የመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር

0
1035

የመንግሥት የንብረት ግዢ እና አስተዳደር አዋጅ ምን እንደሚል በዚህ ሳምንት የፍትሕ አምድ ሰነዱን የምንዳስሰው ይሆናል:: የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ ሥራ ላይ በቆየባቸው ዓመታት ያጋጠሙ የአፈጸጸም ችግሮችን በማስወገድ የመንግሥት በጀት አዘገጃጀት፣ የመንግሥት ገንዘብ አሰባሰብ፣ የክፍያ ፣ የሂሳብ አያያዝ እና የውስጥ ቁጥጥር እንዲሁም የሀብት እና የዕዳ አስተዳደር ብቃት ያለው፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድግ እየተሠራበት ይገኛል::
ይህ አዋጅ ተፈጻሚ የሚሆነው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ይሆናል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁ የሚመለከታቸውን መሥሪያ ቤቶች ዝርዝር በየጊዜው ያወጣል። “የፌዴራል መንግሥት የግዢና የንብረት አስተዳደር አዋጅ 649/2001” ወጥቶ በሥራ ላይ ይገኛል::
አዋጁ የመንግሥት ግዢና የንብረት አስተዳደር በሕግ መሠረት መከናወኑን የሚቆጣጠር “ኤጀንሲ” እና በግዢ ሒደት የሚያጋጥሙ ቅሬታዎችን የሚሰማ “ቦርድ” አቋቁሟል:: ከአዋጁ ሌላ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በሰኔ 2002 ዓ.ም (በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም ተሻሽሎ) ያወጣው “የፌዴራል መንግሥት የግዢ አፈጻጸም መመሪያ” አለ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም የመንግሥት ንብረት የሚገዛና የሚያስወግድ “አገልግሎት” የተሰኘ አካል በደንብ ቁጥር 184/2002 አቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል::
የመንግሥት ግዢ አዋጅ ቁጥር 649/2001 መሠረት ስድስት (6) ዓይነት የግዢ ዘዴዎች ተዘርዝረዋል:: እነዚህም ግልጽ ጨረታ፣ በመወዳደሪያ ሐሳብ መጠየቂያ የሚፈጸም ግዢ፣ በሁለት ደረጃ ጨረታ የሚፈጸም ግዢ፣ ውስን ጨረታ፣ በዋጋ ማቅረቢያ የሚፈጸም ግዢ እና ከአንድ አቅራቢ የሚፈጸም ግዢ ናቸው:: እነዚህን በአጭሩ እንደሚከተለው እናስነብባችኋለን::

ግልጽ ጨረታ
ግልጽ ጨረታ (Open Bidding ወይም Open Tendering) የሚባለው ጨረታው በማስታወቂያ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን በሰፊው ተሰራጭቶ ብዙ ተወዳዳሪዎች የሚጠሩበትና የሚሳተፉበት ነው:: ስለ ጨረታው ዝርዝር መግለጫ የያዘው ሰነድ የሚገኝበት ቦታ፣ ተጫራቾች ምላሽ የሚያቀርቡበት የጊዜ ገደብና ሥፍራ ሁሉ ተጠቅሶ በማስታወቂያው ይወጣል::
በግልጽ ጨረታ የሚካሄደው ግዢ የውጭ ሀገር አቅራቢዎች ለሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ (ኢንተርናሽናል) ግዢም ሆነ የሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ለሚሳተፉበት ብሔራዊ ግዢ ያገለግላል::
የዕቃው ወይም የአገልግሎቱ ዋጋ ከተወሰነ እርከን ማለትም ለግንባታ ሥራ 150 ሚሊዮን ብር፣ ለዕቃ ግዢ 50 ሚሊዮን ብር፣ ለምክር አገልግሎት ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር፣ ለአገልግሎቶች 21 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ግዢው በዓለም አቀፍ ውድድር ሥርዓት እንዲካሄድ ሚኒስትሩ ያወጣው መመርያ ያስገድዳል:: ማስታወቂያው ሰፊ ሥርጭት ባለው “ሚዲያ” እንዲለቀቅ፣ ለመጫረቻው ሰነድ ዝግጅት በቂ ጊዜ እንዲሰጥ፣ መግባቢያ ቋንቋው እንግሊዝኛ እንዲሆን ወዘተ ያስፈልጋል ማለት ነው::
በሌላ በኩል የሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ዋጋ ከላይ ከተጠቀሰው እርከን በታች በሆነ ጊዜ፣ ወይም ዋጋው ከዚያ በላይ ቢሆንም ምርቱ ወይም አገልግሎቱ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገኝ በሚሆንበት ጊዜ ግዢው ሀገር ውስጥ ባሉ ተወዳዳሪዎች መካከል ይፈጸማል ማለት ነው::

