የመደጋገም ጉልበት

0
146

“ዩ ራን  ዘ ዴይ  ኦር ዘ ዴይ ራንስ ዩ” የሚለው ሐሳብ “ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ” ከሚለው የሀገራችን አባባል ጋር  ይቀራረባል። የፈረንጆቹ አባባል ጊዜን ካልተጠቀምህበት ይቀጣሃል ይላል። የሀገራችን አባባል ደግሞ ጊዜ ተጓዥ መንገደኛ  ነው ፈጥነህ ተሳፈር የሚል ነው።

 

በሁለቱም አባባሎች ውስጥ የሚጠቀሰው ጊዜ ነው። ጊዜ ገንዘብ አይደለም። ወርቅም አይደለም። ጊዜ ሕይወት ነው። የሰው ልጆች በምድር  ውስን ጊዜ ነው ያላቸው። ከመወለዳቸው ጀምሮ ወደ ሞት ቀናትን ይቆጥራሉ። እያንዳንዱ የሚቆጠር ቀን እና ሰዓት ወደ ሞት የሚያዳርስ መንገድ ነው።

ቶኒ ሮቢንስ “ሞሽን ክሬትስ ኢሞሽን/እንቅስቃሴ ስሜትን ይፈጥራል” በሚለው አባባሉ ይታወቃል። የሰው ልጆች ከመንቀሳቀስ፣ ከመኖር ስሜት ያገኛሉ። ከስሜት ድርጊት ከድርጊት ደግሞ ውጤት። የሚኖሩለት ምክንያት ሲኖራቸው ጠንካራ ስሜት እና ድርጊት ያገኛሉ። ውጤታቸውም እንዲሁ ጥሩ ይሆናል።

 

አስናቀች ወርቁ

“መሞከር ይሻላል ሁሉንም መሞከር፤

ይገኝ እንደሆነ አንድ ደህና ነገር”

የምትልበት ዘፈን አላት። የሰው ልጆች በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ መቆም የለባቸውም፣ በድርጊት እና ጥረት ውስጥ ማለፍ አለባቸው የሚለውን ሑሳብ ያጠናክራል። “ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፤ ወፍጮው እንዳጎራ መስከረም ዘለቀ” የሚለው ቀደምት  አባባልም ሰው የድካሙን ፍሬ እንደሚበላ ማሳያ ነው።

 

በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሀሴ  የሥራ እና የችግር ወራት ናቸው። አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት በበጋው ወራት በድግስ እና በሌሎች ማሕበራዊ ሁነቶች ያባክነዋል። ጠንካራ ሠራተኞች በጋ ከክረምት የሚበሉት አይቸገሩም። ጊዜያቸውን በከንቱ ያሳለፉ እና ዝክር እና ድግስ የባጁ ሰዎች እነዚህ የክረምት ወራት ላይ የሚበሉት የላቸውም። የጎረቤቶቻቸው ወፍጮ ሲፈጭ እነሱ ቁና ይዘው እህል ለመበደር የሰው ፊት ይቆማሉ።

ሠራተኛ ሰዎች ሁልጊዜም ዕድሎችን ያሳድዳሉ። የዕድል በሮችን ያንካኳሉ። በስራ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሰውነታቸው ኢንዶርፊን የተባለ አነቃቂ ሆርሞን ያመነጫል። ያ የመነቃቃት ስሜት ደግሞ ወደ ድርጊት አስገብቷቸው ጥሩ ፍሬ የሚያስገኝ ተግባርን ይፈጽማሉ።

 

ብዙዎቻችን በሕይወት የምንጋፈጠው ብዙ ነገር አለ። ብዙ የዕድል በሮች ተከፍተውልን ባለንበት መጽናት ሳንችል ስንቀር ተዘግተዋል። ደጋግመን መሞከር እንፈራለን። ደጋግመን መውደቅ ያስደነግጠናል። ትንሽ ሞክረን የመሳኪያው ደጃፍ ስንደርስ ተስፋ ቆርጠን እንሄዳለን።

