተት ሌላኛው ጨለማ ጎን ነው። በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻዎች ወቅት እጩው ብዙኀኑን ለመማረክ ስሜታዊ ንግግር ሲያደርግ ማስተዋል የተለመደ ነው። በእጩው የሚተማመኑ ሰዎች ይሰባሰባሉ እናም ድጋፋቸውን ያሳያሉ።
ፍላጎቶችን የሚጋራ ማህበረሰብ ወይም ቡድን በመጀመሪያ አዎንታዊ ይመስላል። ሆኖም፣ ግለሰቦች በብዙኀን ውስጥ የግል ሰብዕናቸውን ያጣሉ። በምትኩ በብዙኀን ሐሳብ እና መንፈስ ይዋጣሉ። ይህ የሚሆነው የብዙኀኑ አካል እንደሆኑ ወዲያውኑ ጠንካራ ስሜት ስለሚሰማቸው ነው።
ግለሰቦች ወደ ቡድን ሲዋሐዱ የግለሰቡ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የበለጠ በጥንታዊ እና ስሜታዊ በሆነ የብዙኀን መንፈስ ይተካል። አንድ ግለሰብ በምክንያት፣ በክርክር እና በማስረጃ ሊሳብ ቢችልም፣ ብዙኀኑ ግን ለምስሎች፣ ስሜቶች እና ታሪኮች ጠንካራ ምላሽ ይሰጣል። ብዙኀኑ በስሜት ስለሚመራ አስተሳሰቡ የሕፃን ልጅ አስተሳሰብ ሊመስል ይችላል። መደማመጥ፣ መከራከር፣ መረጋጋት፣ የማይታሰቡ ይሆናሉ።
ይህንን እውነት በፖለቲካዊ ሰልፍ፣ የእግር ኳስ ጨዋታ ወይም ታዋቂ ባንድ ኮንሰርት ላይ መመልከት ይቻላል። ብዙኀኑ ብዙ ጊዜ ቀስቃሽ ንግግር ሲደረግ፣ ጎል ሲገባ ወይም ተወዳጅ ዘፈን ሲዘፈን ጠንካራ ስሜቶችን ያሳያሉ።
በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ብዙ ጊዜ ስሜታዊ ፍረጃዎችን እና ሐሳቦችን እንመለከታለን። የፖለቲካ እና ሰላማዊ ሰልፎችም ላይ ስሜት አይሎ ምክንያትን ያፍናታል። ብቻችንን ብንሆን የማናደርገውን ወይም ሊያሳፍረን የሚችልን ተግባር በጋራ ስንሆን እንፈጽማለን። ብዙ የደቦ ፍርዶች፣ ጥላቻዎች፣ አሉታዊ ቅስቀሳዎች፣ ንግግሮች በስሜት የሚነዱ ብዙኀን የሚፈጽሟቸውን ጉዳቶች አድርሰዋል።
ሃርበር የአዕምሮ ጤና ክሊኒክ ድረገጽ የብዙኀንን አስተሳሰብ በእሴቶች፣ በአስተያየቶች እና በእምነቶች ላይ ያለውን ተጽዕኖ አብራርቷል። በዚህም አባላቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የሞራል ችግሮችን ችላ እንዲሉ እና ድርጊቶች የሚያስከትሉትን ውጤቶች እንዳያስቡ ያደርጋቸዋል ብሏል። ከጥላቻ ስሜት በመነሳት እንዲቃወሙ አልፎ ተርፎም እንዲያወግዙ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ የቡድኑ አባላት ጠቃሚ ሃሳቦችን ወይም መረጃዎችን ችላ እንዲሉ ያደርጋል። ጠቃሚ ማስጠንቀቂያዎችን ችላ ብለው ችግር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። አባላቱ ራሳቸውን የሚገመግሙት ሌሎች አባላት ምን ይሉኛል በሚል ነው። የማይቀበሏቸው ሲመስላቸው ጥሩም ሐሳብ ቢሆን ዝም ይላሉ። እና ቡድኑ የተሻለውን እንደሚያውቅ ይገምታሉ። የማይደፈር የመምሰል ቅዠቶችም አሉ። የቡድኑ አባላት ከልክ ያለፈ ተስፋ እንዲያደርጉ እና አደጋን እንዲጋፈጡ ያደርጋቸዋል። የተለየ አስተያየት ያላቸውን ሰዎች አያዳምጡም።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም