የመካለኛው ምሥራቅ አዲሱ ውጥረት

0
174

የሶሪያዉ ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ከተወገዱ በኋላ  እስራኤል ከሶሪያ ጋር የሚያዋስናትን የጎላን ተራራን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥራለች፤ እስራኤል ይህን ያደረገችው የደህንነት ስጋትን ለመከላከል መሆኑን ብታሳውቅም  ውግዘት እየደረሰባት ነው።

እስራኤል እ.ኤ.አ ከ1967 ጀምሮ  አብዛኛውን ጎላንን ተቆጣጥራ እ.ኤ.አ በ1981 አካባቢውን ከግዛቷ ጋር ቀላቅላለች። በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2019 የመጀመሪያዉ የስልጣን ዘመን በአሜሪካ ብቻ ጎላን የእስራኤል ነው በሚል ዕውቅና ማግኘቷም የሚታወስ ነው።

እ.ኤ.አ በ1967 በአረብ – እስራኤል ጦርነት ወይም የስድስቱ ቀን ጦርነት ወቅት እስራኤል ሁለት ሦስተኛውን የጎላንን ቦታ አሸንፋ ተቆጣጥራለች። ከአንድ ወር በኋላም ሰፈራው በዓለም አቀፍ መርህ ሕገ ወጥ ነው ቢባልም የመጀመሪያውን የሲቪል ሰፈራ ሜሮም ጎላን የሚል ስያሜ በመስጠት ዜጎቿን አስፍራለች።

ከሰሞኑ የሶሪያ ወታደሮች ከጎላን ተራራማ አካባቢዎች መውጣታቸውን ተከትሎ እስራኤል ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነውን አካባቢ በቁጥጥር ሥር አውላለች። በሶሪያ በኩል የወጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት እስራኤል በደማስቆ (የሶሪያ ዋና ከተማ) በኩል እስከ 25 ኪሎ ሜትር ዘልቃ ገብታለች። እስራኤል ግን ያን ያህል ርቀት ወታደራዊ ኃይሏ አለመጓዙን ነው ያሳወቀችው።

እ.ኤ.አ በ1973  በአረብ እና በእስራኤል ጦርነት ወቅት ተጨማሪ ጦርነት የተቀሰቀሰ ሲሆን  በ1974 ሶሪያ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተዋል። ሁለቱም ሀገራት ወደየግዛታቸው 80 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲገቡም ስምምነቱ ያስገድዳል።

የጎላን ተራራ ከሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አለታማ ስፍራ ነው፤ ሶሪያን በደቡብ ምዕራብ፣ እስራኤልን ደግሞ በሰሜን ምሥራቅ ያዋስናል። ዛሬ በጎላን ተራሮች ወደ 30 ሺህ የሚገመቱ የአይሁድ ነዋሪዎች ከ30 በላይ በሚሆኑ ሰፈሮች ይገኛሉ።

አካባቢው በእስራኤል ከመያዙ በፊት በሊባኖስ፣ በዮርዳኖስ እና በእስራኤል እንዲሁም በሶሪያ እና እስራኤል በተቆጣጠረችው ጎላን የሚኖሩ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ድሩዝ የሚባሉ ጎሳ አባላት መኖሪያ ነበር። እነዚህ አሁንም ከእስራኤላዊያን ጋር እየኖሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ድሩዞች የእስራኤልን ዜግነት አልተቀበሉም፤ አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው እነዚህ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንደ ሶሪያዊያን ነው የሚቆጥሩት።

ቢቢሲ እንደዘገበው ደግሞ ሶሪያ የጎላን ተራራማ አካባቢዎችን እ.ኤ.አ ከ1948 እስከ 1967 በተቆጣጠረችበት ወቅት በሰሜናዊ እስራኤል አቅራቢያ ጥቃት ለማድረስ ያላት ቁልፍ ቦታ ነበር። እስራኤል በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት የሶሪያን መዲና ደማስቆን መመልከት የሚቻላት ከጎላን ተራራዎች መሆኑም አንዱ ማሳያ ነው። የሶሪያን ወታደሮች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርም ትጠቀምበታለች።

በተመሳሳይ ለሶሪያም ጎላን ከእስራኤል ጋር ባላት ቁርሾ የሚደርስባትን ጥቃት ለመከላከልም ሆነ ለማጥቃት ቁልፍ ቦታ ነው። ከፍታዎቹ የሶሪያን እንቅስቃሴ ለመከታተል ለእስራኤል ጥሩ ቦታ ይሰጧታል። የመሬት አቀማመጡ ከሶሪያ ለሚመጣ ማንኛውም ወታደራዊ ግፊት ተፈጥሯዊ መከላከያ ኃይል ሆኖ ያገለግላታል።

አካባቢው ለም እና እንስሳትም የሚጠጡት ውኃ የሚያገኙት አካባቢ ነው። ውኃ ውድ በሆነበት በመካከለኛው ምሥራቅ በጎላን ተራራ ውኃ የሚገኝበት ቁልፍ ቦታ መሆኑን ልብ ይሏል።

ጎላን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሚገባው የዝናብ ውኃ የሚገኝበት አካባቢም ነው፡፡ እስራኤል እ.ኤ.አ ከ1967 በፊት ወደነበረው ይዞታዋ ትመለስ የሚለው የሶሪያ ጥያቄ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም እንዳይወርድ ምክንያት ሆኗል።