አሜሪካዊው ጸሐፊ ማርክ ትዌይን  “ወደፊት ለመራመድ ዋናው ምስጢር መጀመር ነው። የመጀመር ምስጢር ደግሞ  ውስብስብ እና ከአቅም በላይ የሆኑ ተግባሮችህን ወደ ትናንሽ እና በቀላሉ ሊሰሩ ወደ ሚችሉ ክፍሎች ቀናንሶ በመሥራት መጀመር ነው” ይላል፡፡

 

በተገላቢጦሽ በሚመስል መልኩ ብዙዎቻችን ግዙፍ ነገርን በአንድ ቀን፣ በአንድ ጊዜ ማድረግ እና ማሳካት እንፈልጋለን። ነገሩን ሙሉ እና ጥንቅቅ አድርገን መሥራት እንመኛለን። የምንፈልገው ሙሉቀን፣ ትክክለኛ ጊዜ እና በጀት እስኪገኝ እንጠብቃለን። ሳንጀምር በሐሳብ እንቀራለን። ያ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው።

በትንሽ መጀመር አንፈልግም። በሒደት ማደግን አንመርጥም። ተራራን ድንገት ሮጠን መውጣት እንፈልጋለን። ስናስበው እንፈራለን። በወሬ እና እቅድ እንቀራለን። ምርጥ ምርጥ እቅድ እና ሐሳቦች ያላቸውን ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን አውቃለሁ። መንጠራራት የሚመስሉ የጉራ እቅዶች ወደ ተግባር እስካልተቀየሩ ድረስ ወሬ ናቸው።

 

ግቦቻችን በጣም ትልቅ ሲሆኑ እንጨነቃለን። ትክክለኛውን ሁኔታ ወይም ተስማሚውን ጊዜ እንጠብቃለን። አዕምሯችን አንድ ቀን በቂ ጊዜ ይኖረኛል በሚለው ሐሳብ ይሸወዳል። በዚህ ምክንያት ሳንጀምር ወደ ኋላ እንዘገያለን። መዘግየት ዕድሎችን እንድናጣ እና አቅማችንን ሙሉ በሙሉ እንዳንጠቀም ሊያደርገን ይችላል። ማርክ ትዌይን አሁን ጀምሩ፤ ዛሬ ነገ አትበሉ የሚለን ለዚህ ነው።

እዚህ ላይ የአንድ ገበሬ እና አህያን ታሪክ እንመልከት። ታሪኩ በሕይወት ጉዟችን የሚገጥሙንን ችግሮች ወደ ዕድል እየቀየሩ ስለ ማሸነፍ ነው የሚያወራው።

 

አንድ ቀን የአንድ ገበሬ አሮጌ አህያ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል። ገበሬው አህያውን ለማውጣት ቢሞክርም አልቻለም። አህያውም አርጅቷልና ከትልቁ ጉድጓድ መውጣት አቃተው።

በዚህ ጊዜም  ገበሬው አሳዛኝ ውሳኔ ወሰነ፡፡ አህያውን ከስቃዩ ለመገላገል በሕይወት እያለ በአፈር ለመቅበር አሰበ። ጎረቤቶቹን ጠርቶ አፈር በጉድጓዱ ውስጥ መሙላት ጀመሩ። መጀመሪያ ላይ አህያው እየሆነ ያለውን ሲረዳ በጣም በሚያሳዝን ድምጽ መጮህ ጀመረ።

 

ከትንሽ ቆይታ በኋላ አህያው ፀጥ አለ። ገበሬው ወደታች ሲመለከት ባየው ነገር ተገረመ። በላዩ ላይ በተደፋበት እያንዳንዱ የአካፋ አፈር አህያው አንድ አስደናቂ ነገር ያደርግ ነበር፡፡ ገበሬው አፈሩን  ወደ ጉድጓዱ ሲጨምርለት አህያው ከጀርባው ላይ ያራግፍና አፈር ላይ አንድ እርምጃ ወደ ላይ ይወጣ ነበር።

ይህንኑ ደጋግሞ በማድረግ የአፈሩ ክምር እየጨመረ ሄዶ ብዙም ሳይቆይ አህያው ከጉድጓዱ ወጥቶ በነፃነት ሄደ። ሊቀበርበት የነበረውን ጉድጓድ በአፈር ሞልቶ ወደ ላይ ወጣ፡፡

