የመኸሩ ተስፋ እና ስጋት

0
197

የ2015/16 የምርት ዘመን በግብርና ግብዓት እጅጉን ተፈትኖ አልፏል:: ግብዓት በበቂ መጠን አለመቅረቡ እና የዋጋው ከወትሮው እጅጉን ማሻቀቡ አርሶ አደሩ በበጋው ወቅት ያቀደውን የአፈር ማዳበሪያ እንዳያሳካ አድርጎታል። በምርት ዘመኑ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የታጣውን የሰብል ምርት በማካካስ የክልሉን ምርታማነት አስቀጥሎ ለመጓዝ ይበልጥ ትኩረት ቢሰጥም የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እጥረቱ ግን የምርት መቀነሱ ቀጣይነት እንዲኖረው አድርጓል::

በእርግጥ እንደ ሀገር ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በምርታማነት ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በከፍተኛ ደረጃ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም ከፍተኛ የንቅናቄ ሥራም ተሠርቷል:: ይሁን እንጂ የክልሉ ግብርና ቢሮ በዓመቱ 165 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ የቁም ሰብል ግመታው ከ145 ሚሊየን ኩንታል የበለጠ ምርት እንደማይገኝ አረጋግጧል:: በዚህም አገላለጽ መሰረት በዓመቱ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የታዩ ችግሮች የ20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መቀነስ እንዲስተዋል አድርጓል::

ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በ2016/17 የምርት ዘመን   ፈተና እንዳይሆንም ተስግቷል:: በእርግጥ የክልሉ ግብርና ቢሮም ሆነ የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር ለዓመቱ የመኸር ወቅት በቂ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው:: ይሁን እንጂ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት (ጦርነት) የግብርና ግብዓትን በወቅቱ እና በሚፈለገው መጠን ወደ አርሶ አደሩ ለማቅረብ ፈተና መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል::

በሰሜኑ ጦርነት እና በተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለተከታታይ ዓመታት ሰፊ የእርሻ ማሳቸውን  ጾም ያሳደሩ አካባቢዎች በርካታ ናቸው::  አሁንም ድረስ በክልሉ የቀጠለው ግጭት ደግሞ ግብዓት በወቅቱ በየአካባቢው ተደራሽ እንዳይሆን  በማድረጉ የመኸር ወቅቱ ሌላው ስጋት ነው ሲሉ ከወዲሁ ትኩረት እንዲሰጥ  እየጠየቁ ነው::

በጃናሞራ ወረዳ ክልል  የተባለች ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር እንዳለ ተገኘ በስልክ በሰጡን አስተያየት ድርቁ የዓመት ቀለባቸውን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን አሳጥቷቸዋል:: መንግሥት የነፍስ አድን ሥራ እየሠራ ቢሆንም እርሳቸው ግን ከጠባቂነት ወጥተው በምግብ ራሳቸውን ለመቻል ሌት ከቀን ያሰላስላሉ:: ይህ ሀሳባቸው እውን እንዳይሆን የሚያደርጉ ክስተቶች ደግሞ በድርቁ ምክንያት ተከስተዋል::  በተከሰተው ድርቅ በርካታ እንስሳት መኖ እና ውኃ ፍለጋ ተሰደዋል፣ የቀሩትም ሞተዋል:: ጥቂት የማይባሉትም ተሸጠው  ሕይወትን ለማዳን ለእለት ተግባር ውለዋል::

የእንስሳት በድርቁ ምክንያት ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው የ2016/17 የመኸር እርሻ ፈተና ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ መሆኑንም አርሶ አደሩ ገልጸዋል:: በመሆኑም የግብርና ግብዓትን ጨምሮ የሞቱትንም ሆነ የተሸጡትን የእርሻ በሬዎች መልሶ በመተካት ወደ ምርት ለመግባት መንግሥት እንደ ብድር ያሉ አማራጮችን ተግባራዊ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል::

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እ.አ.አ ጥር 10 ቀን 2024 የሰብዓዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት 173 ሺህ 600 እንስሳት መኖ ፍለጋ ተሰደዋል፤ 86 ሺህ 700 የሚሆኑት ሞተዋል። የድርቁ ተጽእኖ  ከመቀጠሉ አንጻር በአሁኑ ወቅት ያለው የችግሩ ስፋት ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል::

