የመካከለኛዉ ምሥራቅ ፍጥጫ

0
145

የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

እስራኤል፤ በራሷና ምዕራባውያን መንግሥታት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሃማስ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በሰላማዊ ዘጎቿ ላይ ያደርሰውን ግድያና እገታ ተክትሎ፣ በጋዛ የከፈተችውን ጦርነት በማስፋት በሊባኖስ ሌላ የጦርነት ግምባር ከፍታለች። በሊባኖስ የሚገኘውና በኢራን ይደገፋል የሚባለው እስላማዊ ድርጅት ሂዝቦላ፤ እስራኤል በሀማስ ላይ የከፈተችውን ጦርነት በማውገዝ እና እየደረሰ ያለውን ውድመት በመቃወም፣ ከደቡብ ሊባኖስ በኩል በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲያደርስ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ኃይል ለማስወገድና ከቡድኑ የሚደርስባትን ጥቃት ለመከላከል በሚል በቡድኑ ላይ ጦርነት ከፍታ ቆይታለች።
የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ወደሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ይስፋፋል ተብሎ ተሰግቷል። ኢራን እና ሌሎችም የውጭ አካላት በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል። ሐማስ ያለፈው መስከረም መጨረሻ እስራኤል ላይ በሰነዘረው ጥቃት ውስጥ ኢራን እጇ እንደሌለ ብትገልጽም፣ እስራኤል ላይ ‘አስደንጋጭ የመሬት መንቀጥቀጥ’ አይነት የሆነውን ጥቃት እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
ኢራን መጀመሪያ ላይ ከእስራኤል ጋር በቀጥታ አልተጋጨችም። ሆኖም ኢራን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የምትደግፋቸው እና ራሳቸውን ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ ብለው የሚጠሩ ቡድኖች ከእስራኤል ጋር እየተዋጉ ነው። እነዚህም የሊባኖሱ ሄዝቦላህ፣ የየመኑ ሁቲ እና በኢራቅ ያሉ የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ናቸው። አብዛኞቹን ቡድኖች አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት ሽብርተኛ ብለው ፈርጀዋቸዋል።
የጋዛ ጦርነት በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል ያለውን ውጥረት ዳግመኛ ቀስቅሷል። ሄዝቦላህ ሐማስን በመደገፍ በሰሜናዊ እስራኤል አካባቢዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። በመስከረም 26/2016 ዓ.ም የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ ባለው ቀን በእስራኤል ይዞታ ሥር ባሉት የሼባ እርሻዎች ላይ ሄዝቦላህ ጥቃት ከፍቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። እስራኤል በምላሹ በአካባቢው ያሉ የሄዝቦላህ መጠለያ ድንኳኖችን ዒላማ አድርጋ የአጸፋ ጥቃት ፈጽማለች። የሊባኖስ መከላከያ እንዳለው በዚህ ጥቃት ሊባኖሳውያን ተጎድተዋል። “በቀጠናው ውስጥ እና ውጭ” ካለው የሐማስ አመራር ጋር ግንኙነት እንዳለው ሄዝቦላህ አስታውቋል።
የጋዛ ጦርነት ተጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ የሁቲ ንቅናቄ እስራኤል ላይ በሚፈጸመው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ሆነ። ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ የሁቲ መሪ አብዱል-ማሊክ አል-ሀውቲ፣ የእስራኤል ድርጅቶች ንብረት የሆኑ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር አስታወቀ። ከዚያም በተለይም በባብ ኤል-ማንደብ አቅጣጫ በቀይ ባሕር በኩል ወደ እስራኤል የሚጓዙ መርከቦች ዒላማ ሆኑ። እነዚህ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል። መርከቦች በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር በደቡብ አፍሪካ በኩል ዞረው እንዲሄዱ አድርገዋል።