በሰው ልጆች ታሪክ  ውስጥ ብዙ አፈር ይደፋብናል፡፡ ችግሮች፣ መሰናክሎች፣ ትችቶች እና ተግዳሮቶች ያግጥሙናል። በዚህ ጊዜ ሁለት ምርጫዎች ይጠብቁናል፡፡ አፈሩ እንዲቀብረን መፍቀድ ወይም ደግሞ እንደ አህያው አራግፈን ከዱድጓዱ መውጣት፡፡

 

ችግሩ እንዲያሸንፈን ከመፍቀድ ይልቅ ተሻግሮ ማለፍ  ይመረጣል። ይህ ምርጫ ቀላል ግን አይደለም። ከመሞት ደግሞ በእጅጉ የተሻለ ነው። ችግር መማሪያ፣ ማደጊያ፣ ወደ ላይ መወጣጭ አማራጭ ሆኖ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታይቷል።

ይህም ታሪክ የሚያስተምረን ተስፋ አስቆራጭ በሚመስሉ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን በብልሃት እና በጽናት ችግሮቻችንን ወደ ስኬት መወጣጫ ልናደርጋቸው  እንደምንችል ነው።

 

የአሸናፊ ሰዎች ዋነኛ መገለጫ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ የመጽናት ኃይል ነው። በርግጥም ብዙ ውድቀቶች ያጋጥሙናል። እያንዳንዱ ድርጊታችን በመጀመሪያው ሙከራ ስኬታማ አይሆንም። ነገር ግን ምስጢሩ ተስፋ አለመቁረጥ ነው። አሸናፊነት አለመውደቅ አይደለም። ከውድቀት በኋላ ተነስቶ ድጋሚ መሞከር ነው።

 

ስኬት በአንድ ጀምበር ወይም በመጀመሪያ ሙከራ የገጠማቸው ሰዎች የሉም። እስኪሳካ ድረስ ደጋግሞ መሞከር ግዴታ ነው። እያንዳንዱ ሰው በርካታ ውድቀቶችን አስተናግዷል። ስኬታማ መሆን የምንችለው በውድቀቶች ውስጥ አልፈን ብቻ ነው። ውድቀት ያልተለመደ ነገር አይደለም። እያንዳንዱ ውድቀት የሚያስተምረን ነገር አለው። እነዚህን እውነታዎች ተገንዝበው የሚሰሩ ሰዎች ውድቀቶች የስኬት መወጣጫ መሰላሎች መሆናቸውን ይረዳሉ።

 

ፈጣሪዎች፣ አሳሾች፣ አርቲስቶች፣ ጸሐፊዎች፣ ሳይንቲስቶች እና ሌሎችም በልዩ ልዩ ዘርፎች በታላቅነት የሚታወቁት  ሰዎች በመጀመሪያ ሙከራቸው አልተሳካላቸውም።  የሰማነው በተለያዩ መስኮች ያስመዘገቧቸውን የስኬት ታሪኮች ብቻ ነው። ያጋጠሟቸውን ውድቀቶች አናውቅም። ልብ የምንለው ነገር ቢኖር ውድቀት ተስፋ እንዲያስቆርጣቸው አለመፍቀዳቸውን ነው። በዙሪያችን ያለው ዓለም ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ የደረሰው አባቶቻችን በወደቁ ጊዜ ሙከራቸውን ስላልተዉ ነው።

 

ሁልጊዜም በጥረት እና ሙከራ ውስጥ መሆን፤ ደጋግሞ መሞከር ለውጤት ያበቃል። ይህ ሲባል ጽናትን ከግትርነት ጋር ማምታታት አይደለም። መጽናት እና ግትርነት ይለያያሉ። አካሄዳችን የተሳሳተ ከሆነ አቅጣጫ መቀየርም ተገቢ ነው። ብልህ መሆን ተገቢ ነው። ለውድቀት የምንሰጠው ትርጉምም መቀየር አለበት። ማቆም ማለት መተው እና መውደቅ አይደለም። የተሻለ መንገድ ሲገኝ አቅጣጫን መቀየር ማለት ነው። ጽናት ትርፍ እና ኪሳራን እያሰሉ አዋጭ በሆነው መንገድ በድግግሞሽ መራመድ ነው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here