የመኸር እርሻዉ ሲፈተሽ

0
166

የግብርና ሥራ ዓመቱን ሙሉ የሚከወን ተግባር ቢሆንም ክረምት ግን ከሌሎች ጊዜያት በተለየ የሚበዛበት ነው። አርሶ አደሩ ሩጫው ከጊዜ፣ የተፈጥሮ ኡደትን ተከትሎ ከሚዘንበው ዝናብ ጋር ነው። የታታሪ አና የሰነፍ ገበሬ የልፋት እና የውጤት መጠንም በተግባር የሚረጋገጥበት ነው። ለዚህም ነው

“ያረሰ’ማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፣

ወፍጮው እንዳገሳ መስከረም ዘለቀ!” በማለት ነው ለታታሪ ገበሬ የተገጠመለት።

በሌላ በኩል ጊዜውን በአግባቡ ያልተጠቀመ እና የግብርና ሥራውንም ያልከወነ ገበሬ

“በሰኔ ካልዘሩ በጥቅምት ካልለቀሙ፣

እህል የት ይገኛል ከድንበር ቢቆሙ!” ተብሎ ተገጥሞላታል።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በግብርና ሥራ ላይ ለተመሰረቱ ሀገራት የግብርና ግብዓት በወቅቱ ማቅረብ እና ማሰራጨት ግንባር ቀደም ተግባር ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ ደግሞ የተሻለ ምርት በማምረት ጎተራው ይሞላል፤ ገበያው ይጠግባል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአርሶ አደሩ ልፋት ባሻገር የግብርና ግብዓት በወቅቱ መቅረብ ልፋቱን በውጤት እንዲታጀብ ያደርጋል። አርሶ አደሩ ማሳውን በወቅቱ ደጋግሞ ካረሰ እና የሚያስፈልገውን ግብዓት በወቅቱ ካገኘ በቂ ምርት አምርቶ ቤተሰቡን ከመመገብ አልፎ ለገበያ ያቀርባል። ይህም እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማስታገስ ያስችላል።

በአማራ ክልል በ2015/2016 የምርት ዘመን በተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት በአርሶ አደሩ ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ የሚዘነጋ አይደለም። ወቅታዊ የእርሻ ሥራውን በመተው በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ችግሩን ለማሰማት ውድ ጊዜውን አባክኗል። ላልተገባ ወጭም ተዳርጓል። በመሆኑም የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት ከባለፈው ዓመት ትምህርት በመውሰድ ለ2016/2017 የምርት ዘመን በቂ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከግዥ ጀምሮ እስከ ማጓጓዝ ድረስ በትኩረት እየሠሩ ይገኛል። በአማራ ክልል በ2016/2017 የምርት ዘመን የተሻለ የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ መሆኑን አርሶ አደሮች እና  የክልሉ ግብርና ቢሮ የሥራ ኃላፊው ተናግረዋል።

በዚህ ዕትማችንም የመኸር እርሻን በተመለከተ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እናስነብባችኋለን።

አርሶ አደር ተዋቸው በሪሁን የደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ወንጨጭ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ደጋግሞ ማረስን እና ሰብልን መንከባከብ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ አስረድተዋል። ምርታማነትን ለማሳደግ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂ አስፈላጊ መሆናቸውን በማንሳት እርሳቸውም መሬታቸውን በትራክተር በማረስ ጉልበት እና ጊዚያቸውን እንደሚቆጥቡ ነግረውናል። በትራክተር ማረስ የበሬውን እና የሰውን ድካም ይቀንሳል፣ ዘርን ወቅቱ ሳያልፍ ለመዝራት እንዲሁም የተሻለ ምርት ለማምረት ያስችላል ብለዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት ስድስት ሄክታር መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ በተለያዩ ሰብሎች ሸፍነዋል። በቆሎ፣ ዳጉሳ እና በርበሬ ዘርተው እየተንከባከቡ እንደሆነ ለበኩር በስልክ ተናግረዋል። ከባለፈው ዓመት የተሻለ ግብዓት ማግኘታቸውን የተናገሩት አርሶ አደር ተዋቸው፤ ተጨማሪ ዩሪያ እንደሚያስፈልጋቸው  ነግረውናል።  “በ2015/2016 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ከፍተኛ እጥረት ገጥሞኝ ነበር” ያሉት አርሶ አደሩ  በሕገ ወጥ ነጋዴዎችም እንደተመዘበሩ ሐሳባቸውን አጋርተውናል። ህይወታችን የተመሠረተው በግብርና በመሆኑ ግብዓት በወቅቱ መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል። በወቅቱ ማረስ፣ መዝራት፣ መኮትኮት፣ ማረም እና ከተባይ መጠበቅ ደግሞ “የእኛ የአርሶ አደሮች የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባል” ሲሉ  ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን በ2016/2017 የምርት ዘመን 525 ሺህ ያህል ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዷል። በዚህም 19 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። እስካሁንም 505 ሺህ 590 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ የሺጥላ ፍቃዴ ተናግረዋል። እንደ መምሪያ ኃላፊው ማብራሪያ 4 ሺህ 222 መሬት በትራክተር ማረስ ተችሏል። ለውጤታማነቱም በዞኑ ከ965 ሺህ በላይ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ  እንደሚያስፈልግ በዕቅድ ተይዟል። ከ622 ሺህ በላይ ኩንታል ያህሉ ወደ ዞኑ የገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 98 በመቶ (ስድስት መቶ  10 ሺህ ያህል) የሚሆነው ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። ቀሪው የአፈር ማዳበሪያ ፈጥኖ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ከሚመለከታቸው ጋር እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