በታኅሣሥ ወር ሁለት የእስራኤል መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ሁቲዎች አስታወቁ። ከዚህ በፊት የእስራኤላዊ ነጋዴ መርከብን ይዘዋል። ሁቲዎች በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የነዳጅ መኪና የሚሳዔል ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ጥር ላይ የመን ውስጥ አሜሪካ የአየር ጥቃት ፈጽማለች። በየመን ምዕራባዊ አካባቢ አል ሁዴይዳህ የሚገኘውን ራስ ኢሳ የነዳጅ ቀጠና የአሜሪካ እና ዩኬ የአየር ጥቃት ዒላማ ማድረጉን ሁቲዎች ገልጸዋል። ቀጠናውን ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ ኃይሎች ተባብረው ነበር ሁቲዎች ላይ ጥቃት የከፈቱት።
እስራኤል በሊባኖስ የአየር ጥቃት ስትፈጽም ነገሮች የበለጠ ተካረዋል። በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ እስራኤል በቤይሩት የሺዓዎች መኖሪያ በሆነው ዳህያህ አካባቢ በፈጸመችው ጥቃት የሐማስ ምክትል ኃላፊ እና የዌስት ባንክ ተጠሪ የነበረው አል-አሩሪ ተገደለ። አል-አሩሪ በሐማስ እና በሄዝቦላህ መካከል ያለው ቁልፍ አገናኝ ነበር ስትል እስራኤል ገልጻለች። ከቀናት በኋላ ሄዝቦላህ ወደ 40 የሚደርሱ ሮኬቶች ወደ እስራኤል ሜሮን አየር ኃይል ተኩሷል። ይህንንም በእስራኤል ለተፈጸመው ግድያ “የመጀመሪያ አፀፋዊ ምላሽ ነው” ሲል ነበር ሄዝቦላህ ጥቃቱን የገለጸው። በጥር መጀመሪያ ላይ ደግሞ በሌላ የእስራኤል የአየር ጥቃት የሄዝቦላህ ራድዋን ኃይል ምክትል ኮማንደር ዊሳም አል-ታዊል ተገለደ።
በጥር ወር መጨረሻ ላይ በሰሜን-ምሥራቅ ዮርዳኖስ በሚገኘው ‘ታወር 22’ በተባለው የአሜሪካ ወታደሮች ሰፈር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተገደሉ። በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው አካባቢ በደረሰው ጥቃት 34 ሰዎች ተጎድተዋል።
ጥቃቱ የደረሰው በሶሪያ ግዛት እንጂ በዮርዳኖስ አይደለም ስትል ዮርዳኖስ አቋሟን አስታውቃለች። የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቱን አውግዘዋል። በሶሪያ እና ኢራቅ የሚንቀሳቀሰው አክራሪው ታጣቂ ቡድን የሚደገፈው በኢራን ነው ብለዋል። አሜሪካ እጃቸው ያለበትን አካላት ተጠያቂ እንደምታደርግም ተናግረዋል።
የኢራቅ ታጣቂ ቡድን ካታይብ ሄዝቦላህ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል። ይህ ቡድን የሚመራው በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንደሆነ አሜሪካ አስታወቃለች። ነገር ግን ቡድኑ ከኢራን ጋር ምን ያህል ትስስር እንዳለው በግልጽ አይታወቅም። ኢራን ይህንን ጥቃት የፈጸመውን ቡድን አልደገፍኩም ብላለች።
ኢራን ከእስራኤል ጋር ከዚህ ቀደም ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ አልገባችም። ያለፈው ሚያዝያ ላይ በደማስቆ የሚገኝ የኢራን ቆንጽላ ላይ እስራኤል ጥቃት አድርሳለች። ከተገደሉት መካከል የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አባላት ይገኙበታል። ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል መሐመድ ራዛ ዛህዲም በዚህ ጥቃት ተገድለዋል። በወሩ መጨረሻ ላይ ኢራን በሰው አልባ አውሮፕላን እና በሚሳዔል የመጀመሪያውን ቀጥተኛ ጥቃት እስራኤል ላይ ሰነዘረች።