የሰሜን ጎንደር ዞን ለእርሻ የሚውል 156 ሺህ 659 ሄክታር መሬት አለው:: ይሁን እንጂ ባለው ጸጋ ልክ ምርታማነቱን ማረጋገጥ እንዳልቻለ፣ ለዚህም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች እና የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ገዥ ምክንያቶች መሆናቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ  ኃላፊ አቶ ጌታቸው አዳነ በስልክ አስታውቀዋል::

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በ2015 ዓ.ም የተከሰተው የዝናብ እጥረት 76 ሺህ 277 ሄክታር ማሳ ከምርት ውጪ አድርጓል:: ከዚህም 878 ሺህ 623 ኩንታል ምርት ታጥቷል:: ይህም የበርካታ አርሶ አደሮች ሕይወት አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል::

አሁንም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መናጋት ለዞኑ ምርት መቀነስ ተጨማሪ ምክንያት እንዳይሆን እየተፈጠረ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ ባለፉት ዓመታት የታጣውን ምርት ለማካካስ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ኃላፊዉ አስታውቀዋል:: አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ወደ ማምረት እንዲገባ ማነቃቃት፣ ምርታማነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ የግብርና ግብዓት በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጓል::

በዞኑ በመኸሩ ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል:: ለዚህም 91 ሺህ 880 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዷል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም ከ20 ሺህ 165 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ቀርቧል:: በዞኑ ከሚያዚያ ወር መግቢያ ጀምሮ ወደ ዘር የሚገቡ አራት ደጋማ ወረዳዎች ከመኖራቸው ጋር በተገናኘ አሁናዊ ስርጭቱ በሚፈለገው መጠን እንዳልሆነ ተመላክቷል:: መምሪያው ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኀይል ጋር በመቀናጀት ግብዓትን በወቅቱ ለማድረስ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው::

በጸጥታ ችግሩ ምክንያት እየተስተጓጎለ ካለው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በተጨማሪ ስርቆት ሌላኛው ስጋት መሆኑን ጠቁመዋል:: ኃላፊው የችግሩን ስፋት ያሳዩት እስካሁን 17 የንብረት ክፍል ሠራተኞችን ከሥራቸው የማሰናበት እና በሕግ የሚጠየቁትንም በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን በመግለጽ ነው::

ባለፈው ዓመት በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት አርሶ አደሩ ከምርት ውጪ ሆኖ ዓመቱን በጠባቂነት ማሳለፉ፣ እንስሳቱም በረሀብ እና በውኃ እጦት ለሞት እና ለፍልሰት መዳረጋቸው ወደተሟላ እርሻ እንዳይገባ ሊያደርጉት የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው:: በመሆኑም መምሪያው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ተሳታፊ በማድረግ የድርቅ መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ነድፎ በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል:: በዚህም እስካሁን ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ 750 ኩንታል ምርጥ ዘር ማቅረቡን፣ ሌሎችም ለማቅረብ በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል::

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ በተከሰተ ድርቅ፣ በጎርፍ እና የተወሰኑ አካባቢዎችም ከትግራይ ኀይሎች ነጻ ባለመሆናቸው ምክንያት ከ65 ሺህ 547  ሄክታር በላይ መሬት ከምርት ውጭ ሆኖ መክረሙን የብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲሱ ወልዴ በስልክ አስታውቀዋል:: በዚህም 661 ሺህ 17 ኩንታል ምርት ታጥቷል::

ብሄረሰብ አስተዳደሩ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ያጣውን ምርት በከፍተኛ ደረጃ ለመመለስ በ2016/17 የምርት ዘመን ከ120 ሺህ 638 ሄክታር በላይ  መሬት በዘር ለመሸፈን አቅዷል:: እጁን ለድጋፍ የዘረጋው ሕዝብ በምግብ ራሱን እንዲችል የኩታ ገጠም /የክላስተር/ የአስተራረስ ዘዴ ተግባራዊ ይደረጋል:: ምርታማነትን በሚፈለገው ልክ ለማረጋገጥ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያን  በበቂ መጠን እና በወቅቱ ማሰራጨት ይገባል::

ለእቅዱ ተግባራዊነትም ብሄረሰብ አስተዳድሩ በመኸሩ ለሚሸፍነው የማሳ መጠን 69 ሺህ 119 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ በጥናት ተለይቷል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ 34 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን መምሪያ ኃላፊዉ አስታውቀዋል:: የፀጥታ ችግሩ አሁንም የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ እንዳይቀርቡ እክል እንዳይሆን  ግን  ስጋታቸውን አመላክተዋል::