የመወዳደሪያ ሐሳብ በመጠየቅ የሚፈጸም ግዢ
ይህ የግዢ ዓይነት የምክር አገልግሎት ለመግዛት ሲፈለግ የሚያገለግል ነው:: መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቱ ግምታዊ የገንዘብ መጠኑ ከዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር በላይ የሆነ የምክር አገልግሎት ሲፈልግ በቅድሚያ ፍላጎት ያላቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በመጋበዝ ጥሪ ያደርጋል:: በጥሪው መሠረት ከቀረቡት ውስጥ ከሦስት ያላነሱ ከሰባት ያልበለጡ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ይመርጥና እነርሱ ብቻ የመወዳደሪያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ይጋብዛል:: ቀጥሎም በጥራት እና በዋጋ አወዳድሮ አሸናፊውን ይለያል:: የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በሰኔ 2002 ዓ.ም ወጥቶ በታኅሣሥ 2008 ተሻሽሎ ባወጣው መመርያ መሠረት የአገልግሎቱ ግምታዊ ዋጋ ከዘጠኝ መቶ ሺሕ ብር በታች በሆነ ጊዜ መሥሪያ ቤቱ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ከአቅራቢዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲመርጥ ሥልጣን ሰጥቶታል::

በሁለት ደረጃ ጨረታ የሚፈጸም ግዢ
የመሥሪያ ቤቱን ፍላጎት በተሟላ ሁኔታ ለመግለጽ ባልተቻለበት ጊዜ ወይም ለሚገዙት ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ዝርዝር (ስፔሲፊኬሽን) ማዘጋጀት ባልተቻለበት ጊዜ መሥሪያ ቤቱ ጨረታውን በሁለት ምዕራፍ በመከፋፈል ግዢውን ማከናወን ይችላል:: ይህ አካሄድ በሁለት ደረጃ ጨረታ የሚፈጸም ግዢ ይባላል::
በዚህ የግዢ አካሄድ መሥሪያ ቤቱ በመጀመሪያው ዙር ተወዳዳሪዎች ዋጋን ያላካተተ የመወዳደሪያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ የጨረታ ጥሪ ያደርጋል:: መሥሪያ ቤቱ የሚፈልገውን ዕቃ ወይም አገልግሎት አጠቃላይ በሆነ መልክ ገልጾ ሌላውን ዝርዝር ተወዳዳሪዎቹ ራሳቸው አሟልተው እንዲያቀርቡ ይጋብዛል:: ከዚያም ተወዳዳሪዎቹ ያቀረቡለትን የመወዳደሪያ ሐሳቦች ከግዢ ፍላጎቱ ጋር ገምግሞ ሌላ የተሟላ ዝርዝር በማዘጋጀት ለሁለተኛ ጊዜ ተጫራቾች የመጫረቻ ሐሳባቸውን (ዋጋን ጨምሮ) እንዲያቀርቡ ጥሪ በማድረግ የሚከናወን ነው::