በዚህም በኔጌቭ ያለ የእስራኤል አየር ኃይልን ዒላማ ማድረጓን ኢራን አስታውቃለች። የእስራል ጦር እንዳለው፣ አብዛኞቹ ሚሳዓሎች እስራኤል ከመድረሳቸው በፊት እንዲከሽፉ ተደርጓል። በኢራን መከላከያ ሥርዓት ላይ የተወሰነ የአየር ጥቃት በመፈጸም አፀፋዊ ምላሽ ቢሰጥም፣ እስራኤል በይፋ ጥቃቱን መፈጸሟን አላመነችም።
ከሰኔ እስከ ሐምሌ ድረስ ባለው ጊዜ በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ያለው ውጥረት እጅጉን ተባብሷል። ሄዝቦላህ ጥቃቱን ሲያጠናክር እስራኤል ከፍተኛ አመራሮቹን እየገደለች ነው። ቡድኑ ሐምሌ መጀመሪያ ላይ በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል እንዲሁም በሜሮን አየር ኃይል ሮኬቶች ተኩሷል። በጥቃቱ ሳቢያ በእስራኤል ይዞታ ሥር ባለው ጎላን ኮረብታ አካባቢ እግር ኳስ እየተጫወቱ የነበሩ 12 ታዳጊዎች እና ወጣቶች ተገድለዋል።
ሄዝቦላህ ጥቃቱን እንዳልፈጸመ ቢያስታውቅም፣ እስራኤል በምላሹ በሊባኖስ ሰባት የሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች። ሐምሌ ላይ በኢራን የሚደገፈው የየመኑ ሁቲ ቡድን በሚቆጣጠረው የቀይ ባሕር አካባቢ የሆነው ሆዴይዳህ ላይ እስራኤል ጥቃት ፈጽማለች። በጥቃቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ ከ80 በላይ ተጎድተዋል። ሁቲዎች ከዚህ ጥቃት አንድ ቀን በፊት በቴል አቪቭ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አድርሰው አንድ ሰው ሲሞት ስምንት ተጎድተዋል።
የሄዝቦላህ ከፍተኛ ኮማንደር ፉአድ ሹክር በቤይሩት በተፈጸመ የአየር ጥቃት በተገደለ በሰዓታት ውስጥ የሐማስ መሪ ኢስማዔል ሃኒያ በቴህራን አዲሱን የኢራን ፕሬዝዳንት በዓል ሲመት ለመታደም በሄዱበት ተገድለዋል። ኢራን ለሐማስ መሪ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ ብታደርግም እስራኤል ግን እስካሁን ኃላፊነት አልወሰደችም። እነዚህ ክስተቶች ተደማምረው በኢራን እና እስራኤል መካከል ቀጥተኛ እና መጠነ ሰፊ ግጭት ይነሳል፣ ቀጠናውንም ያዳርሳል የሚለውን ስጋት አባብሶታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅን ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳቸው ሊያደርጉት እንደሚችሉ ሲኤን ኤን ዘግቧል፡፡ በመጀመሪያው የምርጫ ዘመናቸው ሳውዲ አረቢያን በመጎብኘት እና በፍልስጤማዊያን እና በእስራኤላዊያን መካከል ያለውን ውጥረት ለመቀነስ ሞክረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው በመቀበላቸው ውጥረቱን አባብሰዋል። አሁንም መሰል ጉዳይ ፈጽመው ችግሩን እንዳያባብሱ ስጋት አለ ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የኢራን ከፍተኛ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኔይ በእስራኤል እና በዩናይትድ ስቴትስ ላይ “በኢራን ላይ ለሚያደርጉት ነገር” እና በተላላኪዎቿ ላይ “ጥርስ የሚሰብር ምላሽ” እንደሚሰጡ መናገራቸውን ኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡ መሪው ኢራን የኑክሌር ፖሊሲዋን ጠበቅ ልታደርግ እንደምትችልም ገልጸዋል፡፡ የተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን የጉዞ ርቀት ትጨምራለችም ተብሏል፡፡
በአሜሪካ ዶናልድ ትራም መመረጣቸውን ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ትራም መመረጣቸው ለሀገራቸው እና ለአሜሪካ ታሪካዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here