እ.አ.አ በ1973 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ሶሪያ የጎላን ተራሮች መልሶ ለመያዝ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ብታደርስም ድንገተኛ ጥቃቱ ከሽፏል። ሮይተርስ እንደዘገበው እ.ኤ.አ በ1973 በአረብ እና በእስራኤል ጦርነት ሶሪያ ጎላንን መልሳ ለመያዝ ብትሞክርም ሙከራዋ ከሽፏል።

እ.ኤ.አ. በ1974 እስራኤል እና ሶሪያ የጦር መሳሪያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ጎላን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአንፃራዊነት ጸጥ ብሎ ቆይቷል።

እ.ኤ.አ በ2000 እስራኤል እና ሶሪያ ጎላንን ወደነበረበት መመለስን እንዲሁም እና የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ ንግግሮችን አድርገው ነበር። ነገር ግን ድርድሩ ሲፈርስ ከዚያ በኋላ የተደረጉ ንግግሮችም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ሶሪያ ከመላው ጎላን እስካልወጣች ድረስ ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት እንደማትደርስ አጥብቃ ትናገራለች።

እስራኤል በበኩሏ ከዐሥር ዓመታት በላይ በዘለቀው የሶሪያ የርስ በርስ ጦርነት እስራኤልን ሊያጠቁ የሚፈልጉ ኃይሎች ጎላንን እንደ መሸሸጊያ ቀጣና ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል ስጋት አለባት።

በሌላ በኩል የአሳድ መንግሥት የረዥም ጊዜ አጋር የሆነችው ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሶሪያ ድንበር ላይ ኃይሏን ለማጠናከር እየጣረች ነው ሲል የእስራኤል መንግሥት ስጋቱን ገልጿል። እስራኤል ከአሳድ ውድቀት በፊት በነበሩት ዓመታት በሶሪያ ውስጥ ተጠርጣሪ የኢራን ወታደራዊ ንብረቶችን በቦምብ ስትደበድብ ነበር። የአሳድ መንግሥት መውደቁን እና ሀገሪቱ በአማጺ ቡድኑ ቁጥጥር ስር መግባቷን ተከትሎ የጎላን ተራራን ተቆጣጥራለች፤ ይህንን ተከትሎ እየተወገዘች ነው፡፡

የአሁኑን የእስራኤልን  ዕቅድ ከተቃወሙት መካከል ጀርመን አንዷ ናት፤ የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ  አሳድ ከስልጣን ከወረደ በኋላ የሶሪያን ፀጥታ እና መረጋጋት ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እድሎችን የማበላሸት ርምጃ ነው ሲል የእስራኤልን  እቅድ አውግዟል፡፡ ሁሉም የአረብ ሀገራት እስራኤልን እየወቀሱ ሲሆን በተለይ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “የሶሪያን ግዛት በቁጥጥር ሥር ማዋል ነው። ይህም የ1974 ስምምነትን ይጥሳል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከሰሞኑ በአማፂያኑ አማካኝነት አሳድ በመብረቃዊ ጥቃት ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የእስራኤል መንግሥት የጎላንን ሕዝብ በእጥፍ ለማሳደግ የ40 ሚሊዮን ሰቅል (11 ሚሊዮን ዶላር) ዕቅድ አጽድቋል።

እስራኤል ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ጎላን በእስራኤል እጅ ለዘለዓለም እንደሚቆይ ካወጀች በኋላ ጎላንን ማጠናከር ቁልፍ እንደሆነ ነው በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል ያሳወቀችው።

“ሶሪያን ለመጋፈጥ ምንም ፍላጎት የለንም። እስራኤል በሶሪያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ የሚወሰነው በመሬት ላይ ባለው ተጨባጭ እውነታ ነው” ሲሉ ኔታንያሁ በቪዲዮ የተለቀቀ ልዩ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ በዘገባው እንዳስታወሰው እ.ኤ.አ በኅዳር ወር 2024 እስራኤል ከሶሪያ ጋር የሚለያትን አካባቢ በማለፍ ግንባታ እያደረገች ነው የሚል ቅሬታ በሶሪያ እና በተባበሩት መንግሥታት ቀርቦባት ነበር።

እስራኤል በሶሪያ  በሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎች እና የምርምር ማዕከላት ላይ ያነጣጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ  የቦምብ ጥቃቶችን ስታደርስ መቀቆየቷን ያስታወሰው ደግሞ አልጀዚራ ነው።

የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ ወደ እስራኤል መሬት በመግባት በእስራኤላዊያን ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ጦርነት ከተቀሰቀሰ አካባቢው ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል፤ በዚህም ከ45 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን እንደሞቱ አልጀዚራ ዘግቧል፤ ጦርነቱ አድማሱን በማስፋትም ወደ ሊባኖስ ዘልቋል፡፡

ከሰሞኑ የባሻር አል አሳድ መንግሥት መውደቁን ተከትሎ ደግሞ የደህንነት ስጋት አለብን በሚል እስራኤል በጎላን አካባቢ አዲስ የመስፋፋት ዘመቻን ጀምራለች፤ ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ተጨማሪ ውጥረትን አስከትሏል፡፡፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የታኅሳስ 14  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here