ውስን ጨረታ
በመንግሥት ግዢ አዋጅ አንቀጽ 49 መሠረት ከሚከተሉት ሦስት ሁኔታዎች አንዱ ሲያጋጥም ግዢው በውስን ጨረታ ሊካሄድ እንደሚችል ይደነግጋል:: ይህም ማለት ጨረታው ሁሉም አቅራቢ ነኝ የሚል የሚጠራበትና የሚሳተፍበት ሳይሆን ውድድሩ በተወሰኑ (በተመረጡ ወይም ቁጥራቸው ጥቂት በሆነ) አቅራቢዎች መካከል ብቻ የሚከናወን ነው::
የመጀመሪያው ሁኔታ ዕቃው ወይም አገልግሎቱ ከተወሰኑ አቅራቢዎች ዘንድ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ነው:: ሁለተኛው ሁኔታ ደግሞ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በመመሪያ ካስቀመጠው የገንዘብ መጠን ያልበለጠ ሲሆን ነው:: በመመሪያ የተቀመጠው የገንዘብ መጠን ለግንባታ ሥራ ስድስት ሚሊዮን ብር፣ ለዕቃ ግዢ አንድ ነጥ አምስት ሚሊዮን ብር፣ ለምክር አገልግሎት ዘጠኝ ሚሊዮን ብር፣ ለሌላ አገልግሎት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚል ነው:: ሦስተኛው ሁኔታ፣ ጨረታ በተደጋጋሚ ወጥቶ “ተወዳዳሪ ያልተገኘ” ሲሆን ነው::
የግዢው ዋጋ ከላይ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን ያልበለጠ ሆኖ አቅራቢዎቹ ብዛት ያላቸው በሆነ ጊዜ “በአቅራቢዎች መዝገብ” ከተመዘገቡት ውስጥ ከአምስት ያላነሱ ተመርጠው እንዲወዳደሩ በማድረግ ይፈጸማል::

በዋጋ ማቅረቢያ የሚፈጸም ግዢ
በዋጋ ማቅረቢያ (ጥሪ) የሚፈጸሙ ግዢዎች በጣም የተወሰኑ ናቸው:: በመጀመሪያ ደረጃ የገንዘብ ሚኒስቴሩ በመመሪያ ካወጣው ጣሪያ ያልዘለሉ መሆን አለባቸው:: ይህም ለግንባታ ሥራ ግማሽ ሚሊዮን ብር፣ ለዕቃ ግዢ ሁለት መቶ ሺሕ ብር፣ ለምክር አገልግሎት አንድ መቶ ሃያ ሺሕ ብር፣ ለሌላ አገልግሎት ግዢ አንድ መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር ነው:: በሁለተኛ ደረጃ የሚገዙት ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ለገበያ የተዘጋጁ ወይም የታወቀ ገበያ ያላቸው መሆን አለባቸው::
በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑ ቢያንስ ሦስት አቅራቢዎች ከአቅራቢዎች ዝርዝር (Suppliers’ List) ውስጥ እንዲመረጡ ተደርጎ ለሚፈለገው ዕቃ ወይም አገልግሎት ዋጋ እንዲጠሩ ይደረጋል:: በዚህም መሠረት የገዢውን መሥሪያ ቤት ፍላጎት ያሟላው እና አነስተኛ ዋጋ ያቀረበው ተወዳዳሪ አሸናፊ ይሆናል::

ከአንድ አቅራቢ የሚፈጸም ግዢ
ይህ የግዢ ዓይነት በአዋጁ አንቀጽ 51 እና አንቀጽ 52 ተደንግጓል:: ዕቃው ወይም አገልግሎቱ ከአንድ አቅራቢ ብቻ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህ ብቸኛ አቅራቢ ግዢው ይከናወናል:: ከመጀመሪያው አቅራቢ ተጨማሪ መለዋወጫዎች በሚያስፈልጉበት ጊዜ ወይም ሥራው የግንባታ ዘርፍ ሆኖ በመጀመሪያው ውል ያልተካተቱ ድንገተኛ ተጨማሪ ሥራዎችን ማሠራት ሲያስፈልግ ወይም ግዢ የተከናወነበት ዓይነት ሥራ በድጋሚ እንዲሠራ ወይም እንዲቀርብ ሲያስፈልግ ወይም በጣም አስቸኳይ ሆኖ (በቶሎ ካልተሠራ ችግር የሚፈጥር ከሆነ) በበላይ ኃላፊ የተፈቀደ ሲሆን ከአንድ አቅራቢ ግዢውን ማከናወን ይቻላል::

የመረጃ ምንጫችን የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጥራዝ (ማንዋል) ነው::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here