ሌላው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አደራው አበበ እንደነገሩን ወቅቱ የግብርና ሥራዎች በስፋት የሚከናወኑበት እና ተስማሚ ጊዜ መሆኑን ያነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም በፈለጉት ጊዜ ግብዓት በማግኘታቸው ከባለፈው ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት)  በማዘጋጀትም ይጠቀማሉ።

አርሶ አደሩ በስልክ እንደነገሩን አራት ጥማድ (አንድ ሔክታር) መሬታቸውን በበቆሎ፣ ስንዴ፣ ድንች እና ገብስ ዘር ሸፍነዋል። በዘር የተሸፈነውን ማሳቸውን እየተንከባከቡ (ማረም) እና ዩሪያ እየጨመሩ ነው። የጤፍ መሬታቸውን ደግሞ እያለሰለሱ፣ እየጎለጎሉ ነው።

የአፈር ማዳበሪያን በፍትሐዊነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳገኙም ተናግረዋል። ነገር ግን የክልሉ የሠላም እጦት በግብርና ሥራቸው ላይ ስጋት ፈጥሯል። አልፎ አልፎ የተኩስ ድምፅ ሲሰሙ ሥራቸውን አቋርጠው ከብቶቻቸው ይዘው እንደሚመለሱ ገልፀዋል። በሠላም ወጥቶ ለመግባት፤ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ሁሉን ነገር ለመከወን መሠረቱ ሠላም በመሆኑ ለሠላም ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል። ችግሮችን በይቅርባይነት እና እርቅ በመፈፀም ሠላም ማውረድ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በ2016/17 የምርት ዘመን ከ612 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ23 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ መኮንን ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት እስካሁን ከ609 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ታርሷል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 296 ሺህ ያህል ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አረጋግጠውልናል። ምርታማነትን ለመጨመር የተሻሻሉ የግብርና አሠራሮችን ለአብነትም በመስመር  መዝራትን ትኩረት አድርጓል። 16 ትራክተሮችን ወደ ሥራ በማስገባት 4 ሺህ 433 ሄክታር ማረስ ተችሏል።

ኃላፊው እንዳሉት በምርት ዘመኑ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን  ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋል። ከዚህ ውስጥም አንድ ሚሊዮን 200 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቷል።

በሌላ በኩል የአፈር አሲዳማነት መስፋፋት ችግር ሆኗል። በመሆኑም የመሬት ለምነቱን ለመጨመር እና የተሻለ ምርት ለማምረት አሲዳማነትን በኖራ ማከም ተገቢ ነው ብለዋል። ለዚህም ከስምንት ሺህ 500 በላይ ኩንታል ኖራ ወደ ዞኑ ገብቷል። አምስት ሺህ 500 ኩንታሉ ኖራ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።  አረም ማረም፣ መኮትኮት፣ ግብዓት መጨመር፣ ከተባይ እና ከበሽታ መጠበቅ እንዲሁም ሰብሉ በጎርፍ እንዳይጎዳ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በክልሉ የተከሰተው ግጭት በግብርና ሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን አሳድሯል። በመሆኑም አርሶ አደሩ የተሻለ ምርት እንዲያመርት ሠላምን ማስፈን ይገባል ብለዋል።

ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከአምስት ሚሊዮን 17 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማረስ ተችሏል። ከዚህ ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን 117 ሺህ በላይ ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል።

ለ2016/2017 የመኸር እርሻ ሥራ የሚያገለግል ከስምንት ሚሊዮን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ በዕቅድ ተይዟል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምሳሉ ጎባው ለአሚኮ እንደገለጹት እስካሁን ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ዩኒየኖች ተጓጉዟል። ከዚህ ውስጥ ከስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ  ደግሞ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here