የተፈጠረው የሰላም መናጋት በተለይ የግብርናው  ዘርፍ በእጅጉ እንዲጎዳ እያደረገ በመሆኑ ሕዝቡ ከመንግሥት የፀጥታ ኀይላት ጎን በመሰለፍ ባለፉት ዓመታት የተከሰተውን የምርት መቀነስ ለማካካስ እንዲተጋ የግብርና መምሪያ ኃላፊዎች ጠይቀዋል:: ወደ ግጭት የገቡ ወገኖችም የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ ሰላማዊ የትግል አማራጮችን በመጠቀም ክልሉን ከቀውስ ሊታደጉት እንደሚገባ ተመላክቷል::

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳሕሉ (ዶ/ር) ወቅታዊ የግብርና ግብዓት አቅርቦትን በማስመልከት መጋቢት 06 ቀን 2016 ዓ.ም ከአማራ ራዲዮ እና ኤፍ ኤም ጣቢያዎች  ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት የግብዓት አቅርቦት ለ2016/17  የመኸር ወቅት ችግር አይሆንም:: በመኸሩ አምስት  ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይታረሳል:: ባለፈው ዓመት ያጋጠመውን የምርት እጥረት መፍታት ደግሞ የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫ ነው::

ክልሉ 8 ሚሊዮን 57 ሺህ 900 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ እንዲፈጸም ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል:: የሁሉንም ግዥ ለመፈጸም ውል መያዙንም አስታውቀዋል:: እስካሁንም ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል  ግዥ ተፈጽሞ ወደብ ላይ ደርሷል:: ከዚህ ውስጥ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተጓጉዞ ወደ ዩኒየኖች ገብቷል:: አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ገብቷል:: ከዚህም ውስጥ 600 ሺህ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል:: ይህም ለመኸር ምርት እና ለመስኖ አገልግሎት የሚውል ነው ተብሏል:: የምርጥ ዘር አቅርቦትም በበቂ መጠን መኖሩን አረጋግጠዋል::

የክልሉ መንግሥት የግብርና ግብዓት እንደባለፈው ዓመት ፈተና እንዳይሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢገኝም በወቅቱ ወደ አርሶ አደሮች እንዲደርስ  የሚደረገው ጥረት  ግን በክልሉ በተፈጠረው የሰላም መናጋት ምክንያት እየተፈተነ መሆኑን ቢሮ ኃላፊዉ አስታውቀዋል:: ይህም በአርሶ አደሮች ህልውና እና በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ጫና የሚያሳድር አካሄድ በመሆኑ የትኛውም አይነት የፖለቲካ ጥያቄ ሊኖር ቢችል ልማት እና ፖለቲካን ለይቶ ማየት እንደሚገባ አሳስበዋል:: በመሆኑም ሁሉም ዜጋ በሕዝብ ልማት ላይ የተደቀነ እኩይ ዓላማ ያላቸውን አካላት በጋራ እና በቁርጠኝነት መታገል እንደሚገባ አሳስበዋል::

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ምክክር ባደረገበት ወቅት የተገኙት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው የሰብል ምርታማነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል:: እየገባ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት እና በጥንቃቄ ማሰራጨት፣ አርሶ አደሮች በተረጋጋ መንፈስ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ፣ የግብርና ባለሙያዎችንም በየደረጃው ወደ ሥራ ማስገባት በዓመቱ ለማሳካት ለታቀደው የሰብል ምርት ውጤታማነት እንደሚያበቃ ተናግረዋል::

በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያጋራው መረጃ እንደሚያመለክተው ለ2016/17 የምርት ዘመን ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ኢትዮጵያ በማጓጓዝ ከክረምት ወራት በፊት ለአርሶ አደሩ ለማድረስ በትኩረት እየተሠራ ነው:: ከፈረንጆቹ ሕዳር 3 ቀን 2023 ጀምሮ ይህንን መረጃ እስካጋራበት መጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጊዜ  ድረስ 939 ሺህ 560 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ ደርሷል:: ከዚህ ውስጥ ከ905 ሺህ 525 ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል:: ቀሪውን የማጓጓዝ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል::

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እና ሌሎችም ማኅበራዊ ቀውሶች ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል ለምታደርገው ጥረት ገዳቢ ክስተቶች ናቸው:: በመሆኑም በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ሀገሪቱ ወደነበራት ሰላም ተመልሳ ወደ ጠንካራ የልማት ሥራ እንድትሸጋገር የበኩላቸውን ጥረት ሊወጡ ይገባል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here